ሆሣዕና
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ልዑሉ ሲናገር “የእኛ ሕዝብህ መሆን ላንተ አያስፈልግህም ያንተ ጌትነት ለእኛ ያስፈልገናል እንጂ፤የእኛ ልጅነት ላንተ አይጠቅምህም ያንተ አባትነት ለእኛ ይጠቅመናል እንጂ” በማለት ገልፆታል፡፡ አባትነቱ በእኛ ልጅነት አይደነቅም፤ጌትነቱም በእኛ ተገዢነት አይከብርም፡፡ ዛዲያ “ታስፈልጉኛላችሁ” መባሉ ስለምንድር ነው?
እንመርምረው ዘንድ አይቻለንም! መልስ እናገኝለት ዘንድም ቅጥነተ አእምሯችን አይወስነውም! እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለ ርኅራኄስ እንደምን ያለ ርኅራኄ ነው ብለን ከማድነቅ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?/ ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ/
ጌታ ሆይ ልትፈልገን መጥተሃልና፤ታስፈልጉኛለችሁ ብለህም በክብር ጠርተኸናልና፤በአፈ አበው ቀደምት፣በልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት፣ጻድቃን ወሰማዕታት፣አእሩግ ወሕፃናት፤በአኰቴተ መላእክት ወሊቃናት እናመሰግንሃለን፡፡ ምስጋናና ክብር ኃይልና ባለጠግነት ጌትነትም በመታረዱ ለፈለገን ለበጉና ለአባቱ ለመንፈስ ቅዱስም ይገባል መቼም መች ለዘላለሙ አሜን! ራዕይ 4፥6-14
ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ ይመጣል
ለጽዮን ንጉሷ እንዲሚመጣ በአፈ ነቢያት ተነግሯታል፡፡ የሚመጣው ግን እንደነ ሰሎሞን በዝሆን ጥርስ በብርና በወርቅ ባጌጠ፤በሀምራዊ ግምጃ በተሸፈነ ሠረገላ ሳይሆን በአህያና በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ የዋህ ሆኖ ነው፡፡
የዋህ የሚለው ኀዳጌ በቀል መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጌታችን የመጣው አንገተ ደንዳና ወደ ሆነ የነቢያቱንና የካህናቱን ደም ወዳፈሰሰ ሕጉንም በወግና በልማድ ወደ አፈረሰ ሕዝብ ነው፡፡ መጻሕፍቱን የነቢያቱንም ቃል ያነባሉ ለመቀበል ግን አይፈልጉም፡፡ ምንም እንኳ ሰይፈ በቀል በእጁ ቢሆንና ፍርድ ቢገባቸውም ሰው የመሆኑ ዓላማ ሁሉን ለማዳን እንጂ በአንድ ስንኳ ለመፍረድ ስላልሆነ በየዋህነት ተገለጠ፡፡ የነቢያትን ደም ባፈሰሰ እጃቸው የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ በመስቀል ሰቅለው ጽዋቸውን ቢሞሉም “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለቱ የምህረት እንጂ የበቀል ጊዜ አለመሆኑን አሳያቸው፡፡ የምህረት የይቅርታ ጊዜ አለ፤ከወዳጆቹ ከነቢያት ጀምሮ ላፈሰሱት ደም የበቀል ጊዜ ደግሞ ይኖራል፡፡ ዮሐ 3፥16፤ማቴ21፥33-46፤ማቴ 23፥29-36
“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው”
ሆሣዕና በዕብራውያን ቋንቋ “አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” የሚል ትርጉም አንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ሆሣዕና የሚለው ቃል ሰው ሲደነቅ ወይም ሲደሰት ከሚያወጣው ድምፅ ጋር በማመሳሰል በሌላ ቋንቋ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው እንደማይቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱም ትርጓሜ አይጣላም፡፡
አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው ቢሉ ጉዞው ወደ መስቀል ነበርና እውነተኛ መድኃኒትም እርሱ ነውና የተገባ ምስጋና ነው፡፡
ቃለ አንክሮ ቃለ ትፍስሕት ነው ቢሉም በዚያ የተሰበሰቡ አብዛኞቹ ያደረገውን ተዐምራቶች እያወሱ ይመሰክሩም ስለነበር፡፡ አንድም ከነበረው የአቀባበል ሁኔታ አንድም እንደ ኢትዮጵያ ሊቃውንት ትርጓሜ የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት ይታይ ነበርና አድናቆቱ የተገባ ነው፡፡
ሆሣዕና እያሉ የሚያመስግኑት ሁሉ“የዳዊት ልጅ” እና “ጌታ” ብለው ጠርተውታል፡፡ በዚህም የዳዊት ልጅ በማለታቸው ፍፁም ሰው መሆኑን አንድም“እግዚአብሔር ማለ አይፀፀትም ከወገብህ ከሚወጣ ከዘርህ በዙፋንህ አኖራለሁ” የተባለው ትንቢት መፈፀሙን ያጠይቃል፡፡አይሁድም በገዛ አፋቸው ክርስቶስ ማነው? ብሎ ሲጠይቃቸው የዳዊት ልጅ ነው ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ አሁን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ላለማመን ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ 2ሳሙ7፥12-14፤ማቴ22፥41-46
በ“ጌታ” ስም የሚመጣ ማለት እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሎ የሚመጣ የተባረከ ነው ብለዋል፡፡ አይሁድ “YHWH” የሚለውን በአብዛኛው የሥነ-መለኮት ሊቃውንት “ያህዌ” የሚል ግምት የሚሠጠውን በኮሬብ ለሙሴ የተገለጠ ስመ አምላክ ለመጥራት ሰለማይደፍሩ “Adonai” ወይም “ጌታ” በሚል ቀይረውታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጌታ የሚለው ቅፅል በቀጥታ ለእስራኤል አምላክ የሚነገር በመሆኑ “በጌታ ስም” “የሚመጣ” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ገልፀዋል፡፡ ማቴ 22፥41-46
ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በዕለተ ሆሣዕና ይመሰክሩ የነበሩ መጻሕፍት አንብበው ከሊቃውንት አፍ ተምረው ትንቢት የተረጎሙ ሱባዔ የቆጠሩ አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጭምር ነበሩ፡፡ አይሁድንም ይበልጥ ያስቆጣው ህፃናቱ ያመሰገኑበት መንፈስ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ተዐምር ነውና፡፡
ምንጊዜም ንፁህ ምስጋና ፣ ንፁህ ጸሎት፣ንፁህ መሥዋዕት፣ንፁህ ልቡና፣ ንፁህ አገልግሎት ይበልጡንንፁህ ሕይወት አጋንንትን፣ ክፍዎችን፣ ተንሎለኞችን፣ ተረፈ አይሁድን፣መናፍቃንን፣ አረማውያንን ያስቆጣል፡፡ ይህ እንዲቋረጥ የማያኖሩት እንቅፋት የማይፈፅሙት ድርጊት አይኖርም፡፡ ንጹሐ ባህርይ ከሆነው ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ በንፁህ ህይወት የኖሩ በንፁህ አገልግሎት የፀኑ ሁሉ ተገፍተዋል ተዋርደዋል፤ለሞትም ወደ መታረጃቸው ተነድተዋል፡፡ ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ንፁህ ሁን በዓለም ወደ ኋላ ትቀራለህ ትዋረድማለህ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ግን ትቀድማለህ ትከብርማለህ፡፡ ማቴ 14፥1-4 ዮሐ15፥18-21
ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁሉ ይዘው የተቀበሉት የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ወደ መስቀል የሚወጣ ለድል ነውና፡፡ ይህ ሁሉ የሰው አቀባበልና ምስጋና ጌታችንን ለአመል ከዓላማው አላዘናጋውም፤ ለመጣባት ለዚያች ሰዓት አዘጋጀው እንጂ፡፡ አድናቆት ሊያጅበን ምስጋና ሊነጠፍልን ይችላል፤ዓላማችን ምን መሆኑን ግን ልንረሳ አይገባንም፡፡ ከሰዎች ክብርን ብንቀበል ከእግዚአብሔር ከሆነው ክብር ከተጣልን ምን ይጠቅመናል፡፡ ሊጠቀምብህ የሚፈልግ ያወድስሃል ሊጠቅምህ የቆረጠ ግን ይገሥፅሃል፡፡ ወዳጀህን መምረጥ ያንተ ድርሻ ነው፡፡
የአይሁድ ሊቃናት እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻለችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል“ ይባባሉ ነበር፡፡ ቅንዐት ጥላቻን ይወልዳል ጥላቻ ደግሞ ሞትን፡፡ ጌታችን እንደቃሉ ወደ ትክክለኛዋ ሰዓት ቢመጣም በቁሙ ሲታይ ግን የሆሣዕና ትዕይንት በአይሁድ ሊቃናት ላይ ያሳደረው ቅንዐትና ቁጣ በሞቱ ላይ እንዲቆርጡ በከፍተኛ ሁኔታ አነሣስቷቸዋል፡፡እርሱ ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንደ ሰዓቱ ደርሶአል፡፡እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ብትሞትም ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች”በማለት በሞቱ ይበልጡ ብዙዎችን እንደሚያድንና ወደ ራሱ እንደሚስብ ነግሯቸዋል፡፡
የእግዚአብሔር መንግስት ከጥንት ጀምሮ የሚጋፏት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን ከመጨመር ልዑለ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከመከተል አላስቆሙትም፡፡ ገና በሃይማኖቱ ጠንክሮ እየቆመ በኅሊና ትንሣኤ ኃጢአትን ድል አድርጎ እየዘመረ ይከተለዋል፡፡ የታመነ መሪ ነውና፡፡“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ መከተል ማለት በግብር መምሰል በአርአያነቱ መጽናት ነው፡፡ በህይወታችን በኑሮአችን ከመሰልነው በሞቱ እንመስለዋለን በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን፡፡ ክርስትና ማለት ቅሉ ይኸው ነውና፡፡ የበዓሉ ጌታ ቸርነቱ ይደረግልን! ማቴ11፥12፤ዮሐ10፥1-18፤ሮሜ 6፥5
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት