ስቅለት
ጌታ " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" በሚለው ቃሉ በመስቀሉ ላይ" ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ ጌታ በልደቱ ተፈጥሯችንን፣ በጥምቀቱ ጥምቀትን፣ በፆሙ ፆምን፣ጸልዮ ጸሎትን አንዳች ሳይኖረው ኑሮ መንኖ ጥሪትን፣የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ትህትናን፣ታግሦ ትዕግስትን፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሰማዕትነትን ወዘተ…ፍፁም እንዳደረጋቸው ይቅር ብሎም ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ እርሱ በዚያ ሰዓት የፈፀመው የይቅርታ ሥራ ተከታይ ተቀፅላ የማያስፈልገው የማይደገም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው፡፡
የአዳም በደል(ኃጢአት) ፍፁም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትን የሠራው ከባህርዩ አንቅቶ ሳይሆን በዲያብሎስ ተታሎ ነውና፡፡ የዲያብሎስና የአዳም በደል ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የኃጢአት የስህተት የሐሰት ሁሉ ነቅዑ ዲያቢሎስ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ዲያብሎስን "…እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና" በማለት የክፋት ሁሉ ምንጩ መነሻው ዲያብሎስ እንደሆነ መስክሮበታል፡፡ ሰው ከዲያብሎስ ያልተማረው ከራሱ አንቅቶ የሠራው ወደፊትም የሚሠራው ኃጢአት የለም አይኖርምም፡፡ ዮሐ 8፡፡ ጌታ የተንኮል ምክሩን እስኪያፈርስበት ድረስ የዲያብሎስ ጥረትም ይኸው ነበር፡፡ ሰውን አዘቅት ውስጥና፤ አምላኩንና የቀደመን መልኩን(ክብሩን) በመርሳት በድንቁርና ጨለማ ተውጦ በመዳኑም ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር ቅዱስ እግዚአብሔርም አዳምን እንደ ዲያብሎስ ይህስ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ከሚጨምር በቀር የቀደመ ሕይወቱ ናፍቆት አይደለም የመዳን ምኞት የሌለው ነው በማለት ከማዳኑ ቸል እንዲለው ተመኝቶ ነበር፡፡
ምንም እንኳ በመጽሐፍ "በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም " ቢባልም በየዘመናቱ የአዳምን ዘር ወክለው የድኅነትን ምኞትና ተስፋ አንግበው በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት የሚታዩ ቅዱሳን አልጠፉም፡፡ መዝ 13፡ 1-3
ይልቁንም ዲያብሎስ በአዳም ዘር ውስጥ ከርሱ ባህርይ ከምትገኝ ንጽህት ዘር ተወልዶ እንደሚያድነው የሰጠው ተስፋ፤ያቺ ንጽህት ዘርም እንደ ሚያበራ ንፁህ ዕንቁ በአበው አካልና ባህርይ ውስጥ ስትፋለስ መምጣቷ ኃጢአት በአዳም ላይ ባህርያዊ እንዳይሆንና ዲያብሎስም የተመኘው እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ" ተፈፀመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል"(የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ) ያለው እኛም "ምክሀ ዘመድነ" ምክንያተ ድኂን (የባህርያችን መመኪያ የድኅነታችን ምክንያት) የምንላት፡፡
በመሆኑም ፈፅሞ በበደል ከእግዚአብሔር የይቅርታ ድንበር ውጪ ያልሆነውን አዳምን የበደለው በምክረ ከይሲ ተታሎ እንጂ ከባህርይ አንቅቶ እንዳልሆነ ጌታ ሲመሰክርለት " የሚሠሩትን አያውቁምና" አለ፡፡ አውቆ አጥፊ እና በስህተት የሚበድል እኩል አይሆንምና በዲያብሎስ ቅጣት ለአዳም ድኅነት ተፈረደ፡፡ አንድም
አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ፍፃሜውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልዓ" እንዳለ፣ ዲያብሎስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን እንዳያስተውሉ ቢጋርድባቸው ነው እንጂ፤ ኃጢአት ምን ፍዳ እንደሚያመጣባቸው ፈፅመው ጠንቅቀው ቢረዱ አሁን የሚሠሩትን አይሠሩትም ነበር ሲል ነው:: ዛሬም ጊዜ እንኳ ሰው ይህን ቢያውቅ ዘላለማዊው ቅጣትም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ቢረዳ ዛሬ የሚሠራውን ባልሠራው ነበር፡፡ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑ በራሱ እጅግ አስጨናቂ ነውና፡፡ ቅዱሳን ኃጢአትን ብቻ ያይደለ በዓለም ያለ ግብርን ሁሉ እንደ ምናምን ቆጥረው እርግፍ አድርገው ትተው በፍፁም ኃይላቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸውና በፍፁም ልባቸው ጌታን የሚከተሉ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትንና ምረረ ገሃነምን በመረዳታቸው ነው፡፡
ጌታ በመስቀል በነበረባት በዚያች ሰዓት ራሱን ፍፁም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት፤ ዘላለማዊ ካህን (አስታራቂ) እና ይቅር ባይ(ታራቂ) በመሆን አቀረበ፡፡
አዳም ከፈጣሪ ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ጸጋው በመገፈፉ ጠባዩ በማደፉና ባህርይው በመጎስቆሉ የተነሳ ይኸው በዘሩ ተጋብቶ የጠብን ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ሊገኝ አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉ በኃጢአት ስለተያዘና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው እርቅን ማምጣት አልቻለም፡፡ከአዳም ጀምሮ የነበሩ ታላላቅ አበው፣ከሙሴ ጀምሮ የተነሱ ነቢያት ከአሮን አንስቶ የነበሩ ካህናትና ከእያሱ ኋላ የተነሱ መሣፍንት ዳዊትንም የተከተሉ ነገሥት በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት መሥዋዕት ኃጢአትን በደልን ማራቅ ህዝቡንም ከህዝቡ ማስታረቅ አልቻሉም ነበር፡፡
በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ስለህዝቡ ኃጢአት መስዋዕትና ምልጃ ከማቅረባቸው በፊት ስለራሳቸው ኃጢአት መስዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ ድኅነት ጊዜያዊ እርቅ ከማምጣት ያለፈ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እነርሱም ህዝቡን እንደጥላ(ምሳሌ) በነበረችው ድንኳንና የኦሪት ሥርዓት ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተከትሏቸው ይወርዱ ነበር፡፡ እነርሱም የበለጠ ሊያድናቸው ወደሚችል በብርቱ ጸሎትና ምልጃ ይቃትቱ ነበር፡፡ " አንሥዕ ኃይለከ ወነአ አድኀነነ"(ኃይልህን ግለጥና መጥተህ አድነን) እያሉ በዘመናቸው ሁሉ ይጮኹ ነበር፡፡
ከዚያም በላይ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ድረስ በኩላብ ተቸንክረው በመጋዝ ተተርትረው ደማቸው ቢፈስም ለዓለም አይደለም ለራሳቸውም ቤዛ መሆን አልቻለም የኒህ ሁሉ ደም ይካሰስ ይፈራረድ እንደሆን እንጂ ይቅርታን ሰላምን ሕይወትን አንድነትን አላመጣም፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ "እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡ጽድቁንም እንደ ጥሩር ለበሰ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ…" እንዳለ የተፈረደውን ፍርድ ሊያስቀር የሚችል እንደሌለ ባወቀ ራሱ ወደዚህ ዓለም መጣ ሥጋንም ለብሶ ተገለጠ፡፡ ኢሳ 59፡ 15-17
ጌታ ዓለሙን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ሲገለጥ ክህነቱ(የማስታረቅ አገልግሎቱ) ከብሉይ ኪዳን ካህናት በእጅጉ የራቀና የመጠቀ ነበር፡፡
፩. የብሉይ ካህናት መሥዋዕት ሲያቀርቡ መጀመርያ ለራሳቸው ቀጥሎ ለህዝቡ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለ ኃጢአት ያለ ነውር ስለተገለጠ ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሲናገር " ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ዕብ 5፥5-4
፪. የብሉይ ካህን በዘር ጨምሮም በቅዱስ ቅባት ተቀብቶ የክህነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ሰያሜ ካህናት የሆነው ጌታ ግን ከማንም አልተቀበለውም፡፡ ስለ እርሱ እንደተባለ" አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ" ሿሚ የለበትም፡፡ዕብ 5፥5-6
፫. የብሉይ ካህን ጊዜአዊ እርቅን የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሊያሰጥ የሚችል የፍየልና የኮርማዎች ደም ያቀርብ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሥጋን ነፍስን ደመ ነፍስን የሚቀድስ ክቡር ደሙን አፍስሶና ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ አስታረቀን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ" የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ፤ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?" በማለት ገልፆታል፡፡ ዕብ9፥13-14
ጨምሮም "…የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ "መስዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ፡፡በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተፃፈ አምላኬ ሆይ ፍቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ" ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትና ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደህግ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህ ላደርግ መጥቻለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም ፊተኛውን ይሽራል በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡" በዚህም ቃል በግልፅ ቃል መሥዋዕተ ኦሪት ተሽሮ መስዋዕተ ሐዲስ እንደተተካ ይህ የሆነበት ምክንያትም የኃጢአት ሥርየት ማምጣት አለመቻሉና መለኮታዊውንም ፍርድ አለማርካቱ መሆኑን አትቷል፡፡ዕብ 10፥4-10
የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የእውነተኛይቱ ምሳሌ በምትሆን ቅድስተ ቅዱሳን በዕለትና በዓመት ኃጢአትን ሊያስወግዱ የማይችሉበትን መስዋዕቶች ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ምሳሌይቱ ሳይሆን አማናዊ ወደሆነችው ቅድስት አንድን መስዋዕት አንድ ጊዜ አቅርቦ ኃጢአትን በማስወገድ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "… ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሰዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሺር አንድ ጊዜ ተገልጦአል…" ጨምሮም " ሊቀ ካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡" በማለት ጽፏል፡፡ዕብ 9፥24-28፤ ዕብ 10፥11-12
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የማስታረቅ አገልግሎቱን በራሱ ብቻ አላስቀረውም ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደራሴው በመሆን በእርሱ ተገብተው በሚሠውት የእርሱ ሥጋና ደም በእምነት ለሚቀርቡ ሁሉ ጊዜአዊ ያይደለ ዘላለማዊ ድኅነትን ፍፁም ይቅርታን ለምዕመናን ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ"…ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤ በደላቸውም አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ " በማለት የአዲስ ኪዳን ካህናት ከብሉይ ካህናት ምን ያህል የሚበልጥ የክህነትን ክብር እንደተቀዳጁ ጽፏል፡፡ 2ቆሮ 5፥18-21
ከላይ በተብራራው ላይ መሥዋዕቱ እርሱ መሥዋዕቱን አቅራቢውም እራሱ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ ሌላው በዚሁ የምናየው ነጥብ ተወካፌ መሥዋዕቱ እርሱ ራሱ መሆኑንም ነው፡፡ በአዳም የሞትን ፍርድ የፈረደበት እርሱ፤የይቀርታን የድኅነትን ቃል " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቀር በላቸው" በማለት አወጀልን፡፡ በዚህ ቃል የጠብ ግድግዳ ፈረሰ የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ለሰው ዘር ፍፁም ካሣ ተክሶ አዳምም ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም" እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው" ብሏል፡፡ አክሎም " እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግደግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡" በማለት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንዴት እንደታረቀን አስተምሯል፡፡ኤፌ 2፥13-16፤ቆላ 2፥13-15
በአዲስ ሥርዓት በሆነ ደሙ ላጠበን ከበደላችንም ሁሉ ላነፃን ይቀርታውንና ምህረቱን ላበዛልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም መቼም መች ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!
ይቆየን!
ጥር 2005 ዓ.ም
ቀሲስ ታምራት ውቤ