Login
Main menu

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ስድስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

እንኳን ለብርሃነ ልደቱና ጥምቀቱ አደረሳችሁ፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍትም ረድኤትም በረከት ያሳድርብን አሜን!

ባለፉት ተከታታይ ትምህርታዊ ጹሑፎች አምላክ ልንለው የምንችለው አካል ሊያሟላ ስለሚገባው ባህርያት እያየን እዚህ ደርሰናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሁሉ ሥፍራ የሚገኝ አምላክ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? የትኛውም ፍጡር በቦታ በጊዜና በሁኔታ የተወሰነ እንደሆነ የነገረ-መለኮት ሊቃውንትም ሆኑ የፍልስፍና ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ በምድራውያንም ሆነ ለሰማያውያን ግዙፉንም ይሁኑ ረቂቃን ፍጥረታት በዚሁ የታጠሩ ናቸው፡፡

ሰማያውያን መላእክት እንኳ የልዑሉን ትዕዛዝ ለመፈፀም ሲተጉ አንዱን ሥፍራ ለቀው ወዳንዱ መሔድ ግድ ይላቸዋል፡፡ እንደሪቂቅነታቸው በረቂቅ ከተማ በሦስቱ ሰማያት ኢዮር፣ ራማና ኤረር ወስኖ አስፍሯቸዋል፡፡ ተልኳቸውን ከፈፀሙ በኃላ ወደዚሁ የመላእክት ከተማ ተመልሰው በምስጋና ይተጋሉ፡፡

ለልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንደተናገረው     "ለመለኮት በታች ያለውን ለማንሳት ማጎንበስ ራስንም ማዘንበል ያለበት አይደለም በላይ ያለውን ያወርድ ዘንድ በፊትና በኋላ በቀኝና በግራ ያለውንም ለማቅረብ መዘዋወር የሚያሻው አይደለም፡፡ ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ" ቅዱስ ዳዊትም " ከመንፈስህ ወዴት እሔዳለሁ፤ ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ውቅያኖስም ጥልቅ ብወርድም በዚያ ትገኛለህ፤ እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ ከአጽናፍ አጽናፍ ብበርም እጅህ በዚያ ትመራኛለች ቀኝህም ትይዘኛለች" በማለት ስለ ልዑል እግዚአብሔር በሁሉ መገኘት ዘምሯል፡፡ መዝ139፥7-10፤ ቅዳሴ ማርያም

ቤተመቅደስን ያነፀ ሰሎሞንም በጌታ እግዚአብሔር ፊት ሲፀልይ…"ሰማያትም ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ሊይዙህ አይችሉም፡፡ እንግዲያው እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ?..."በማለት ገልጾታል፡፡ 1ነገ 8፥27

በኢሳይያስም "ሰማይ ዙፋኔ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት ለእኔ የምትሠሩልኝ ቤት እንዴት ያለ ነው? ሲል በሁሉ የመላ መሆኑን ገልጿል፡፡ ኢሳ66፡1፤ ማቴ 5፥34

በዘመኑ ፍፃሜ በመጽሐፍ ቅዱስ "በመጀመርያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበር ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለእርሱ አልሆነም" ተብሎ ልዕልናው ምልዓቱ ስፍሐቱ ከሀሊነቱ የተነገረለት አምላክ "ቃል ሥጋ ሆነ" ተብሎ ትህትናው ተገለጠ፡፡ ምልዓቱን ስፍሐቱን ሳይለቅ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ የሰውን አካልና ባህርይ በመንሳቱ በቦታ በጊዜና በሁኔታ የማይወስነው እርሱ በቦታ በጊዜና በሁኔታ ተወሰነ፡፡ ዮሐ1፥1-14

በቦታ ስንል ፤ በቤተልሔም ተወለደ፣ ወደ ግብፅ ተሰደደ፣ በናዝሬት አደገ፣ወደ ምኩራብ ገባ፣ ወደ  ኢየሩሳሌም ወጣ፣በቀራንዮ ተሰቀለ፣በጎሎጎታ ተቀበረ ወ.ዘ.ተ…ማለት ነው፡፡

በጊዜ ስንል፤ በ12 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፣ በ30ዘመን ተጠመቀ እርሱም ራሱ "ጊዜዬ ገና ነው" ብሎ እንደተናገረ የመሳሰሉትን ነው፡፡

በሁኔታዎች፤ ማለት ተፀነሰ፣ ተወለደ፣ ተሰደደ፣ ተራበ፣ተጠማ፣ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ፣ ተቀበረ ወዘተ… ማለታችን ነው፡፡

ነገር ግን ምንም እንኳ ከላይ ለተጠቀሱት ነገሮች ተገዢ ባይሆንም በፈቃዱ በእውነት በእነዚህ ስር ሆነ፡፡  ያም ሆኖ ግን ለእኛ የለበሰውን ደከማ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ኃያል አምላክነቱን ፣አላዋቂ ሥጋን የተዋሀደ ሁሉን አዋቂነቱ፣ ራሱን ባዶ በማድረጉ ውስጥ ያለ ባለጠግነቱን (ሁሉ የእርሱ ከእርሱ በእርሱ መሆኑን) በውሱንነት የተጋለጠ አለመወሰኑን ወዘተ…በሥራውና በቃሉ ገለጠለን፡፡

በማኅፀነ ማርያም ያለተከፍሎ በምልዓት እያለ ሊወሰን ከምልዓቱ አልጎደለም፡፡ በምሳሌ ፀሐይ በጠፈር ሰማይ ሆና ብርሃኗ ወደምድር ሲመጣ በፀሐይቷ ዘንድ በምልዓት አንዳለ ከእኛ ዓይን እንዲዋሃድ፤ ጨለማውን እንደሚገፍ የተሰወረውን እንደሚገልጥ የእርሱም እንዲሁ ነው፡፡ ከሦስተንቱ አልጎደለም  አራት ወደመሆንም አልተጨመረም፡፡ ይህንም በቃሉ ሲያስረግጥ…"ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም ይኸውም በሰማይ ያለ የሰው ልጅ ነው" ብሏል፡፡ ዮሐ 3፥13 ይህን በተናገረበት ቅፅበት በኒቆዲሞስ ፊት ያለ እርሱ እንደምን በሰማይ ያለ የሰው ልጅ ነው ሊል ይችላል? ምልዓቱን(በሁሉ ቦታ መገኘቱን) ለመግለፅ ካልሆነ በቀር፡፡

ለሐዋርያትና በስሙ ላመን ክርስቲያኖች ሁሉ በገባልን ቃልም እንዲህ ብሏል፡-

ማቴ18፥20 …በስሜ ሁለትና ሦስት ባላችሁበት በመካከላችሁ እሆናለሁ፡፡

ማቴ28፥19… አባቴ አንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ፡፡ ሂዱና አህዛብን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዘኳችሁንም እያስተማራችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው፡፡ እነሆ እስከዓለም ፍፃሜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡

ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስዩስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ " የመለኮቱ ሙላት በሥጋው ተገልጦ ይኖራል " እንዳለ በለበሰው ሥጋ በመለኮታዊ ሥልጣን በአባቱ ዙፋን በአባቱ ክብር ተቀምጦ ራቂቁንም ሆነ ግዙፉን ዓለም የሚታየውንም ሆነ የማይታየውን እንደሚገዛ እንዲሚጠብቅ እንደሚያስተዳድር ገልጿል፡፡ቆላ 2፥9

ዳግመኛም ሲመጣ በክበበ ትስብዕት በግርማ መለኮት ይመጣል፡፡ ይህም ማለት በክበበ ትስብዕት የተወጋ ጎኑ፣ የተቸነከሩ እጆቹ እግሮቹ እየታዩ ይመጣል፡፡ ምንም እንኳ በክበበ ትስብዕት ቢሆንም እነደ አምላክነቱ ሁሉ እኩል ያየዋል፡፡ በኋላ በቀኝ በግራ የሚሆን የለም አንዱ ቀርቦ አንዱ ርቆ አንዱ ከጀርባ አንዱ ከጎን ሆኖ አያያውም፡፡ ለሁሉ በእኩል ከፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል አንጂ፡፡ ምን የአዳም ዘር በዝቶ እንደ እንድጽፍቀተ ሮማን ቢጨናነቅ ሁሉ በእኩል ርቀት በአንድ ዓይነት በፊቱ ያየዋል፡፡ ይህም ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ ውሱን ሲሆን ምሉዕ አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር ያሳያል፡፡

ልዑል ሲሆን ሳለ ትሁት ሆኖ ራሱን በምንችለው መጠን የገለፀልን፤ ይወዳጀን ዘንድም ፍቃዱ የሆነ ጌትነቱን ፈጣሪነቱን የባህርይ አማላክነቱን አምነን እንመስክር ዘንድ የመረጠን የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ አዳኝ ርኅሩኅ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ክብር ምስጋና ይግባው፡፡

ለዘለዓለሙ አሜን!

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ስምንት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በሚል ቃለ ብሥራት ሰላምታችንን እያስቀደምንና በትንሣኤው ትንሣኤያችንን እያወጅን ሰነበትን፡፡ “በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፈንታ ደስ ይለናል፡፡” እንዳለ ነቢዩ ዳዊት ፍርድህን ከሰማንበት ቃልህ፤ ምህረትህን ፣ ይቅርታህን ፤በሞት አዋጆች ፈንታ ትንሣኤና ሕይወትን፤ከባርነት ተላቀን ነፃነትን በመቀዳጀታችን የመከራውን ዘመን አስረስተህ ደስታን ሞላኸን፡፡ ከዛሬ ፪ሺ ዓመት ገደማ የበዛልን ሥጦታህ ከአበው ወደ ውሉድ እየተላለፈ ደስታው ሳይፈዝ ስሜቱ ሳይደበዝዝ “ግበሩ በዓለ በትፍስህት” እንዲል ዛሬም እንደያኔው አከበርነው፡፡ ሰውነታችን በፆም እንዳከበረችህ በመብልም አመሰገነችህ፡፡ በድካማችን፣በትካዜያችን፣በረሃብና በጥማችን፣ በሀዘንና በዕንባችን ወራትም ትዝታችን አንተ ነበርህ፤ በደስታና በሐሤት በመብልና በመጠጥ ወራትም የአንደበታችን ቅኔ የዝማሬያችን ጉልበት አንተው ነህ፡፡

በምሴት ይደምፅ ብካይ ወበጽባህ ፍስሐ” እንዳለ ክቡር ዳዊት በጨለማ ኦሪት፣ በጨለማ ኃጢአት በጨለማ ሞትና ሲዖል በተያዝንበት ወራት አለቀስን፤ የወንጌል ብርሃን፣ የትንሣኤ ብርሃን፣ የጽድቅ ፀሐይ በወጣበት ዘመን ሐሤት እናደርጋለን፡፡ የፊትህን ብርሃን አይተናልና ቀኑን ሁሉ ደስ ይለናል፡፡ ይኸውም በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያገኘነው ዘላለማዊ ይቅርታህ ነው፡፡

ከላይ ያልነውን ሁሉ ያልነው ስለ ዐብይ ፆም ሰንበታትና ስለ ጌታችን ስቅለት ትንሽ ጽፈን ስለነበር ምነው ትንሣኤውስ? ላለመባል ነው፡፡ ትንሣኤ ካልታወጀ ካልተሰበከ ክርስትና ተብሎ ነገር የለምና፡፡ ትንሥኤውንም የማያምንና የማይሠብክ ሰውም ከመላእክት አንድነት ሊጨመር ከነቢያትና ከሐዋርያት ከጻድቃንና ከሰማዕታት ኅብረትም አንድ ሊሆን አይቻለውም፡፡ የኒህ ሁሉ መከራቸው በትንሣኤው ማመናቸው ክብራቸው ትንሣኤውን መመስከራቸው ነውና፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ ሉቃ 241-8 1ቆሮ 151-ፍፃሜ

ዐብይ ፆም በነገሠባቸው ሁለት ወራት ስለጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት በተከታታይ እናቀርበው የነበረውን ትምህርታዊ ጹሑፍ በይክረም አቆይተነው ነበር፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ቀጥለን እንጽፋለን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ይላል፡፡ ክብር ሁለት ወገን ነው፡፡ አንዱ የባህርይ ሲሆን ሌላኛው የጸጋ ክብር ነው፡፡ ሮሜ 137

.የባህርይ ክብር የጌታ እግዚአብሔር የብቻው ነው፡፡ ማንም ማን በዚህ ሊመሰል፣ሊጠራ ሊታመንና ሊመለክ አይችልም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሿሚ የሌለበት ንጉሥ፤ አክባሪ የማይሻ ክብሩ ነው፡፡ ሌላው ፍጡር ሁሉ ቢነግሥ ቢከብር ወደው ፈቅደው ወይም ተገደው ተዋርዶ ባገኛቸው ላይ ነው፡፡ ሕዝብ ከሌለ ንጉሥ ተገዢ ሳይኖርም ገዢ አይኖርም፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ግን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ንጉሥ ነው፡፡ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም” እንዲል ክቡር ዳዊት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው“ ከዓለም አስቀድሞ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር በመንግሥቱ በሦስትነቱ በአምላክነቱ ነበር” በማለት ገልጾታል፡፡

በዚህ ክብር ሊጠራ ሊመሰገን የሚችል አልነበረም አይኖርምም፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስም እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም በማለት አስጠንቅቋል፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለፈጣሪ በሚገባና በሚቀርብ ክብር ምስጋና ማክበር ተገቢ ነውን? መልሱ “ይደልዋ ” ወይም “ይገባወል” ነው!

- ዮሐ 114-18….አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን…መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው ” በዚህ ቃል የእርሱ ክብር ከአባቱ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ፍፁም አንድ አንደሆነ ተረዳን፡፡ ለፍጡር እንዲህ ይባል ዘንድ ከቶም አይቻልም፡፡

- ማቴ 1627- የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና…..የሚለውም ከላይ ያለውን የሚያጠናክር ነው፡፡

- የፈጣሪ ምስጋና ለፍጡር አንደማይሠጥ የክርስትና ጽኑዕ ሕግ ነው፡፡ በራዕየ ዮሐንስ ም 56-14 ያለው ሰማያዊ የቅዳሴ ሥርዓት ስንመለከት መንበሩን የሚሸከሙ ኪሩቤል ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ሱራፌል እልፍ አእላፋት መላእክትም በተባርዮ(እየተቀባበሉ) “…በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን!አሜን!” እያሉ ሲዘምሩ ታይተዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጡር ቢሆን በሰማያዊያን መላእክት አፍ ይህን ምስጋና ባልተቀበለም ነበር፡፡ “በጉ” የሚለው የሚወክለው እርሱን ነውና፡፡ ራሱ ጌታችን በተናገረው “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ባንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አክብረኝ” ማለቱ በቅድምና በክብር መኖሩን ያሳያል፡፡ ፍጥረት ያልነበረበት ጊዜ እንደነበርም እናውቃለንና፤ከፈጣሪ በቀር ቅደመ ፍጥረት በክብር ሊኖር የሚችል ማን ሊኖር ይችላል? ዮሐ 175

- የባህርይ ክብር ወይም አንድን ነገር የባህርይ ነው ስንል ከማንም በሥጦታ ያልተቀበልው ፍቅር ሲሆን የሚጨመርለት ከፈቃድ ሲወጣ የሚቀነስበት ያይደለ ሰጭም ሆነ ነሺ የሌለበት ማለት ነው፡፡ ፍጡራን ሁሉን የተቀበሉ ከፈጣሪ ልግስና ነው፡፡ በድካም በጥረት በዋጋ ስላላገኙት “በጸጋ(በስጦታ)” ተብሎ ይገለፃል፡፡ ከፈጣሪ የተቀበልናቸው ሥጦታዎች ሁሉ በዋጋ የማይተመኑም በመሆናቸው በጸጋ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድም ጠይቀን ለምነን ያገኘናቸው ባለመሆናቸው ከልዑሉ ልግስና የተነሣ በጸጋ ያገኘናቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡

ለፍጡራን የተሠጡ ሁሉ በመታዘዝ ይጨመርላቸዋል ከፈቃድ ሲወጡ ይገፋፉታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሰው በመሆኑ ቅድመ ዓለም ከነበረው ክብር የተቀነሰ ወይም የተጨመረ ነገር የለም፡፡ በሰዎች ዘንድ ብዙ ወርደትን መቀበሉም ፈቃዱን እንጂ በባህርዩ የጎደለበት ነገር ኖሮ አይደለም፡፡

ከትንሣኤ በኋላም የኤማሁስ መንገደኞችን ሲወቅስ “ክርስቶስ መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? ነው ያላቸው፡፡አዲስ ክብር አልተቀበለም የትህትናን ሥራ ሠርቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ገባ እንጂ፡፡ ይህም ሲባል አጥቶት(ተወስዶበት) ነበር መልሶ አገኘው ማለት አይደለም፡፡ በፈቃዱ ራሱን ዝቅ ማድረጉን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ራሱን ዝቅ ማድረጉ የፈቃድ እንጂ የባህርይ አይደለምና፡፡

በተጨማሪ እኒህን ጥቅሶቸወ ተመልክተው ያገናዘቡ፡፡

ማቴ 2531 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፡፡

ዮሐ517-18፤ ዮሐ1030-37፤ ዮሐ148-11 1ጴጥ 4112ጴጥ 318

- የክብር ባለቤት እንደመሆኑም በአፈ መላእክት ወሰብዕ በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች ያለ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግነዋል ለአምላክነቱም እንደሚገባ ይሰግድለታል፡፡

- ማቴ211- የጥበብ ሰዎች በቤተልሔም በእናቱ እቅፍ ሲያገኙት እጅ መንሻ በማቅረብ ሰግደዋል፡፡

- ዮሐ91-ፍፃሜ፡- ባለው ውብ ታሪክ ላይ ጌታ ዓይኑ ይበራለትን ሰው አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህ? ሲለው አምን ዘንድ እርሱ ማነው? በማለት መልሶ ጠይቆታል፡፡ ጌታም አይተኸዋል የሚያነጋግርህም እርሱ ነው ባለው ጊዜ አምናለሁ ጌታ ሆይ በማለት ሰግዶለታል፡፡

- ማቴ1433- በባህር ላይ እየተራመደ ሔዶ ወደ ታንኳዋ በገባ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሰግደውለታል፡፡

- ብዙ ዓሣ ባጠመደ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ ደሟ በቆመ ጊዜ ሴቲቱ፤ ልጁ የሞተችበት ኢያኢሮስም ለጌታችን ሰግደውለታል፡፡ ሉቃ 58፤ማር 533፤ ማር 523

- በትንሣኤው ጊዜ የገሊላ ሴቶችና ደቀመዛሙርቱ ሰግደውታል፡፡ ማቴ 289 እና 17

- ራዕ 511-14፡ አየሁም በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎችም ዙርያ የበዙ መላእክትን ድምጽ ሰማሁ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፡፡ በታለቅ ድምጽም የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋና በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ፡፡በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፡፡በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ አራቱም እንስሶች አሜን አሉ፤ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ፡፡

በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ(የእግዚአብሔር በግ) በፍጡራን ሁሉ አንደበት ተመስግኗል፡፡ ሦስት ነገሮችንም እንመለከታለን፡፡

. ምስጋናና ክብር ይገባዋል የተባለው ከዘላለም እስከ ዘላለም ነው፡፡ መነሻና መድረሻ ጥንትና ፍፃሜ የሌለው ከዘላለም እስከ ዘላለም በምስጋና በክብር ተፈርቶ የኖረ ከርሱ በቀር የለምና፡፡

. ምስጋናና ክብር የቀረበለት ከባህርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ተካክሎ ነው፡፡ ከፈጣሪ ጋር ተካክሎ(ተጫፍሮ) በአንድ ምስጋናና ክብር ሊቀርብለት የሚችል ፍጡር ደግሞ ሊኖር አይችልም፡፡

. የመከራ የስደት የረሃብ የጥም የሞት የእስራት ፍርሃት ስጋት የሌለባቸው፤እበላ እጠግብ እሾም እሸለም ብለው የማያጎበድዱ፤የልዑሉን ፈቃድ ብቻ የሚፈፅሙ ኪሩቤል ሱራፌልና አጠቃላይ መላእክት በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም መስገዳቸው አምላክነቱን ቢያውቁ አንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ፊልጵ 25-11 “…እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ…(እስከ ቁጥር 11 ይፃፍ)



የመንፈሳዊው ዓለም ነዋሪዎች መላእክት ተፈጥሯቸው ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመራባት፣በመድከም ለመዘንጋት፣ ለሀብት መጓጓት፣ ለመሞት ወዘተ…ተላልፎ ያልጠሠጠ፤ታናሹን ማዋረድ ለታለቁ ማጎብደድ የሌለባቸው ለአንዱና በጌትነቱ ብቸኛ ለሆነው አምላክ በፍፁም ኃይላቸውና በፍፀም አሳባቸው የሚገዙ የሚያገለግሉም ደገኛ ፍጥረት ናቸው፡፡

መላእክቱ ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ” መዝ 102(03)20፤“መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዩቹን የእሳት ነበልባል” መዝ 9011፤“አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ” ትን.ዳን 622 “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ…መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ…መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና“ ዘጸ 2320 ላይ የተጠቀሱ ሀሳቦች የመላእክት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያመላክታሉ፡፡ እርሱም ፈቃዱን ይፈፅም ዘንድ ለመዓትም ሆነ ለምህረት ይልካቸዋል፡፡ ስሙን ተሸክመው ስለሚሄዱ ባለሙሉ ሥልጣን ናቸው፡፡ ሉቃ 119 የጌታን ፈቃድ ይፈፅማሉ እንጂ የረሳቸው ፈቃድ የላቸውም፡፡ለሌላም አይገዙም፡፡ ዘፀ 2321

ከላይ ባየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አሳቦች የእግዚአብሔር መላእክት የተባሉት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኞችና አገልጋዩች እንደሆኑም ተመዝግቧል፡፡

- ማር 113-…መላእክቱም አገለገሉት” ፤መላእክት አላለም መላእክቱ እንጂ፡፡

- ማቴ 1341-“የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፡፡”

- ማቴ2430-31- “…የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፡፡

መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፡፡

አንዳንዶች በራዕይ 127 ላይ የተመዘገበውን በመያዝ ሚካኤልና መላአክቱ ሰለሚል ከዚህ የተለየ ትርጉም አይሠጠውም ይላሉ፡፡ምክንያቱም ሚካኤልና መላእክቱ ማለቱ ቅዱስ ሚካኤልን የመላእክት ጌታ(የአምላክ) አያደርገውምና፡፡

በዚህ ምንባብ ሚካኤልና መላእክቱ የሚለው ቃል ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ መሆኑን ለማመልከት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ዳን 211 ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን ሀሳቦች ዓይነተኛ በሆነ መንገድ የሚያስታርቃቸውና ልዩነታቸውን የሚያሳየን ከዚህ የሚከተለው ምንባብ ነው፡፡

- ዕብ 11-ፍፃሜ፡- ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመላእክት በኩል ያለውን ልዩነት ባብራራበት መልእክቱ ከመላእክትስ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ደግሞም እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ፡- የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡

የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም” ሲል ቅዱስ ሚካኤልንም ጨምሮ መሆኑ የተረዳ ነገር ነው፡፡ በኲር፣ የሰው ልጅ፣ በግ ወዘተ…ተብሎ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና የተገባው በእግዚአብሔር ዙፋን እስኪቀመጥ የከበረ፣ መላእክት የሰገዱለትና ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኑት ፍፁም የባህርይ አምላክ ቢሆን አይደለምን? በዚህም የመላእክት ጌታ መሆኑን አወቅን፡፡

- ራዕይ 226-7- ላይ “…የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ፡፡ “የሚለውን በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር አስራ ስድስት ከተፃፋው ጋር ሲነፃፀር ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክት አምላክ ጌታ ፈጣሪ እንርሱም ታዛዦቹ መልእክተኞቹ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ቃሉ እንዲህ ይላል “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንደ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ፡፡”

ይቆየን!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ሰባት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

መግቢያ፡ በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

ሌላው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነቱን ከገለፀባቸው ባህርያት አንዱ ኃጢአትን የማስተሰረይ(ይቅር የማለት) ሥልጣኑ ነው፡፡

በመጽሐፍ እንደተፃፈ ኃጢአትን ማስተሰረይ ብቸኛ የቅዱስ እግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡ በማር.ወን 25- ላይ ሽባውን ሰው እንዲፈውስላቸው በአልጋ አድርገውና የቤቱን ክዳን ነቅለው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሲያቀርቡት አንተ ሰው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ነበር ያለው፡፡ በዚያ የነበሩ አይሁድም "ይህ ሰው በርግጥ ይሳደባል ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ማን ይችላል?" በማለት ሲያጉረመርሙ ጌታችን ግን "የሰው ልጅ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንዲያውቁ አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ሽባውንም ፈውሶታል፡፡ እዚህ ላይ"የሰው ልጅ" እያለ ጌታ የሚጠራው ራሱን እንደሆነ አስተውል፡፡

ኃጢአት የሚሠራ ሰው በዋናነት የሚበድለው ቅዱስ እግዚአብሔርን ነው፡፡ ምክንያቱም፡

1. ሕጉን ይተላለፋል አድርግ የተባለውን ሲያስቀር አታድርግ የተባለውንም ሲያደርግ የአግዚአብሔርን ሕግ ማቃለሉ አይደለምን?፡፡ ለልዑል እግዚአብሔር ፍቅርና ክብር እንዳለን የሚታወቅበት ብቸኛ መንገድ በቃሉ(በሕጉ) ታዛዥ ሆነን መገኘት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ዓመፀኞች ነን፤ ዓመፃ ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአትንም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር አልተወለደም፤እግዚአብሔርንም አያውቀውም፡፡ 1ዮሐ 2

2. እግዚአብሔርን የሚበድለው የፈጠረውን ፍጥረት በማሳዘኑ ነው፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር የፍጡራኑ በደልና ሥቃይ የሚሰማው አምላክ ነው፡፡ ገዢያችን አባታችን ነውና፡፡ የግዛቱ መደፈርና የህዝቡ በጦርም ሆነ በምርኮ መንገላታት ንጉስን ከዙፋኑ አውርዶ ከቤተመንግስቱ አስወጥቶ ጦርነት እንደሚያስከትተው፤የሚስቱ የልጆቹ መጠቃት የአባትን ቁጣ ቀስቅሶ ለበቀል አንደሚያነሣሣው ለልዑል እግዚአብሔርም የፍጡራኑ መበደል አንዲሁ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ከአካላችን አንዱ ብልት ላይ የሚደርስ አደጋ ህማሙ ነፍሳችን እንደሚሠማት ለጌታ እግዚአብሔርም በፍጡራኑ ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲሁ ነው፡፡

በመሆኑም ሰው ኃጢአት ሠርቶ ባልንጀራውን ቢበድል ይቅርታን ማግኘት ያለበት ከተበዳዩ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ምሳሌ፡- አንድ ሰው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ብላቴናን በግዳጅ ቢደርስባት ጥቃቱ(በደሉ) የእርሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማኅበረሰቡና የመንግስት ጭምር ነው፡፡ ምንም እንኳ በዳዩ ሽማግሌ ልኮ ካሣ ከፍሎ ከተበዳይዋም ሆነ ከቤተሰቧ ይቅርታን ቢያገኝ የሀገሪቱን ሕግ በመተላለፉና በአንዲት ንፁህ ዜጋ ላይ ወንጀል በመፈፀሙ በመንግስት ሕግ ከመጠየቅ አይድንም፡፡ ማኅበረሰቡም ይህ ሰው ነገ ሊያደርሰው የሚችለው ተመሳሳይ በደል ሊታረም የሚችልበትን መንገድ ከመጠየቅ ችላ አይልም፡፡ ስለዚህ ያ ሰው ፍፁም ይቅርታን አግኝቻለሁ ብሎ በሰላም መኖር የሚችለው ከግል ተበዳይዋ፣ ከቤተሰቧ፣ ከማኅበረሰቡና ከመንግስት ይቅርታ ሲደረግለት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለምም ይኸው ነው፡፡ ሰው የግል ተበዳይን ብቻ ሳይሆን ቅዱስ እግዚአብሔርን ፍፁም ይቅርታ በሚጠይቅ ሰዓት ስርየትን ያገኛል፡፡ የአባቱን ሀብት ያባከነው ወጣት ወደቤቱ ሲመለስ ለአባቱ "በሰማይና በምድር ፊት በድያለሁ" ያለው ለዚህ ነው፡፡ በምድር ወላጅ አባቱን በሰማይ ያለ ፈጣሪውን በድሏልና፡፡ሉቃ 15

ስለዚህ በዚህ አግባብ ፍፁም የኃጢአት ይቅርታን ሊሠጥ የሚችል ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዳዊት " ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ አጥንቶቼ ሁሉ የተቀደሰ ስሙን ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል ከደዌሽ ሁሉ የሚፈውስሽ…"

በማለት የይቅር ባይነት ሥልጣን የቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን ይገልፃል፡፡ ጨምሮም…ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ" እንዲሁም "አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ አቤቱ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና" በማለት ያስረግጣል፡፡መዝ 311-5፣ መዝ1021-14፣መዝ 129(130)3

ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን የጌታ እግዚአብሔር መሆኑ ከታወቀ ኢየሱስ ክርስቶስ "ኃጢአትህ() ተሰረየችልህ()" ማለቱ እርሱ አምላክ(እግዚአብሔር) ለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡

ሉቃ748- ሽቱ የቀባችውን ሴት በቃሉ "ኃጢአትሽ ተሰረዮልሻል በሰላም ሂጂ" ብሎ ሲያሰናብታት በዚያ የነበሩ "ኃጢአትን ስንኳ የሚያስተሠርይ ይህ ማነው? እስከማለት ተገርመዋል፡፡

ሉቃ2343- በመስቀል ላይ ሳለ በቀኙ የተሰቀለ ወንበዴ በሰማይና በምደር የተፈፀሙ ተዓምራቶችን አይቶ "በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" ብሎ ላቀረበው የይቅርታ ልመና" ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ" በማለት የይቅርታ ባለቤት መሆኑን አሳይቷል፡፡

ሉቃ2446-"ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤በስሙም ንስሐና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአህዛብ ሁሉ ይሰበካል"፡፡ ልናስተውል የሚገባን በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በዓለም ሃይማኖቶች ታሪክ ንስሐና የኃጢአት ሥርየት በስሙ የሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በቡድሐም፣ ሆነ በክሪሽና በዘራስተርም ሆነ በመሐመድ የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም በቀደምት አበው ሆነ በነቢያት፣ በነገስታት ከጌታም በኋላ በተነሱ በሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ስም የኃጢአት ሥርየት አልተሰበከም፡፡ ሁሉ በእርሱ ከኃጢአት ነፁ ለዚሁም ምስክር ሆኑ እንጂ፡፡

የሐዋ.ሥራ 237-38- ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ጰራቅሊጦስ የሰበከውን የሰሙ ልባቸው የተነካ ሰዎች ምን እናድርግ ? ብለው በጠየቁ ሰዓት የተሰጣቸው መልስ "ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" የሚል ነው፡፡

1ዮሐ11-10- ያየነውን እንመሠክራለን ያለ ዩሐንስ ወንጌላዊ "ኃጢአት የለብንም ብንል ውሸተኞች ነን … የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል…በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነ ጻድቅ ነው፡፡" በማለት የኃጢአትን ይቅርታ እንዴት እንደሆነ ጽፎልናል፡፡

ኃጢአትን ይቅር የሚል በደልን የሚደመስስ ለሚወዱትም መንግሥቱን የሚያወርስ ጌትነቱ በሁሉ ላይ የሆነ በመጨረሻው ዘመን ግን የባርያን መልክ ይዞ የተገለጠ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ስለ ኀጢአታችን ብዙ ልንፆም፣ በፀፀት ልናለቅስ፣ በርካታ ምፅዋት ልንሠጥና በድካም እስክንዝል ልንሰግድ እንችላለን ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ይቅርታውን ደጅ የምንጠናበት መንገድ እንጂ በራሱ ፍፁም ሆኖ ይቅርታን የሚያስገኝ አይደለም፡፡ ይቅርታን ለማግኘት ለኃጢአታችን መስዋዕት ሆኖ የቀረበ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን ልንበላ ክቡር ደሙንም ልንጠጣ የግድ ያስፈልገናል፡፡

መጽሐፍ "ያለ ደም ሥርየት የለም" እንዲል ጌታም በቃሉ "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም"፡፡ እንዲል ዕብ፣ዮሐ 653

ጸሎት- ቅዱስ አምላክ ሆይ አናመስግንሀለን፡፡ ከቸርነትህ ገናናነት የተነሣ ሥጋህንና ክቡር ደምህን ለህይወት ለመድኃኒት እንዲሆነኝ ሰጥተኸኛል፡፡ ይህም በሕይወት ዘመኔ የተቀበልኩት በዋጋ የማይተመን እኔን የመውደደህ ስጦታ ነው፡፡ ቸር ሰውን ወዳጅ ሆይ ወደ ሕይወት መድኃኒት እንዳልቀርብ ዲያብሎስ በብዙ የምክኒያት ሰንሰለቶች አስሮኛልና ፍታኝ፡፡ ምክንያትን ቆርጬ የምጥልበትን ኃይል አድለኝ፡፡ በእኔም ዘንድ መኖርያህን ታደርግ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን!አሜን!

አቡነ ዘበሰማያት



ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

 



Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል አምስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን የሚያውቅ የባህርይ አምላክ ስለመሆኑ፤

መግቢያ፡- ባለፉት ሳምንታት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሁሉን ቻይ" አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ በዛሬው ጹሑፋችን አምላካዊ ባህርያት ከሆኑት አንዱን "ሁሉን ማወቅ" ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በማስደገፍ እናያለን፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩን ይግለጽልን!

ሁሉን ማወቅ የእግዚአብሔር የብቻው /የተለየ/ ባህርዩ ነው፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በውቅያኖስ፣በብርሃንም ሆነ በጨለማ ፣ በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም እርሱ የማያውቀው ከእርሱ ተሰውሮ የሚፈጸም አንዳች ስንኳ የለም፡፡ ሁሉንም ከመሆኑ በፊት እንደተደረገ አድርጎ ያውቀዋል፡፡ በጸሎተ ኪዳን እንተፃፈ " እምቅድመ ህሊና ኲሎ የአምር፣ ወእምቅድመ ህሊና ይፈትን" ከህሊና አስቀድሞ ያውቃል፣ ከሀሳብም ቀድሞ ይመረምራል፡፡ ዓለምን ጅማሬው ላይ ሆኖ ፍፃሜውን ያውቀዋል፡፡ በአጭር ቃል ከእርሱ ምንም ምን አይሠወርም የክፍዎችንም ሆነ የበጎዎችን ምክር ያውቃል፣ የጠቢባንንም አሳባቸውን ይመረምራል፡፡ ከመሆኑ አስቀድሞ እንጂ ከተደረገ በኋላ ተመራምሮ በነገሩ የሚደርስ አይደለም፡፡ በመሆኑም አኛንም ማንም ከሚያውቀን ይልቅ ከራሳችንም በላይ ያውቀናል በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሏል፡፡

1ሳሙ 2፥3 " አትታበዩ በኩራትም አትናገሩ፡ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና…"

1ኛ ዮሐ 3፥20 " እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል"

ይህ እንዲህ ከሆነ "ሁሉን አዋቂነት" የሚለው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀፀል ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምላሽ "በትክክል" የሚል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እነሆ፡፡

ማቴ9፥1-8 ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ ባመጡ ጊዜ ሽባውን"አንተ ልጅ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ" አለው፡፡ ከጻፎች ግን አንዳንዶቹ በልባቸው ይህስ ይሳደባል አሉ፡፡ ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?...

ማቴ 12፥15 ጌታችን በሰንበት ስለፈወሰ ፈሪሳውያን ሊገድሉት ሲማከሩ ምክራቸውን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ ይላል፡፡

ማቴ 12፥22-27 ሕዝቡ በአጋንንት ላይ ባለው ሥልጣን ሲደነቁ ፈሪሳውያን ግን በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል በማለት ሲያስቡ ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው እርስ በርሷ የምትለያይ መንግስት አትፀናም…

ማቴ 17፥24-27 ቀረጥ ሰብሳቢዎች ጰጥሮስን በውጭ አግኝተው መምህራችሁ ግብር አይገብርምን? ብለው ሰለጠየቁት ጴጥሮስ ይህን ሊናገር ወደ ቤት ሲገባ አስቀድሞ የሆነውን አውቆ ዓሣ አጥምዶ ያገኘውን እንዲከፍል ነግሮታል፡፡

ሉቃ 5፥1-11 ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሊቱን ደክሞ ያልሆነለትን በጌታችን ትዕዛዝ ብዙ ዓሣ በመያዙ ቢደሰትም በታላቅ ፍርሃት ጌታን "እኔ ኃጥአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ" ብሎታል፡፡ መተርጉማን ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል ሲፈቱት የባህሩን ውስጥ እንዲህ ያወቀው የእኔንማ ልብ እንዴት ይመረምረው ብሎ እንደፈራ ያትታሉ፡፡

ሉቃ 7፥36-50 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስምዖን ፈሪሳዊ ቤት ለምሳ በተቀመጠበት ወቅት ባለ ሽቶዋ ማርያም እግሩን እየሳመች በእንባዋ እያጠበችና በፀጉርዋ እያበሰች ሽቶ ቀብታ ሰለኃጢአቷ ሥርየት በአርምሞ ስትማፀ ስምዖን ፈሪሳዊ አይቶ ይህስ ነብይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ባወቀ ነበር ኃጥአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ለዚህ ሰው የልቡን አውቆ  ምን ዓይነት አስደናቂ መልስ እንደሰጠው ቃሉን አንብብ፡፡

ሉቃ 8፥43-48 12 ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት የነበረች ሴት ጌታን ህዝቡ እያገፋው ሳለ ተሰውራ የቀሚሱን ዘርፍ በመንካቷ ተፈወሰች ጌታም ማን ነው የነካኝ ብሎ ሲጠይቅ ሐዋርያት ህዝቡ ይገፉሃል ማነው የነካኝ ትላለህን? ሲሉት አንድ ሰው ዳሶኛል ኃይል ከእኔ እንደወጣ እኔ አውቃለሁና ብሎ ነው የመለሰው ሴቲቱም እንዳልተሠወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች የተደረገላትንም በህዝቡ ሁሉ ፊት መሠከረች፡፡

ሉቃ 22፥31-34 ጌታችን እንደሚያዝና ሁሉም ጥለውት እንደሚሸሹ በተናገረበት ምሴተ ሐሙስ ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎች ቢክዱህ እኔ አልክድህም ብሎ ለሠጠው የትምክህት መልስ" ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ቀድሞ ነግሮታል፣ ይኸውም እንደቃሉ ተፈፅሟል፡፡

ዮሐ2፥5 " ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፡፡ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡

ዮሐ 1፥47-50 ፊልጶስ ናትናኤልን ጋብዞ ወደ ጌታችን ባመጣው ሰዓት ጌታ "በልቡ ተንኮል የሌለበት የእስራኤል ስው እነሆ" በማለቱ ናትናኤል ከወዴት ታውቀኛለህ? ቢለው ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች አየሁህ የሚል መልስ ሲሰጠው" መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ" በማለት እርሱ ሁሉን አዋቂ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን መስክሯል፡፡

ዮሐ4፥1-መጨረሻ  በተፃፈው ፍፁም የሚመስጥ ታሪክ ሳምራዊቷ ሴት ለሀገሯ ሰዎች ከጌታችን ጋር ስለነበራት ቆይታ ስትገልፅላቸው ወደ እርሱ እንዲመጡም ስትጋብዛቸው "ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ…" ብላለች ቁጥር 29

ዮሐ6፥15 እንጀራ በልተው ሲጠግቡ እርስ በርሳቸው ከሆነስ አይቀር ስንራብ እያበላ ፣ስንጠማ እያጠጣ፣ስንታመም እየፈወሰ፣ስንሞት እያሰናዳ ቢገዛን መልካም በሆነ ኑ እናንግሠው ብለው ያሰቡትን አውቆ ከአጠገባቸው ፈቀቅ ብሎ ወደ ተራታ ወጣ ይላል፡፡

ዮሐ11፥1-መጨረሻ ፡- በቦታው በአካል ባይገኝም ስለአልዓዛር መታመምና መሞት ቀድሞ ለሐዋርያት ነግሯቸዋል፡፡

v  ጌታችን ስለሞቱና ትንሣኤው አስቀድሞ ተናግሯል፡፡

ማቴ 24፥1-መጨረሻ፡- የዓለም መጨረሻና የዳግም ምፅዓቱ ምልክቶችን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡        ዮሐ16፥29-30 ሐዋርያት"እነሆ አሁን በግልጥ ትናገራለህ፣በምሳሌም ምንም አትናገርም ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፡፡

ዮሐ21፥15-17 በጥብርያዶስ ባህር ዳርቻ ጌታችን ከስምዖን ጴጥሮስ ጋር በነበረው ቆይታ "ትወደኛለህን?" ብሎ ሦስት ጊዜ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው የመጨረሻ ምላሽ "ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ " የሚል ነው፡ በዚህም ሁሉን አዋቂ መሆኑን አስረግጦ መስክሯል፡፡ በመቀጠል ጌታችንም ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሣር ዘመን በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔር ያከብር ዘንድ እንዳለው ነግሮታል ይህም ሁሉን አወቂ መሆኑን ያስረገጠበት መንገድ ነው፡፡

ራስን መመዘኛ /መመርመርያ/ ጥያቄ!

 

.የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አዋቂነቱ በእኔ ሕይወት ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

ለ. በእርግጥ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ መሆኑን በእውነት አምናለሁ?

. እግዚአብሔር ከሁሉን አዋቂነቱ ወሰን ተሠውሬ ኃጢአት ሠርቼ አውቃለሁን?

መ. ቅዱስ እግዚአብሔር / ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ / ከልቤ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያህል ነው? እንዴትስ እረዳዋለሁ?

 

v  በሀገር ውስጥ ላላችሁ ለጥያቄዎቹ መልስና ሀሳባችሁን በሪፖርት(በወረቀት) በጉባኤ ቀን ትሰጣላችሁ፡፡

ይቆየን!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ዓራት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

       በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

መግቢያ

        የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይነቱ በሞት ላይ በነበረው ሥልጣንም ገልጿል፡፡ ሞት የኃጢአት ውጤት(ደመወዝ) ነው፡፡ ለሞት ያልተገዛ ፍጥረትም የለም፡፡ ከአዳም ጀምሮ የአዳማዊው ተፈጥሮ ተጋሪ የሆኑ ልጆቹና ለአዳም የተፈጠሩት ፍጥረቶች ሁሉ በሞት ጥላ ሥር ወድቀዋል፡፡ ርዕሳነ አበው፣ነብያት፣ነገሥታት፣ካህናት፣ሁሉ በሞት መዳፍ ተያዙ ማምለጥም የታቻለው ወይም ይህን የሞት ፍርድ ሊያስቀር የቻለ አንድ ስንኳ አልተገኘም፡፡

ይህንኑ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ 5፥12-21 በጥሩ ሁኔታ አብራርቶታል፡፡ "…ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት… ነገር ግነ በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ…" ጨምሮም "…የኋላኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና፡፡ነገር ግን ሁሉ ተገዝቶአል ሲል ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው" ፡፡ 1 ቆሮ 15፥25-28 በማለት የሞትን ሥልጣንና የሞትን ሥልጣን ሰብሮ ኃያልነቱን(ሁሉን ቻይነቱን) የገለፀውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ ግልፅ አድርጓል፡፡

      አበው ለብዙ ዘመናት ከዚህ የሞት ባርነት ነፃ ሊያወጣቸው ወደሚችል በብዙ ልመና ሲቃትቱ ኖረዋል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ሞትን ሻረው፡፡ ሞት ነግሦባት በነበረች ምድር ለመጀመርያ ጊዜ " እሰቀላለሁ፣ እሞታለሁ በሦስተኛውም ቀን እነሳለሁ" እንዲሁም " ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ በፍቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፤ይህቺን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ፡፡" በማለት ሞትን ያስደነገጠ የአዳምን ተስፋ ያረጋገጠ አዋጅ ተሰማ፡፡ ዮሐ 10፥18፣ ማቴ 16፥21

     መግደልና ማዳን የእግዚአብሔር ብቻ ሥልጣን መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ ነው፡፡ ኦሪ.ዘዳ 32፥39፣ 1ሳሙ 2፥6፣ ማቴ 10፥28-31 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን "ነፍሴን ላኖራትም ላነሣትም ሥልጣን አለኝ" በማለት በሞት ላይ ያለውን ገዢነቱን በተጨማሪም የመግደልና የማዳን መለኮታዊ ሥልጣን ያለው ወይም እርሱ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ገለፀ፡፡ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች ሰዓትም የተናገረውን አስተውል፡፡ "ኢየሱስም በታላቅ ድምጽ ጮኾ አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ፡፡" ይህ ጩኸት ይህ ቃል የሞትን ሥልጣን ያረጋገጠ የዲያቢሎስ መንግስት የቆረጠ ነው፡፡ ሉቃ 23 ፥46

ልዩ ከምትሆን ቅድስት ትንሣኤው በፊትም በኢየሩሳሌም አውራጃዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ሙታንን በማስነሳት እርሱ በሞት ላይ ፍፁም ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን አሳይቶናል፡፡

-    ሉቃ 8፥49-56 ፡- ኢያኢሮስ የተባለው የምኩራብ አለቃ ልጁ በሞተችበት ወቅት ጌታችን በቃሉ አስነስቷታል፡፡ "አንቺ ብላቴና ተነሺ" ብቻ በማለት

 

-    ዮሐ 11፥1-44 ፡- የጌታ ወዳጅ አልዓዛር ሞቶ በተቀበረ በአራተኛው ቀን ጌታችን ትንሣኤና ሕይወት እርሱ መሆኑንና በእርሱ የሚያምን ቢሞትም እንኳ ህያው እንደሚሆን ካወጀ በኋላ ወደመቃብር ሔዶ "አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና" በማለት አስነስቶታል፡፡

በዚህ ላይ ምናልባት አንዳንዶች ነቢያት፣ሐዋርያት ድውይ ፈውሰዋል፣ምውት አንስተዋል ይህን አደረጉ ብለን "ሁሉን ቻይ" እንደማንላቸው ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንዲሁ ነው ብለው ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ 1ኛነገ 17፥17-24፣ 2ኛ ነገ 4፥32-37፣ ሐዋ.ሥራ 9፥40

መልስ

1ኛ- ነቢያትም ሆኑ ሐዋርያት ሙት እስከማንሳት የደረሱት ከልዑል እግዚአብሔር በተሠጣቸው ሥልጣን ጾመው፣ ጸልየው፣ ወድቀው፣ ተነስተው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፡፡ ማር16፥17፣ ሉቃ 10፥17-20፣ዮሐ 14፥12-14፡ እውነት እውነት እላችኋለው በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል… ማናቸውም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ፡፡ ያለውን ቃልኪዳን ይጠብቅላቸዋል፡፡ የእርሱ ግን መጾም፣መጸለይ፣ መውደቅ፣መነሣት ሳያስፈልገው በሥልጣኑ ነው፡፡

2ኛ- ከነቢያትም ሆነ ከሐዋርያት ሙት እስከማንሳት የደረሱ ሁሉ በመጨረሻ እነርሱ ራሣቸው በሥጋ ሞት ተይዘዋል፡፡ ጌታችን በትንሣኤ ዘጉባኤ እስኪያስነሳቸውም ይጠብቃሉ፡፡ሙት ያስነሱ እነርሱ ለራሳቸው ግን አስነሺ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እርሱም ትንሣኤ ሕይወት የተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእርሱ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ይህንኑም ለማስረዳት ነው ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት ሰዓት እንኳ ብዙ ሙታን ተነስተው በኢየሩሳሌም የታዩት፡፡ በማቴ 27፥51-54 መላእክትም ለሴቶቹ " ሕያዋን ከሙታን መካከል ስለምን ትሹታላችሁ እርሱ በዚህ የለም ተነሥቶአል" ያሉአቸው፡፡ ሉቃ 24፥6

         በእነዚህ ከብዙ በጥቂቱ አእምሮን ለማንቃትና እምነትን ለማፅናት ከተጠቀሱት በተጨማሪ ብዙ የመፅሐፍት ቅዱስ ክፍሎችና የአበው ትምህርት ሁሉን ቻይነቱን አምልተው አስፍተው ገልፀውታል፡፡ ያን በማንበብና በማስተዋል የበለጠ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው አምላካዊ ባህርያት ከሆኑት "ሁሉን አዋቂ" ስለመሆኑ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም እንማራለን፡፡

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ጥቅምት 2005

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ሦስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

         በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

            በቀደመ ጽሑፋችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ድንቅ በሆነ ጽንሰቱ፣ ልደቱና በልጅነት ወራት አስደናቂ ህይወቱ ተመልክተናል፡፡ በይቀጥላል ጌታችን በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ራሱን በትምርቱና በተዐምራቱ በገለጠበት ወቅት የህንኑ አስረግጧል፡፡

ዮሐ 2፥1-12 ፡- በተገለጠው ተዐምራት ጌታችን ውሃውን ወደ ወይን መቀየሩን እናውቃለን፡፡ የውሃ እና የወይን ባህርይ በውስጣቸውም የሚይዙት ውሁድ(Substance) የተለያየ እንደሆነ የተረዳ ነገር ነው፡፡ ጌታ በዚህ ተዐምራቱ ካልነበረ(ከሌለ) ነገር አንድን ነገር ማምጣት(መፍጠር) የሚችል መሆኑን አሳይቶናል፡፡

ዮሐ 5፥1 ፡- 38ዓመት ልምሾ ሆኖ እንደትኋን ካልጋ ተጣብቆ የኖረውን መፃጉዕ በቃሉ ብቻ    መፈወሱ ሁሉን ቻይነቱን ያስረዳል፡፡

ዮሐ 9፥1 ፡- በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን መፍጠሩም እንደዚያው በዚሁ ምንባብ ላይ ዓይኑ  የበራለት ሰው በሰጠው ምስክርነት "…ዓለም ከተፈጠረ የዕውርን ዓይን የከፈተ ከቶ አልተሰማም" ማለቱ የጌታችንን ሁሉን ቻይነት የሚያስገነዝብ ምስክርነት ነው፡፡

ማቴ 9፥27-31 ፡- ባለው ተመሳሳይ ታሪክም ሁለቱ ማየት የተሳናቸው ሰዎች እነዲምራቸው  ሲለምኑት "ይህን ማድረግ እንድችል ታምናለችሁ?" ብሎ ነበር የጠየቃቸው ሁሉን ማድረግ ከሚችል ከእርሱ በቀር በሥልጣን ይህን መናገር የሚችል ይኖራልን?

ሉቃ 13፥10-17 ፡- 18 ዓመት በድካም መንፈስ ጎብጣ የኖረች ሴት ሌሎችም በዚህ ጹሑፍ ያልተጠቀሱ ተዐምራቶች የሁሉን ቻይነቱ ማስረጃዎች ናቸው ወንጌል ይህን በአንድ ቃል ሲያጠቀልለው "ህሙማንን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡለት እርሱም ፈወሳቸው" ይላል ከመጣው ውስጥ ተስኖት ሳይፈውሰው የመለሰው አንድ ስንኳ የለም፡፡

በተፈጥሮ ላይ ሁሉን ቻይነቱን ሲገልፅ

ሉቃ 5፥1-10 ፡- ስምዖን ጴጥሮስና ጓደኞቹ ዓሣ ማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ ሞክረው ተስኗቸው   ቀርተዋል፡፡ ጌታ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ መረባቸውን በታንኳይቱ በስተቀኝ እንዲጥሉ ሲያዝ ሌሊቱን ደክመው መያዝ እንዳልቻሉ እንደቃሉ ግን መረቡን እንደሚጥሉ ገልፀው ቢጥሉ መረባቸው እስኪቀደድ ዓሣ ማጥመድ ችለዋል ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን ኃይል ያሳያል፡፡

ማቴ 8፥22-25 ፡- ሐዋርያት የሚቀዝፉትና ጌታ ከበስተኋላ ያንቀላፋባት ታንኳ በብርቱ ማዕበል ስትንገላታ ባህሩም ሊደፍናት ሲቀርብ ሐዋርያት ጌታን ቀስቅሰው "ስንጠፋ አይገድህምን?" ባሉት ጊዜ ጌታ የእምነታቸውን ማነስ ወቅሶ ነፋሱን እና ማዕበሉን ገሠፀ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ሐዋርያትም ሁሉን ቻይነቱን በተረዱ ወቅት "ነፋሳትና ባህር ስንኳ የሚታዘዙለት እርሱ ማንው? ብለው ሰገዱለት ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን አዛዥነት በግልፅ ያስረዳል፡፡

ማቴ 14 ፡-በዚህ ሁለት ታላላቅ ተዐምራት ተደርገዋል፡፡ የመጀመርያው በአምስት ቂጣና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ያህል ወንዶች ሴቶችን ህፃናት ሳይቆጠሩ መግቦ 12 ቅርጫት ፍርፋሪ ማስነሳቱ ሲሆን ሁለተኛው ሐዋርያት በባህሩ መካከል ሳሉ ባህሩን እነደየብስ እየረገጠ መምጣቱ፤ ጴጥሮስ ተጠራጥሮ ሊሰጥም ሲል በውሃ ላይ ቆሞ ውሃ ውስጥ የሚሰጥምን ማውጣቱ ለሁሉን ቻይነቱ መጋለጫ አይደለምን?

          እኒህ ከላይ የተገለፁት ተዐምራት ሁሉ ከአእምሮ በላይ የሆኑ ቢሆኑም ለሰው ልጅ በተሰጠው ደካማ ቋንቋ ስለተፃፉ ግን ውጣቸውን በመንፈስ ለመመርመርና ለማድነቅ ካልተዘጋጀን የሚፈጥሩብን ስሜትም እንዲሁ ደካማ ነው፡፡ በእምነት ለማደግ በቅዱስ እግዚአብሔር ፀጋ ለመበልፀግ ለሚጋደሉ ግን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዓለማትን የፈጠረና ሁሉ በእርሱ ትዕዛዝ የሚመራ መሆኑን ለመረዳት ታሪኮቹ ከበቂ በላይ የሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ባነበብነው መልዕክት ጌታ መንፈስ ቅዱስ ህሊናችንን ለእውነታ ምርኮ ልቦናችንን  ለፍፁም አምልኮ የተዘጋጀ እንዲሆን ይርዳን!

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

ጥቅምት 2005

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ሁለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

          ባለፈዉ ትምህርታችን የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው ከዘላለም እስከ ዘላለም ህያው የሆነ አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል' በይቀጥላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውነታ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እናያለን፡፡

ሁሉን ቻይ :- ማለት እንዳሰበ የሚሠራ እንደፈቀደም የሚያከናዉን& ለሥራው ረዳት አጋዥ    አማካሪ የማይሻ& ሁሉን ከባህርይ የሚያከናውን& በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች በሁሉ የሚሠራ& በሁሉ የሚያዝ በሁሉ ላይ የሠለጠነ &ማንም ማን ለምን ይህን ታደርጋለህ ብሎ ሊከለክለዉ ሊያግደው ሊያስቆመው የማይቻል& በአጠቃላይ ይበልጥ ገላጭ በሆነ ቃል "የሚሳነው ነገር የሌለ" ማለት ነው፡፡ ጥያቄዉ ሁሉን ቻይ የሚለው የአምላካዊ ባህርይ መገላጫ ቅፅል ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋል ወይ? የሚል ነው፡፡ የኦርቶደክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም መልስ እንዴታ ይገባል ነው!!!

ማስረጃ

ትን.ኢሳ 9*6 ህፃን ተወልዶልናልና……ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት                  የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ኃያል አምላክ የሚለው ቃል የተወለደው በሥጋ የተገለጠው እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን የሚያስረግጥ ነው፡፡

ዮሐ 1*3 ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡

          በዚህ ቃልም በቅደምና የነበረው ቃል በኋለኛው ዘመን ሥጋን የተዋሃደው ቃል ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ያስገኘ ምንም ምን ያለእርሱ የሆነ እንደሌለ የሚያስረዳ ነው፡፡

ቆላ 1*15 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትንና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፡፡ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፡፡

የማይታ አምላክ ምላሌ ሲል አምላክ አይደለም ማለቱ አይደለም፡፡ "በሰው ምሳሌ ሆኖ" ሲል ሰው አልሆነም ለማለት እንዳለሆነ ሁሉ ፊል 2*6-8 ሁሉ በእርሱ እንደተገኘ ለእርሱ ክብርም እንደተፈጠረ በመግለጥ ሁሉን ቻይነቱን መሠከረ፡፡

      ፅንስቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ

       ምድር ያለ ዘር ሴት ያለወንድ ትፀንስ ዘንድ ሕገ-ተፈጥሮ አይፍቅድም፡፡ ሁሉ የተገኝ በዚሁ የተፈጥሮ ሥርዓት አልፎ ነው፡፡ የጌታ ፅንት ግን እንዲህ አይደለም ወንጌላዊው ማቴዎስ" ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች" እንዳለ የጌታ ፅንስ ከሦስት ግብራት ንፁህ ነው፡፡ ይኸውም ዘር&ሩካቤ&ሰስሎተ ድንግልና ነው፡፡ጌታችን ሲፀነስ ሩካቤ አልተፈፀም፡ዘርዐ ብእሲ አላስፈለገም የእመቤታችን ድንግልናም አልተለወጠም፡፡ በዚህ እውነትም የተወለደልን ህፃን ኃያል አምላክ ወይም ሁሉን ቻይ መሆኑን ገለጠልን፡፡       ማቴ 1*18-25 & ሉቃ 1*26-56

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ

      የጌታ ልደቱ እንደ ፅንሠቱ ሁሉ ልዩ ነው በልደቱ የእናቱን ድንግልና አልለወጠውም ምጥ ጭንቅ አላገኛትም፡፡ ሰው በር ከፍቶ ወጥቶ ከኋላዉ እንዲዘጋዉ የእርሱ ልደት እንዲህ አይደለም ማኅተመ ድንግልናዋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳን አልተለወጠም ይህ እንዴት ይሆናል? ለሚል

-ጌታ በተዘጋ ቤት ጣርያ ሳይነቅል ግድግዳ ሳያፈርስ መሠረት ሳየቆፍር በር መስኮት ሳይከፍት እንዴት ከሐዋርያት መካከል እንደተገኘ ይመርምር፡፡ ሉቃ 24

ትን.ሕዝ 44*1-3 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አምጣኝ ተዘግቶም ነበር እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡

             ምሥራቅ እመቤታችን የእውነተኛዉ ፀሐይ መውጫ ናትና& መቅደሰ የማኅፀንዋ 9ወር ከ5ቀን ተመስግኖበታልና& በር የማኅተመ ድንግልናዋ ተዘግቶ ይኖራል ማለቱ ለዘላለም እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ ፀንታ መኖርሯን ሲገልጥ ነው፡፡

መዝ.ዳዊ 146*1-2 ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ጽዮንም ሆይ ለአምላክሽ እልል በይ የደጆችሽን መወርመርያ አፅንቷልና፡፡ /በዚህ ጥቀስ ኢየሩሳሌም ጽዮን የተባለች እመቤታችን የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና& የደጆችሽ መወርወርያ የተባለ ማኀተመ ድንግልናዋ ነው አፅንቶ እንደሚጠብቀው ግልጽ ሆኗል፡፡

ኢሳ 66*7 ሳታምጥ ወለደች* ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጀን ወለደች ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶአል?

የህፃንነት እድሜው

           በተዐምረ ኢየሱስና በተለያዩ የቤ/ክ መፃህፍት እንደተገለጠው ጌታ በህፃንነቱ ይፈፅማቸው የነበሩ ተዐምራቶች ሁሉን ቻይ አምላክ ለመሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ከሩቅ ምሥራቅ የመጡትን የጥበብ ሰዋች በኮከብ መምራቱ ሊቃውንትን በሚጠይቀው ጥያቄና በሚሠጠው መልስ ማስደመሙ በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሥልጣን እውቀቱም የባህርይ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይቆየን!

                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                                    ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

                                    ጥቅምት 2005ዓ.ም

Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል አንድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

       በ2005ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ቅዱስ እግዚአብሔር ባዘጋጀልን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መማር እንጀምራለን፡

ትምህርቱ የሚዳስሳቸዉ ነጥቦች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ

·         ቀዳማዊ ወድኅራዊ ሕያዉ ዘላለማዊ አምላክ ስለመሆኑ

·         ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት ስለመወለዱ(ስለ ሁለቱ ልደታት)

·         ስለ ድንቅ  ልደቱና የልጅነት ህይወቱ፣ ስለጥምቀቱ፣ ስለትምህርቱና፣ ስለተዓምራቱ፣ ስለህማሙ፣ስቅለቱ፣ ሞቱ፣ትንሣኤዉና ዕርገቱ፣ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ፣ ወዘተ…ይሆናል፡፡

 

       በቅድሚያ አንድን አካል "አምላክ" ነው ለማለት የአምላክነት ባህርያት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሁሉ ነገር የማንነቱ መገለጫ ወሰን ባህርዩ ነውና፡፡ ሰለዚህ የአምላክነት ባህርያት የሚባሉትና የየትኛዉንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም ፍልስፍና አራማጅ የሚያስማሙት፡-

-    ሕያዉነት(ዘላለማዊነት)    - ሁሉን ቻይነት(Omnipotent)   - ሁሉን አዋቂነት (Omniscient)

-    በሁሉ ስፍራ መገኘት(በቦታ አለመወሰን)Omnipresent

-    ተወካፌ ጸሎት ወአኮቴት (የፍጡራንን ሁሉ ጸሎትና ምስጋና ለመቀበል የተገባው)

-    ዘሥሉጥ ላዕለ ኵሉ(በሁሉ ላይ የሠለጠነ፡በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡

 

1.   ሕያውንት(ዘላለማዊነት):- የዘላለማዊነት ጫፍ ከመገኘት በኋላ (ድኅረ ህላዌ) የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከፊትም የሚኖር ነው' የዘላለም ጫፍ ፊተኛ እና ኋለኛ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም "ኣልቦቱ ጥንተ ወኢተፍፃሜት" እንዲል በቀዳማዊነት ባይሆንም በድህራዊነት ግን ሰውና መላዕክት ይመስሉታል፡፡

 

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሰው ምሳሌ ሆኖ የባርያውን መልክ ይዞ በመካከላችን ቢገለጥም እርሱ ዘላለማዊ ህያው አምላክ መሆኑን ከዚህ በታች የተጠቀስት ምንባባት ያስረዳሉ፡፡

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች

 

v  መዝ109(110) *3 :- ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀኝ በቅዱሳን ብርሃን ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ          ከሆድ ወለድሁህ

v  ምሳ 8 *2-36:- "…እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ በቀድሞ ሥራዉ መጀመሪያ@ ከጥንቱ ከዘላላም  ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርም አስቀድሞ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፡፡

v  ትን.ኢሳ 48*16:- "…ወደ እኔ ቅርቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስዉር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል"

v  ትን.ሚክ 5* 2:- "አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንደ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡ (ከማቴ 2፤5-6 ጋር ይገናዘብ)

v  ዮሐ 1*1-3 :- "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአበሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር…ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳንች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም"

v  ዮሐ 1*30 :- "አንድ ሰው ከኃላዬ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል" መጥምቁ ዮሐንስ ጌታን በሥጋ ልደት 6 ወር እንደሚቀድመዉ በግልፅ የታወቀ ሲሆን እንዴት እንዲህ አለ ቢሉ በቅድምና መኖሩን ማኅፀነ ማርያም የህላዌው መጀመርያ መገኛ አለመሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

v  ዮሐ 8* 55-59 :- "… ገና ሃምሳ አመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ኢየሱስም እዉነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" አላቸዉ፡፡

v  ዩሐ17* 5 :- "… አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንደ በነበረኝ ክብር አክብረኝ

v  ዕብ1*10:- "… ስለ ልጁ ግን ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናፀፍያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጠማል@ አንተ ግን አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም" ቅዱስ ጳዉሎስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት አንዱ ለመሰላቸው እርሱ የመላእክት ጌታ አምላክ እንጂ መልዐክ አለመሆኑን ሲያስረዳ የፃፈው ነው፡፡

v  ራዕ5* 6-8:- "…እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትን ያዩታል… ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡

v  ራዕይ 1*17-18:- "… አትፍራ ፊተኛዉና መጨረሻዉ ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያዉ ነኝ"፡፡

v  ራዕይ 22*12:- "… እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራዉ መጠን እከፍል ዘንድ ወጋዬ ከአኔ ጋር አለ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው መጀመሪያዉና መጨረሻው እኔ ነኝ"፡፡

 

ተጨማሪ ጥቅሶች:- ሉቃ 1* 31-36 & ዮሐ 10* 30& ዮሐ14* 8-11& ቈላ 1*15-20

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

መስከረም 2005 ዓ.ም

Read more...

...በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ብፁዕ ነው፡፡ መዝ ፩፡፩

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

      በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ብፁዕ ነው፡፡ መዝ ፩፡፩

በመዝሙረ ዳዊት የተመሰገኑ ጠባይዓትንና አካሄዶችን አመለካከቶችንና ተግባራትን “ብፁዕ” በሚል የውዳሴ ቃል እያጀበ ተቀኝቶ እናገኛለን፡፡

ብፁዕ የሚለው ቃል “በፅዐ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የሚወጣ ሲሆን የተደነቀ የተመሰገነ ንዑድ ክቡር የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡

ከላይ በተቀመጠው ጥቅስ ክቡር ዳዊት ሦስት አንድን ሰው ወደ ጥፋት የሚወስዱ ጉዳዩችን አንስቶ ከእነርሱ በተቃራኒ የሚገኝ ቢኖር ንዑድ ክቡር ነው ይለናል፡፡

ቀዳሚው በክፉዎች ምክር ያልሄደ ብፁዕ(ምስጉን) ነው ይላል፡፡ ምክር አንድን ሰው ክፉውን ጠባይዕ እንዲተው መልካሙን ደግሞ እንዲያፀና አስነዋሪ ተግባር የበጀ መስሎት የሚኖር ካለ እንዲመለስ፤ የተወደደ ሥራ ለመሥራት መንገድ የጠፋውንም ለማመላከት የሚለገስ የፍቅር የበጎነት መግለጫ ነው፡፡ ሰው የሚመክረው የሚያፈቅረውንና የሚጠነቀቅለትን ነውና፡፡

የገንዘብ ልግስና ራቁት ይሸፍን ረሃብ ያስታግስ ይሆን እነጂ ከክፉ ጠባይ ሊመልስ አይችልም፡፡ ቀና መንገድም አያመለክትም ገንዘብ፡፡ ጊዜያዊ ምክር ግን ቀዋሚ ስጦታ ነው፡፡

በተቃራኒው ክፉ ምክር ደግሞ ሰውን በነፍስ በሥጋ በአሁኑም ሆነ በዘላለማዊው ዓለም ሊያጠፋው ይችላል፡፡የክፉ ምክር መዝገቡ ክፉ ልብ ነው፡፡ ጌታም በወንጌል ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል አስተምሯል፡፡ ጨምሮም ሰውን የሚያረክሱ ክፉ አሳቦች ሁሉ መዝገባቸው ክፉ ልብ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል ማቴ 7፤ ማቴ 15፡፡ በመሆኑም ምክር ሁሉ እንደ መካሪው ማንነት ይወሰናል፡፡ በሕይወት ጉዞ ሰው ክፉም መልካም መካሪ ሊገጥመው ቢችልም በዚያ ተምስርቶ በሚሠራው ሥራ ወይም በሚገልጠው ጠባይ የሚወደሰውም ሆነ የሚነወረው ፤የሚሸለመውም ሆነ የሚቀጣው ራሱ ነው፡፡

ንጉስ ዳዊት በቃሉ ክፉ መካሮች እነዳሉ ከገለጠ በኋላ ብፁዕ የሚባለው ግን በነዚያ ምክር ፈቅዶም ሆነ ተታሎ ያልሄደ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ በክፉ ምክር የተጎዱ የብዙ ሰዎችን የሕይወት ተሞክሮ በዋቢነት ዘግቦ ይዟል፡፡

. የእናታችን ሔዋን በምክረ ከይሲ መመራት በራሷም ሆነ በዘሯ በመከራ ለመጎብኘታቸውና በሞት ለመዳኘታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ መካሪ ምክሩን የሚጀምረው ጉዳያችንን /ምሥጢራችንን/ ከመስማት ነውና በመጀመሪያ ለማን ምን መንገር እንዳለብን ማስተዋል ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የሔዋንና የአዳም በደል/ኃጢአት/ ባህርያዊ ያይደለ በክፉ ምክር ተታለው የፈፀሙት ቢሆንም ከመቀጣት አልዳኑም፡፡ ወደ ቀደመ ክብራቸው የተመለሱ በልጅ ሞት ተክሰው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለ ወላጅ በደል የልጅ ሞት ምን ያህል ይከብድ፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው በወላጆች ጥፋት ልጆች በቀደምት በደል ደኅርት መቀጣታቸው፡፡

ሔዋን እንደ ርዕስ ተነስቶ ምክርና ማስጠንቀቂያ ባልተሠጠበት ጉዳይ ላይ ቢሆን ኖሮ የሳተች ባልፈረድንባት ነበር፡፡ ነገር ግን መልካምነቱን የምታውቀው የአባትነት ድምፁን የለመደችው በእጁ ከመፍጠር አንስቶ ሁሉ እድትገዛ የሠጣት ጌታ እግዚአብሔር የመከራትን ምክር ማንነቱን በማታውቀው ለእርሷ ሕይወት ምንም አስተፅኦ ባልነበረው ባዕድ (እንግዳ) በአንዲት ቅፅበት ንግግር የብዙ ዓመቱን የፍቅር ግንኙነት ማቃለሏ ጭምር በብዙ ያስወቅሷታል፡፡

በመሆኑም ሲጀምር መካሪም ማን መሆኑን ሲቀጥልም ምክሩ በጉዳዩ ላይ አስቀድመን ከሰማናቸው አስተያየቶችም ሆነ ማስጠንቀቂያዎች ጋር ያለውም ተዛምዶ ወይም ተቃርኖ ፈትነን መጓዝ ከኛ የሚጠበቅ ዓይነተኛ ተግባር ነው፡፡ ሰው የሚያስበው የሚናገረው የሚወስነው የሚሰራው ወዘተ ለራሱ ብቻ አይደለም ውጤቱም በራሱ ብቻ አይቆምም፡፡ ላለፈ ትውልድ ታሪክ ለሚመጣውም ደኅንነት ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡ የኛ ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የብዙዎች ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክር እንዲሁም ተግባር ውጤት ነው፡፡ የኛም ተጽእኖ በሌሎች ላይ እንዲሁ ነው፡፡ በእኛ የአካልም ሆነ የመንፈስ አብራክና ማህፀን ውስጥ ብዙ ልጆች ሳይሆን ትውልዶች አሉ፡፡ ዛሬ በክፉ ምክር ስተን የምንፈፅመው ተግባር በርካታ ትውልድን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመልካም ምክር ተመስርተን የምንሰራው ሥራም ለትውልደ ትውልድ ጥቅም ይውላል፡፡ ብዙዎቹም ይታነፁበታል፡፡ ስለነቢዩ ዳዊት ልጆችም እንዲህ ተጻፈ፡፡

ለ. የንጉስ ዳዊት የበኩር ልጅ አምኖን በአባቱ በኩል እህቱ የሆነችውን ትዕማርን በማፍቀሩ ምክንያት ትካዜ በዛበት፡፡ እህል የማይበላ ከመሰሎቹም ጋር የማይጫወት ስሜቱን እያሰታመመ የሚቆዝም ሆነ፡፡ ይህን የተመለከተ ኢዮናዳብ የተባለ ጓደኛውም የንጉሱ ልጅ በምን ምክንያት ደስታ እንደራቀው በጠየቀው ጊዜ በውስጡ ያለውን እረፍት የነሳውን ስሜቱን ተረከለት፡፡ የኢዩናዳብ ምክርም “ታምሜያለሁ ብለህ ተኛ ንጉሱ ልጆቹን ይወዳልና ሊያይህ ይመጣል በዛን ጊዜ ትዕማር ከእጇ እንድበላ ወደኔ ትመጣ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን ብለህ ጠይቀው በዛን ጊዜ የወደድከውን ትፈፅማለህ” የሚል ነበር፡፡ አምኖን እንደተመከረው አደረገ ትዕማርም ባባቷ በንጉስ ዳዊት ወንደምሽ ታሟልና ተንከባከቢው የሚል መልእክት ደረሳት፡፡ ትዕማር የሚበላው ልታቀርብለት ወደ እልፍኙ ስትገባ ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንደ ግድ አላት ትዕማር “ወንድሜ ሆይ አይሆንም እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባም እና አታሳፍረኝ ይህን ነውረኛ ሥራ አታድርግ እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምቴዎች እንዳንዱ ትሆናለህ፡፡ እንግዲህስ ለንጉሱ ንገረው እኔንም አይነሳህም ” 2ሳሙ 13፡1-ፍፃሜ በማለት የመከረችውን አልሰማትም፡፡ ከክብር አሳነሳት የንጉስ ዳዊትን፣ የራሱን፣ የትዕማርና ባጠቃላይ ለቤተሰቡና ለእስራኤል ኃፍረት የሆነ ነውርን ፈፀመ፡፡ በዚህ ሳያበቃ ወትሮም ዝሙት በፍቅር ለምድ ተጀቡና ቀርባው ነበርና ሲያልፍለት ከቀደመው የከፋ በደል ፈጸመ፡፡ መጽሐፍ አምኖን ትዕማርን “ቀድሞ ከወደዳት ውድ ይልቅ ኋላ የጠላት ጥል በለጠ” እንዲል በጉልበት ካስነወራት ከክብርም ካሳነሳት በኋላ በታላቅ ውርደት ከቤቱ አስወጥቶ አባረራት፡፡

ክርስቲያኖች የዝሙት መልኳ እነሆ ይህን ይመስላል፡፡ ፊት ታጣድፋለች መብልና እንቅልፍ በመንሳት እረፍት አሳጥጣ ታስጨንቃለች፡፡ ኅሊናችን በትክክል እንዳያስብ በስሜት ግርዶሽ ታጨልመዋለች፡፡ በዚህ ላይ ለዝሙት የሚያበረታታ የሚፋፋ ክፉ መካሪ ሲያጋጥም መጨረሻዋ መራር ይሆናል፡፡

በዝሙት በተወጠረ ኅሊና ዘንድ ፍቅር አትታወቅም፣ትዕግስትም ሥፍራ የላትም፣ራስን መግዛት ምውት ናት፡፡ በመተቃቀፍ ውስጥ ፍቅር የለችም ጊዜያዊ ስሜት እንጂ፡፡ አንዱን የእንዱን አካል ማክበር አይታሰብም ተራ መጠቀሚያ አድርጎ ከመቁጠር በቀር፡፡

እህቶች ሆይ በክፉ ኅሊና ከሚያደባ በልዝብ ምላስ ከሚሸነግል በመጎምዥት ዓይን ከሚያይ ተጠንቀቁ፡፡ በማን እልፍኝ እንደተገኛችኁም አስተውሉ፡፡

ትዕማር በንፅህና ሙሽራዋን የምትጠብቅ የክርስቲያን ነፍስ ትወክላለች፡፡ ድንግልና በሥጋ ላለ ንጽህና ማሳያ ነውና፡፡ አምኖን የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ይህች ዓለም እኛን በሥጋ ፍቃድ አጥምዳ በኃጢአት እስክትጥለን ድረስ ዕረፍት የላትም ክብራችንን ከጣልን በኋላ ግን ትከፋብናለች፡፡ ኢዩናዳብ የዲያብሎስ ምሳሌ ነው የዚህ ሁሉ ሴራ አቀናባሪ ነውና፡፡ በዓለም ከሚሠራው ኃጢአት፣ተንኰል፣ክፋት፣ዝሙት፣ጥላቻ መከዳዳት ወዘተ…ጀርባ ያለው ክፉው የዲያብሎስ ምክር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ብዙዎች ወደ ዓለም እልፍኝ በክብር ገብተው በውርደት፤በሳቅ ገብተው በለቅሶ፤በዕልልታ ገብተው በዋይታ፤በሙላት ገብተው በጉድለት ወጥተዋል፡፡ አምኖን “እኅቴ” እያለ ይነጋገራት እንዳልነበር ፈቃዱን ከፈጸመ በኋላ “ይህቺን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት” በማለት ጭካኔውን ገልጿል፡፡ ዲያብሎስ ማንንም በክቡር ማማ ላይ ሲያወጣ በመልካም ሲያነጋግር ለእኔ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው ብሎ ካሰበ የመጨረሻው የሞኝነት እርከን ላይ መቆሙን ይወቅ፡፡ ከዝንብ ማር እንደማይገኝ ከዲያብሎስም ርኅራኄን አትጠብቅ፡፡እርሱ ፍቅርን ማወቅም መፈጸምም የሚሻ ፍጥረት አይደለም፡፡

ትዕማርም የንጉስ ልጆች ደናግላኑ የሚለብሱትን ብዙ ኅብር ያለውን ልብሷን ቀዳ በራሷ ላይ አመድ ነስንሳ እጅዋንም ራሷ ላይ ጭና እያለቀሰች ሄደች፡፡

በብዙ ኅብር ያጌጠ ልብስ የተባለ በብዙ ሀብታት(ጸጋዎች) የከበረ በንጉስ ልጅ ማዕረግ የተደነቀ ተፈጥሯችንን ያመለክታል፡፡ በክፉ ምክር ግን ይህ ሁሉ ይጠፋል፡፡

ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት መበለት ሆና ተቀመጠች አምኖንም ከሁለት ዓመት በኋላ በአበሴሎም የቂም ሰይፍ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡

. አምኖን በእህቱ ላይ በሠራው በደል የተበቀለው አቤሴሎም በተራው እስራኤል በተሰበሰቡት በፀሐይ ፊት አባቱ ንጉስ ዳዊትን ለማዋረድ ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ፡፡ ይህን ታላቅ ኃጢአት ያለ ኃፍረት ይፈጸም ዘንድ ያነሳሳው ክፉ መካሪው አኪጦፌል ነበር፡፡ እርሱም በተራው ክፉ አሟሟት መጨረሻው ሆነ፡፡

እኒህ ሁሉ ታሪኮች የሚያሳዩን በክፉዎች ምክር መሄድ ለገሚሱ የሕይወት ምሬት ለተከታዩም መራር ፍጻሜ እንደሚያስተከትል ነው፡፡

ክቡር ዳዊት ንጉሱ ሳኦል ነፍሱን ሲሻ ካንዴም ሁለቴ ለመግደል የሚያሰችለው አጋጣሚ ቢመቻችለትና ዙራውያውን ያሉ መካሪዎችም እጁን እንዲያነሳ ቢጎተጉቱትም “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄንን አላነሳም እንደ ቅንነቴ ይመልስልኛል” በማለት ክፉ ምክራቸውን አልተቀበለም በዚህም “እንደ ልቤ” እስከ መባል በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝቷል፡፡

ማጠቃለያ፡- ምክር ሰምቶ ለሚፈጽማት መልካም መሆኗ አሌ የማይባል ሀቅ ቢሆንም የምክሩን ዓይነት ግን ከእነዚህ ሕግጋት ጋር የማይጣረስ መሆኑን ማስተዋል ያሰፈልጋል፡፡

፩. የተፈጥሮ ሕግ፡- የተደነቀው ተፈጥሯችን ያለ ሕግ አልተሠራም፡፡ በዙሪያው ካሉ ሌሎች ፍጡራን ጋር በኅብረት እንዲኖር የሚያደርገው የመደጋገፍና የድኅንነት ሕገጋት አሉ፡፡ በአጠቃለይ በግላዊ ተፈጥሯችን ላይም ሆነ ከሌሎች ጋር በሚያስተሳስረን የተፈጥሮ ቀመር ጋር የሚጋጭ ምክርና ተግባር በዚህ ምድር ያለንን ቆይታ ያዛባዋል፡፡ ተፈጥሮን በሠራት ዘንድን ያስጠይቀናል፡፡ ዛሬ በሥልጣኔ ወይም በነጻነት ስም ከተፈጥሮ ባህርይ ውጪ የሚፈጸሙ ብዙ አስነዋሪ ተግባራት እንደ መልካም የመብት ጥያቄ በየመድረኩ ሲነሱና የወራዙትን ሕሊና በሚማርክ መልኩ ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ዘመናዊው ሚዲያ የማኅበረሱቡን የሥነ-ምግባር ዕሴቶች ጠብቆ የማቆየትና ለትውልድ የማስተላለፍ ሚናውን ዘንግቶ ንግድ ላይ ያተኮረ በመሆኑም ለወጣቶቹ ሕይወት ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ተቀርጿል፡፡ ዛሬ ዋጋ እያሰከፈለን ያለው የዚህ ሁል ድምር ውጤት ነው፡፡

፪. የማኅበረሰብ ሕግ፡- ማንኘውም ሰው ማንነቱ ተቀርፆ የሚመጣው በዚህ እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ የመጠበቅና ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ከማኅበረሰብ መገለል ወይም አንደ ሥርዓት አልባ መቆጠር ከዚህ በተቃራኒው ከመሆን  የሚመጣ ነው፡፡

. አምላካዊ ሕግ፡ የተፈጥሮም ሆነ የማኅበረስብ  ሕግ ወይም ሌላ ሕገጋት መነሻቸው አምላካዊ ሕግ ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን የምንሰማው ምክር ሁሉ የሚመዘነው ከዚህ አንፀር ነው፡፡ ከአምላካዊው ሕግ በተቃራኒ የሚቀርብ ምንጩ ከክፉ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የአምላክ ሕግ የአምላክ ምክር ለሁሉ እርምጃችን ሚዛን ነው፡፡

ሰው ይህንን ሁሉ በማስተዋል በክፉዎች ምክር ከመጓዝ ቢቆጠብ በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ደኅንነቱ በዙሪያው ላሉ መሰሎቹና በተፈጥሮ ለሚዛመዱት ሁሉ የደስታና የሰላም ምንጭ ይሆናል፡፡ ትናንትን በፀፀት ዛሬን በኃፍረትና በንዴት ነገንም በፍርሃት የሚያስተናግድ ሕይወትም አይኖረውም፡፡ ስኬታማ ሕይወት ይሏል ይህ ነው፡፡

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

ሕዳር ፳፻፮ ዓ.ም

Read more...

ስቅለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ በወልድ ስም  አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብዬ በማመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ሳያደርጉ እማር አስተምር እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና፡፡

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት አደረሳችሁ!

አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!

      ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ታላቅ ቃል የተናገረው በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም እንኳ በነቢዩ በኢሳይያስ እለተ ዓርብን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት " በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" ያለው፤ የጌታን ትዕግስቱን ሲያጠይቅ፤ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ እንጂ ለምዕመናን ጥቅም የሚሆን ቃላቶችን አልተናገረም ለማለት አይደለም፡፡

     ጌታ በመስቀል ሆኖ የተናገራቸውን ቃላት በቤተክርስቲያን "ሰባቱ አጽራሐ መስቀል" ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእኒህ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል ደግሞ ቀዳሚው(የመጀመርያው) " አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዚኢየአምሩ ይገብሩ" የሚለው ነው፡፡

ስለምን ጌታ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል በቀዳሚነት ይህን ተናገረ ቢሉ፡-

ሀ. ወደዚህ ዓለም የመጣው ለዚሁ ነውና ነው፡፡ ይኸውም ትዕዛዝን በማፍረስ ከእግዚአብሔር የተጣላውን(የራቀውን) አዳምን ካሣ ከፍሎና ቤዛ ሆኖ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ነውና ይኽንኑ መፈፀምን ከሁሉ አስቀድሞ ጌታችን ስለዚሁ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ የሚበላ ሲያቀርቡለት " እናንተ የማታውቁት የምበላው አለኝ" በማለት ሲመልስ፤ ሌላ ሰው የሚበላ ያመጣለት ሲመስላቸው ድግሞ "የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው" በማለት አስረድቷቸዋል " ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል" በሚል አስተምህሮውም ምን ያህል ለዚህች ሰዓት ዝግጁ እንደነበር አስረግጧል፡፡ ዮሐ 4፥ ፣ዮሐ 9፥

      ጌታችን የሰውን ድኅነት የመጣበትን ዕርቅ የመፈፀም ሥራ ከመደብደቡ፣ከመገረፉ፣ከመንቸንከሩ በአጠቃላይ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራም ይበልጥ ቅድሚያ ትኩረት ይሠጠው እንደነበር በዚህ እናውቃለን፡፡ ከህማሙ ይልቅ ቅድሚያ የሰጠው የሰውን ድኅነት መሆኑ በዚህ ቃል ተረጋግጧል፡፡ የመቁሰሉ የሞቱ ዓላማ ይኸው ነውና፡፡

ለ. ጠላትን መውደድን በተግባር ለማስተማር ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር " ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ ፣ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ" እንዳለ፤ ጠላቶቹ ሳለን ለወደደን ለእኛ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ለሰቃልያኑም ራርቶ ይቅርታን ለመነልን፡፡ ይህን የሚፈፅሙ ማን መሆኔን ባያውቁ ነው ሲል ይቅርታውን አበዛልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር" እንዳለ በዚህም ሰው በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ቢተላለፍ ንስሐ ከገባ ስርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኝ አስታወቀን፡፡ ለእኛም ስለይቅርታ በቃል ያስተማረንን በተግባር ፈጽሞ አብነት ሆነን እኛም እርሱን አብነት አድርገን ምን ቢበድሉን ፈጽመን ይቅር እንድንል በተግባር አሳየን ሰማዕታትም አርአያውን ተከተሉ፡፡የሐዋ.ሥራ 7፥60

. ጌታ ሌሎቹን ስድስቱን ተናግሮ ይህን ትቶ ቢሆን ኖሮ በኋላ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ወልደ ማርያም ሲሰቀል ወልደ እግዚአብሔር ተለይቶት ነበር ለሚል የስህተት ትምህርታቸው ይመቻቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመስቀል የተሰቀለው፣ መከራን በነሣው ሥጋ የተቀበለው እርሱ በመስቀሉ ላይ ሳለ በመከራው ሰዓት "አባት ሆይ" ብሎ በመጣራቱ መለኮት በለበሰው ሥጋ መከራን ተቀበለ ሞተ…ወዘተ የሚለውን እውነተኛ ትምህርት አጸና፡፡ ይህን ትቶ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" "ተጠማሁ" ወዘተ…የሚለውን ብቻ ተናግሮ ቢሆን ለስህተት ትምህርታቸው ማስረጃ ባደረጉት ነበር፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ከሥጋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳ እንዳልተለየ በዚህ አውቀን ተረዳን፡፡ዕሩቅ ብእሲ(ፍጡር) እግዚአብሔርን " አባት ሆይ" ብሎ ይጠራ ዘንድ አይቻልምና፡፡ እርሱም ተከሶ የተሰቀለበት ምክንያት ይኸው ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል" እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሐር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡" ዮሐ 5፥18

በተጨማሪም ያቺ ሰዓት የይቅርታ የምህረት እንጂ የክስና የፍርድ ሰዓት አልነበረችምና ለሰቃልያኑ እንኳ ምህረትን አደላቸው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ" እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ከቁጣም የራቀ ምህረቱም የበዛ ነው ሁልጊዜም አይቀስፍም ለዘላለምም አይቆጣም እንደ ኃጢአታችንም አላደረገብንም፤ እንደበደላችንም አልከፈለንም " እንዳለ፤ በዮሐንስ ወንጌልም " በእርሱ የሚያምን ሁለ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና፡፡" ጌታም " ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም" በማለት ያቺ የይቅርታ ሰዓት በእርሱም ሆነ ከርሱ ርቀው በኖሩ ፍጥረቶቹ በጽኑ ናፍቆት ትጠበቅ ስለነበር ነው ይቅርታውን የገለፀባት፡፡ ዮሐ 3፡16

     ለሰቃልያኑም ዕድሜ ለንስሐ ሰጣቸው፡፡ ምናልባት በጊዜ ስቅለቱ የተፈፀመውን ዓይተው ሊድኑ ለሚችሉ የመዳን ዕድልን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም የሆነውን ዓይተው ፍፁም አምላክነቱን የተረዱ ፈያታዊ ዘየማንና የጭፍሮች አለቃ የነበረው አምነው መስክረዋል፡ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እና "ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር" በማለት፡፡ ሉቃ 23፥39-43፤ ማር 15፥39

    ለሌሎቹም በስቅለቱና በሞቱ ባያምኑ ዜና ትንሣኤውን ሲሰሙ ምናልባት አምነው ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ 40 ዘመን ታገሣቸው፡፡ ይህም የይቅርታውን ስፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ተጠቅመውበታል፡፡ ያልተጠቀሙበት ግን በ70 ዘመን ጥጦስን አስነስቶ ቀጥቷቸዋል፡፡


 

        ጌታ " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" በሚለው ቃሉ በመስቀሉ ላይ" ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ ጌታ በልደቱ ተፈጥሯችንን፣ በጥምቀቱ ጥምቀትን፣ በፆሙ ፆምን፣ጸልዮ ጸሎትን አንዳች ሳይኖረው ኑሮ መንኖ ጥሪትን፣የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ትህትናን፣ታግሦ ትዕግስትን፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሰማዕትነትን ወዘተ…ፍፁም እንዳደረጋቸው ይቅር ብሎም ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ እርሱ በዚያ ሰዓት የፈፀመው የይቅርታ ሥራ ተከታይ ተቀፅላ የማያስፈልገው የማይደገም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው፡፡

      የአዳም በደል(ኃጢአት) ፍፁም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትን የሠራው ከባህርዩ አንቅቶ ሳይሆን በዲያብሎስ ተታሎ ነውና፡፡ የዲያብሎስና የአዳም በደል ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የኃጢአት የስህተት የሐሰት ሁሉ ነቅዑ ዲያቢሎስ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ዲያብሎስን "…እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ  የሐሰትም አባት ነውና" በማለት የክፋት ሁሉ ምንጩ መነሻው ዲያብሎስ እንደሆነ መስክሮበታል፡፡ ሰው ከዲያብሎስ ያልተማረው ከራሱ አንቅቶ የሠራው ወደፊትም የሚሠራው ኃጢአት የለም አይኖርምም፡፡ ዮሐ 8፡፡  ጌታ የተንኮል ምክሩን እስኪያፈርስበት ድረስ የዲያብሎስ ጥረትም ይኸው ነበር፡፡ ሰውን አዘቅት ውስጥና፤ አምላኩንና የቀደመን መልኩን(ክብሩን) በመርሳት በድንቁርና ጨለማ ተውጦ በመዳኑም ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር ቅዱስ እግዚአብሔርም አዳምን እንደ ዲያብሎስ ይህስ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ከሚጨምር በቀር የቀደመ ሕይወቱ ናፍቆት አይደለም የመዳን ምኞት የሌለው ነው በማለት ከማዳኑ ቸል እንዲለው ተመኝቶ ነበር፡፡

      ምንም እንኳ በመጽሐፍ "በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም " ቢባልም በየዘመናቱ የአዳምን ዘር ወክለው የድኅነትን ምኞትና ተስፋ አንግበው በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት የሚታዩ ቅዱሳን አልጠፉም፡፡ መዝ 13፡ 1-3

     ይልቁንም ዲያብሎስ በአዳም ዘር ውስጥ ከርሱ ባህርይ ከምትገኝ ንጽህት ዘር ተወልዶ እንደሚያድነው የሰጠው ተስፋ፤ያቺ ንጽህት ዘርም እንደ ሚያበራ ንፁህ ዕንቁ በአበው አካልና ባህርይ ውስጥ ስትፋለስ መምጣቷ ኃጢአት በአዳም ላይ ባህርያዊ እንዳይሆንና ዲያብሎስም የተመኘው እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ" ተፈፀመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል"(የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ) ያለው እኛም "ምክሀ ዘመድነ" ምክንያተ ድኂን (የባህርያችን መመኪያ የድኅነታችን ምክንያት) የምንላት፡፡

    በመሆኑም ፈፅሞ በበደል ከእግዚአብሔር የይቅርታ ድንበር ውጪ ያልሆነውን አዳምን የበደለው በምክረ ከይሲ ተታሎ እንጂ ከባህርይ አንቅቶ እንዳልሆነ ጌታ ሲመሰክርለት " የሚሠሩትን አያውቁምና" አለ፡፡ አውቆ አጥፊ እና በስህተት የሚበድል እኩል አይሆንምና በዲያብሎስ ቅጣት ለአዳም ድኅነት ተፈረደ፡፡ አንድም

      አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ፍፃሜውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልዓ" እንዳለ፣ ዲያብሎስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን እንዳያስተውሉ ቢጋርድባቸው ነው እንጂ፤ ኃጢአት ምን ፍዳ እንደሚያመጣባቸው ፈፅመው ጠንቅቀው ቢረዱ አሁን የሚሠሩትን አይሠሩትም ነበር ሲል ነው:: ዛሬም ጊዜ እንኳ ሰው ይህን ቢያውቅ ዘላለማዊው ቅጣትም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ቢረዳ ዛሬ የሚሠራውን ባልሠራው ነበር፡፡ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑ በራሱ እጅግ አስጨናቂ ነውና፡፡ ቅዱሳን ኃጢአትን ብቻ ያይደለ በዓለም ያለ ግብርን ሁሉ እንደ ምናምን ቆጥረው እርግፍ አድርገው ትተው በፍፁም ኃይላቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸውና በፍፁም ልባቸው ጌታን የሚከተሉ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትንና ምረረ ገሃነምን በመረዳታቸው ነው፡፡

      ጌታ በመስቀል በነበረባት በዚያች ሰዓት ራሱን ፍፁም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት፤ ዘላለማዊ ካህን (አስታራቂ) እና ይቅር ባይ(ታራቂ) በመሆን አቀረበ፡፡

      አዳም ከፈጣሪ ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ጸጋው በመገፈፉ ጠባዩ በማደፉና ባህርይው በመጎስቆሉ የተነሳ ይኸው በዘሩ ተጋብቶ የጠብን ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ሊገኝ አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉ በኃጢአት ስለተያዘና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው እርቅን ማምጣት አልቻለም፡፡ከአዳም ጀምሮ የነበሩ  ታላላቅ አበው፣ከሙሴ ጀምሮ የተነሱ ነቢያት ከአሮን አንስቶ የነበሩ ካህናትና ከእያሱ ኋላ የተነሱ መሣፍንት ዳዊትንም የተከተሉ ነገሥት በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት መሥዋዕት ኃጢአትን በደልን ማራቅ ህዝቡንም ከህዝቡ ማስታረቅ አልቻሉም ነበር፡፡

     በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ስለህዝቡ ኃጢአት መስዋዕትና ምልጃ ከማቅረባቸው በፊት ስለራሳቸው ኃጢአት መስዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ ድኅነት ጊዜያዊ እርቅ ከማምጣት ያለፈ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እነርሱም ህዝቡን እንደጥላ(ምሳሌ) በነበረችው ድንኳንና የኦሪት ሥርዓት ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተከትሏቸው ይወርዱ ነበር፡፡ እነርሱም የበለጠ ሊያድናቸው ወደሚችል በብርቱ ጸሎትና ምልጃ ይቃትቱ ነበር፡፡ " አንሥዕ ኃይለከ ወነአ አድኀነነ"(ኃይልህን ግለጥና መጥተህ አድነን) እያሉ በዘመናቸው ሁሉ ይጮኹ ነበር፡፡

    ከዚያም በላይ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ድረስ በኩላብ ተቸንክረው በመጋዝ ተተርትረው ደማቸው ቢፈስም ለዓለም አይደለም ለራሳቸውም ቤዛ መሆን አልቻለም የኒህ ሁሉ ደም ይካሰስ ይፈራረድ እንደሆን እንጂ ይቅርታን ሰላምን ሕይወትን አንድነትን አላመጣም፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ "እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡ጽድቁንም እንደ ጥሩር ለበሰ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ…" እንዳለ የተፈረደውን ፍርድ ሊያስቀር የሚችል እንደሌለ ባወቀ ራሱ ወደዚህ ዓለም መጣ ሥጋንም ለብሶ ተገለጠ፡፡    ኢሳ 59፡ 15-17

     ጌታ ዓለሙን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ሲገለጥ ክህነቱ(የማስታረቅ አገልግሎቱ) ከብሉይ ኪዳን ካህናት በእጅጉ የራቀና የመጠቀ ነበር፡፡

፩. የብሉይ ካህናት መሥዋዕት ሲያቀርቡ መጀመርያ ለራሳቸው ቀጥሎ ለህዝቡ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለ ኃጢአት ያለ ነውር ስለተገለጠ  ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሲናገር " ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ዕብ 5፥5-4

፪. የብሉይ ካህን በዘር ጨምሮም በቅዱስ ቅባት ተቀብቶ የክህነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ሰያሜ ካህናት የሆነው ጌታ ግን ከማንም አልተቀበለውም፡፡ ስለ እርሱ እንደተባለ" አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ" ሿሚ የለበትም፡፡ዕብ 5፥5-6

፫. የብሉይ ካህን ጊዜአዊ እርቅን የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሊያሰጥ የሚችል የፍየልና የኮርማዎች ደም ያቀርብ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሥጋን ነፍስን ደመ ነፍስን የሚቀድስ ክቡር ደሙን አፍስሶና ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ አስታረቀን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ" የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ፤ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?" በማለት ገልፆታል፡፡ ዕብ9፥13-14 

     ጨምሮም "…የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ "መስዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ፡፡በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተፃፈ አምላኬ ሆይ ፍቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ" ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትና ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደህግ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህ ላደርግ መጥቻለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም ፊተኛውን ይሽራል በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡" በዚህም ቃል በግልፅ ቃል መሥዋዕተ ኦሪት ተሽሮ መስዋዕተ ሐዲስ እንደተተካ ይህ የሆነበት ምክንያትም የኃጢአት ሥርየት ማምጣት አለመቻሉና መለኮታዊውንም ፍርድ አለማርካቱ መሆኑን አትቷል፡፡ዕብ 10፥4-10

     የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የእውነተኛይቱ ምሳሌ በምትሆን ቅድስተ ቅዱሳን በዕለትና በዓመት ኃጢአትን ሊያስወግዱ የማይችሉበትን መስዋዕቶች ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ምሳሌይቱ ሳይሆን አማናዊ ወደሆነችው ቅድስት አንድን መስዋዕት አንድ ጊዜ አቅርቦ ኃጢአትን በማስወገድ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "… ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሰዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ  ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሺር አንድ ጊዜ ተገልጦአል…" ጨምሮም  " ሊቀ ካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡" በማለት ጽፏል፡፡ዕብ 9፥24-28፤ ዕብ 10፥11-12

      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የማስታረቅ አገልግሎቱን በራሱ ብቻ አላስቀረውም ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደራሴው በመሆን በእርሱ ተገብተው በሚሠውት የእርሱ ሥጋና ደም በእምነት ለሚቀርቡ ሁሉ ጊዜአዊ ያይደለ ዘላለማዊ ድኅነትን ፍፁም ይቅርታን ለምዕመናን ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ"…ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤ በደላቸውም አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ " በማለት የአዲስ ኪዳን ካህናት ከብሉይ ካህናት ምን ያህል የሚበልጥ የክህነትን ክብር እንደተቀዳጁ ጽፏል፡፡ 2ቆሮ 5፥18-21

     ከላይ በተብራራው ላይ መሥዋዕቱ እርሱ መሥዋዕቱን አቅራቢውም እራሱ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ ሌላው በዚሁ የምናየው ነጥብ ተወካፌ መሥዋዕቱ እርሱ ራሱ መሆኑንም ነው፡፡ በአዳም የሞትን ፍርድ የፈረደበት እርሱ፤የይቀርታን የድኅነትን ቃል " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቀር በላቸው" በማለት አወጀልን፡፡ በዚህ ቃል የጠብ ግድግዳ ፈረሰ የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ለሰው ዘር ፍፁም ካሣ ተክሶ አዳምም ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም" እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው" ብሏል፡፡ አክሎም " እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግደግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡" በማለት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንዴት እንደታረቀን አስተምሯል፡፡ኤፌ 2፥13-16፤ቆላ 2፥13-15

     በአዲስ ሥርዓት በሆነ ደሙ ላጠበን ከበደላችንም ሁሉ ላነፃን ይቀርታውንና ምህረቱን ላበዛልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም መቼም መች ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!

ይቆየን!

ጥር 2005 ዓ.ም

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 

Read more...

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ