በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በሚል ቃለ ብሥራት ሰላምታችንን እያስቀደምንና በትንሣኤው ትንሣኤያችንን እያወጅን ሰነበትን፡፡ “በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፈንታ ደስ ይለናል፡፡” እንዳለ ነቢዩ ዳዊት ፍርድህን ከሰማንበት ቃልህ፤ ምህረትህን ፣ ይቅርታህን ፤በሞት አዋጆች ፈንታ ትንሣኤና ሕይወትን፤ከባርነት ተላቀን ነፃነትን በመቀዳጀታችን የመከራውን ዘመን አስረስተህ ደስታን ሞላኸን፡፡ ከዛሬ ፪ሺ ዓመት ገደማ የበዛልን ሥጦታህ ከአበው ወደ ውሉድ እየተላለፈ ደስታው ሳይፈዝ ስሜቱ ሳይደበዝዝ “ግበሩ በዓለ በትፍስህት” እንዲል ዛሬም እንደያኔው አከበርነው፡፡ ሰውነታችን በፆም እንዳከበረችህ በመብልም አመሰገነችህ፡፡ በድካማችን፣በትካዜያችን፣በረሃብና በጥማችን፣ በሀዘንና በዕንባችን ወራትም ትዝታችን አንተ ነበርህ፤ በደስታና በሐሤት በመብልና በመጠጥ ወራትም የአንደበታችን ቅኔ የዝማሬያችን ጉልበት አንተው ነህ፡፡
“በምሴት ይደምፅ ብካይ ወበጽባህ ፍስሐ” እንዳለ ክቡር ዳዊት በጨለማ ኦሪት፣ በጨለማ ኃጢአት በጨለማ ሞትና ሲዖል በተያዝንበት ወራት አለቀስን፤ የወንጌል ብርሃን፣ የትንሣኤ ብርሃን፣ የጽድቅ ፀሐይ በወጣበት ዘመን ሐሤት እናደርጋለን፡፡ የፊትህን ብርሃን አይተናልና ቀኑን ሁሉ ደስ ይለናል፡፡ ይኸውም በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያገኘነው ዘላለማዊ ይቅርታህ ነው፡፡
ከላይ ያልነውን ሁሉ ያልነው ስለ ዐብይ ፆም ሰንበታትና ስለ ጌታችን ስቅለት ትንሽ ጽፈን ስለነበር ምነው ትንሣኤውስ? ላለመባል ነው፡፡ ትንሣኤ ካልታወጀ ካልተሰበከ ክርስትና ተብሎ ነገር የለምና፡፡ ትንሥኤውንም የማያምንና የማይሠብክ ሰውም ከመላእክት አንድነት ሊጨመር ከነቢያትና ከሐዋርያት ከጻድቃንና ከሰማዕታት ኅብረትም አንድ ሊሆን አይቻለውም፡፡ የኒህ ሁሉ መከራቸው በትንሣኤው ማመናቸው ክብራቸው ትንሣኤውን መመስከራቸው ነውና፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ ሉቃ 24፥1-8 ፤ 1ቆሮ 15፥1-ፍፃሜ
ዐብይ ፆም በነገሠባቸው ሁለት ወራት ስለጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት በተከታታይ እናቀርበው የነበረውን ትምህርታዊ ጹሑፍ በይክረም አቆይተነው ነበር፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ቀጥለን እንጽፋለን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ይላል፡፡ ክብር ሁለት ወገን ነው፡፡ አንዱ የባህርይ ሲሆን ሌላኛው የጸጋ ክብር ነው፡፡ ሮሜ 13፥7
፩.የባህርይ ክብር የጌታ እግዚአብሔር የብቻው ነው፡፡ ማንም ማን በዚህ ሊመሰል፣ሊጠራ ሊታመንና ሊመለክ አይችልም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሿሚ የሌለበት ንጉሥ፤ አክባሪ የማይሻ ክብሩ ነው፡፡ ሌላው ፍጡር ሁሉ ቢነግሥ ቢከብር ወደው ፈቅደው ወይም ተገደው ተዋርዶ ባገኛቸው ላይ ነው፡፡ ሕዝብ ከሌለ ንጉሥ ተገዢ ሳይኖርም ገዢ አይኖርም፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ግን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ንጉሥ ነው፡፡ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም” እንዲል ክቡር ዳዊት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው“ ከዓለም አስቀድሞ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር በመንግሥቱ በሦስትነቱ በአምላክነቱ ነበር” በማለት ገልጾታል፡፡
በዚህ ክብር ሊጠራ ሊመሰገን የሚችል አልነበረም አይኖርምም፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስም እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም በማለት አስጠንቅቋል፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለፈጣሪ በሚገባና በሚቀርብ ክብር ምስጋና ማክበር ተገቢ ነውን? መልሱ “ይደልዋ ” ወይም “ይገባወል” ነው!
- ዮሐ 1፥14-18….አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን…መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው ” በዚህ ቃል የእርሱ ክብር ከአባቱ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ፍፁም አንድ አንደሆነ ተረዳን፡፡ ለፍጡር እንዲህ ይባል ዘንድ ከቶም አይቻልም፡፡
- ማቴ 16፥27፡- የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና…..የሚለውም ከላይ ያለውን የሚያጠናክር ነው፡፡
- የፈጣሪ ምስጋና ለፍጡር አንደማይሠጥ የክርስትና ጽኑዕ ሕግ ነው፡፡ በራዕየ ዮሐንስ ም 5፥ 6-14 ያለው ሰማያዊ የቅዳሴ ሥርዓት ስንመለከት መንበሩን የሚሸከሙ ኪሩቤል ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ሱራፌል እልፍ አእላፋት መላእክትም በተባርዮ(እየተቀባበሉ) “…በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን!አሜን!” እያሉ ሲዘምሩ ታይተዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጡር ቢሆን በሰማያዊያን መላእክት አፍ ይህን ምስጋና ባልተቀበለም ነበር፡፡ “በጉ” የሚለው የሚወክለው እርሱን ነውና፡፡ ራሱ ጌታችን በተናገረው “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ባንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አክብረኝ” ማለቱ በቅድምና በክብር መኖሩን ያሳያል፡፡ ፍጥረት ያልነበረበት ጊዜ እንደነበርም እናውቃለንና፤ከፈጣሪ በቀር ቅደመ ፍጥረት በክብር ሊኖር የሚችል ማን ሊኖር ይችላል? ዮሐ 17፥5
- የባህርይ ክብር ወይም አንድን ነገር የባህርይ ነው ስንል ከማንም በሥጦታ ያልተቀበልው ፍቅር ሲሆን የሚጨመርለት ከፈቃድ ሲወጣ የሚቀነስበት ያይደለ ሰጭም ሆነ ነሺ የሌለበት ማለት ነው፡፡ ፍጡራን ሁሉን የተቀበሉ ከፈጣሪ ልግስና ነው፡፡ በድካም በጥረት በዋጋ ስላላገኙት “በጸጋ(በስጦታ)” ተብሎ ይገለፃል፡፡ ከፈጣሪ የተቀበልናቸው ሥጦታዎች ሁሉ በዋጋ የማይተመኑም በመሆናቸው በጸጋ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድም ጠይቀን ለምነን ያገኘናቸው ባለመሆናቸው ከልዑሉ ልግስና የተነሣ በጸጋ ያገኘናቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡
ለፍጡራን የተሠጡ ሁሉ በመታዘዝ ይጨመርላቸዋል ከፈቃድ ሲወጡ ይገፋፉታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሰው በመሆኑ ቅድመ ዓለም ከነበረው ክብር የተቀነሰ ወይም የተጨመረ ነገር የለም፡፡ በሰዎች ዘንድ ብዙ ወርደትን መቀበሉም ፈቃዱን እንጂ በባህርዩ የጎደለበት ነገር ኖሮ አይደለም፡፡
ከትንሣኤ በኋላም የኤማሁስ መንገደኞችን ሲወቅስ “ክርስቶስ መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? ነው ያላቸው፡፡አዲስ ክብር አልተቀበለም የትህትናን ሥራ ሠርቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ገባ እንጂ፡፡ ይህም ሲባል አጥቶት(ተወስዶበት) ነበር መልሶ አገኘው ማለት አይደለም፡፡ በፈቃዱ ራሱን ዝቅ ማድረጉን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ራሱን ዝቅ ማድረጉ የፈቃድ እንጂ የባህርይ አይደለምና፡፡
በተጨማሪ እኒህን ጥቅሶቸወ ተመልክተው ያገናዘቡ፡፡
ማቴ 25፥31 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፡፡
ዮሐ5፥17-18፤ ዮሐ10፥30-37፤ ዮሐ14፥8-11 ፤1ጴጥ 4፥11፤ 2ጴጥ 3፥18
- የክብር ባለቤት እንደመሆኑም በአፈ መላእክት ወሰብዕ በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች ያለ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግነዋል ለአምላክነቱም እንደሚገባ ይሰግድለታል፡፡
- ማቴ2፥11፡- የጥበብ ሰዎች በቤተልሔም በእናቱ እቅፍ ሲያገኙት እጅ መንሻ በማቅረብ ሰግደዋል፡፡
- ዮሐ9፥1-ፍፃሜ፡- ባለው ውብ ታሪክ ላይ ጌታ ዓይኑ ይበራለትን ሰው አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህ? ሲለው አምን ዘንድ እርሱ ማነው? በማለት መልሶ ጠይቆታል፡፡ ጌታም አይተኸዋል የሚያነጋግርህም እርሱ ነው ባለው ጊዜ አምናለሁ ጌታ ሆይ በማለት ሰግዶለታል፡፡
- ማቴ14፥33፡- በባህር ላይ እየተራመደ ሔዶ ወደ ታንኳዋ በገባ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሰግደውለታል፡፡
- ብዙ ዓሣ ባጠመደ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ ደሟ በቆመ ጊዜ ሴቲቱ፤ ልጁ የሞተችበት ኢያኢሮስም ለጌታችን ሰግደውለታል፡፡ ሉቃ 5፥8፤ማር 5፥33፤ ማር 5፥23
- በትንሣኤው ጊዜ የገሊላ ሴቶችና ደቀመዛሙርቱ ሰግደውታል፡፡ ማቴ 28፥9 እና 17
- ራዕ 5፥11-14፡ አየሁም በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎችም ዙርያ የበዙ መላእክትን ድምጽ ሰማሁ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፡፡ በታለቅ ድምጽም የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋና በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ፡፡በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፡፡በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ አራቱም እንስሶች አሜን አሉ፤ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ፡፡
በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ(የእግዚአብሔር በግ) በፍጡራን ሁሉ አንደበት ተመስግኗል፡፡ ሦስት ነገሮችንም እንመለከታለን፡፡
፩. ምስጋናና ክብር ይገባዋል የተባለው ከዘላለም እስከ ዘላለም ነው፡፡ መነሻና መድረሻ ጥንትና ፍፃሜ የሌለው ከዘላለም እስከ ዘላለም በምስጋና በክብር ተፈርቶ የኖረ ከርሱ በቀር የለምና፡፡
፪. ምስጋናና ክብር የቀረበለት ከባህርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ተካክሎ ነው፡፡ ከፈጣሪ ጋር ተካክሎ(ተጫፍሮ) በአንድ ምስጋናና ክብር ሊቀርብለት የሚችል ፍጡር ደግሞ ሊኖር አይችልም፡፡
፫. የመከራ የስደት የረሃብ የጥም የሞት የእስራት ፍርሃት ስጋት የሌለባቸው፤እበላ እጠግብ እሾም እሸለም ብለው የማያጎበድዱ፤የልዑሉን ፈቃድ ብቻ የሚፈፅሙ ኪሩቤል ሱራፌልና አጠቃላይ መላእክት በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም መስገዳቸው አምላክነቱን ቢያውቁ አንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ፊልጵ 2፥5-11 “…እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ…(እስከ ቁጥር 11 ይፃፍ)
የመንፈሳዊው ዓለም ነዋሪዎች መላእክት ተፈጥሯቸው ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመራባት፣በመድከም ለመዘንጋት፣ ለሀብት መጓጓት፣ ለመሞት ወዘተ…ተላልፎ ያልጠሠጠ፤ታናሹን ማዋረድ ለታለቁ ማጎብደድ የሌለባቸው ለአንዱና በጌትነቱ ብቸኛ ለሆነው አምላክ በፍፁም ኃይላቸውና በፍፀም አሳባቸው የሚገዙ የሚያገለግሉም ደገኛ ፍጥረት ናቸው፡፡
“መላእክቱ ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ” መዝ 102(03)፥20፤“መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዩቹን የእሳት ነበልባል” መዝ 90፥11፤“አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ” ትን.ዳን 6፥22 “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ…መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ…መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና“ ዘጸ 23፥20 ላይ የተጠቀሱ ሀሳቦች የመላእክት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያመላክታሉ፡፡ እርሱም ፈቃዱን ይፈፅም ዘንድ ለመዓትም ሆነ ለምህረት ይልካቸዋል፡፡ ስሙን ተሸክመው ስለሚሄዱ ባለሙሉ ሥልጣን ናቸው፡፡ ሉቃ 1፥19 የጌታን ፈቃድ ይፈፅማሉ እንጂ የረሳቸው ፈቃድ የላቸውም፡፡ለሌላም አይገዙም፡፡ ዘፀ 23፥21
ከላይ ባየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አሳቦች የእግዚአብሔር መላእክት የተባሉት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኞችና አገልጋዩች እንደሆኑም ተመዝግቧል፡፡
- ማር 1፥13፡-…መላእክቱም አገለገሉት” ፤መላእክት አላለም መላእክቱ እንጂ፡፡
- ማቴ 13፥41፡-“የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፡፡”
- ማቴ24፥30-31፡- “…የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፡፡
መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፡፡
አንዳንዶች በራዕይ 12፥7 ላይ የተመዘገበውን በመያዝ ሚካኤልና መላአክቱ ሰለሚል ከዚህ የተለየ ትርጉም አይሠጠውም ይላሉ፡፡ምክንያቱም ሚካኤልና መላእክቱ ማለቱ ቅዱስ ሚካኤልን የመላእክት ጌታ(የአምላክ) አያደርገውምና፡፡
በዚህ ምንባብ ሚካኤልና መላእክቱ የሚለው ቃል ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ መሆኑን ለማመልከት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ዳን 21፥1 ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን ሀሳቦች ዓይነተኛ በሆነ መንገድ የሚያስታርቃቸውና ልዩነታቸውን የሚያሳየን ከዚህ የሚከተለው ምንባብ ነው፡፡
- ዕብ 1፥1-ፍፃሜ፡- ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመላእክት በኩል ያለውን ልዩነት ባብራራበት መልእክቱ ከመላእክትስ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ደግሞም እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ፡- የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡
“የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም” ሲል ቅዱስ ሚካኤልንም ጨምሮ መሆኑ የተረዳ ነገር ነው፡፡ በኲር፣ የሰው ልጅ፣ በግ ወዘተ…ተብሎ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና የተገባው በእግዚአብሔር ዙፋን እስኪቀመጥ የከበረ፣ መላእክት የሰገዱለትና ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኑት ፍፁም የባህርይ አምላክ ቢሆን አይደለምን? በዚህም የመላእክት ጌታ መሆኑን አወቅን፡፡
- በራዕይ 22፥6-7፡- ላይ “…የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ፡፡ “የሚለውን በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር አስራ ስድስት ከተፃፋው ጋር ሲነፃፀር ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክት አምላክ ጌታ ፈጣሪ እንርሱም ታዛዦቹ መልእክተኞቹ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ቃሉ እንዲህ ይላል “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንደ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ፡፡”
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር