ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል አንድ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በ2005ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ቅዱስ እግዚአብሔር ባዘጋጀልን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መማር እንጀምራለን፡
ትምህርቱ የሚዳስሳቸዉ ነጥቦች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
· ቀዳማዊ ወድኅራዊ ሕያዉ ዘላለማዊ አምላክ ስለመሆኑ
· ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት ስለመወለዱ(ስለ ሁለቱ ልደታት)
· ስለ ድንቅ ልደቱና የልጅነት ህይወቱ፣ ስለጥምቀቱ፣ ስለትምህርቱና፣ ስለተዓምራቱ፣ ስለህማሙ፣ስቅለቱ፣ ሞቱ፣ትንሣኤዉና ዕርገቱ፣ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ፣ ወዘተ…ይሆናል፡፡
በቅድሚያ አንድን አካል "አምላክ" ነው ለማለት የአምላክነት ባህርያት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሁሉ ነገር የማንነቱ መገለጫ ወሰን ባህርዩ ነውና፡፡ ሰለዚህ የአምላክነት ባህርያት የሚባሉትና የየትኛዉንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም ፍልስፍና አራማጅ የሚያስማሙት፡-
- ሕያዉነት(ዘላለማዊነት) - ሁሉን ቻይነት(Omnipotent) - ሁሉን አዋቂነት (Omniscient)
- በሁሉ ስፍራ መገኘት(በቦታ አለመወሰን)Omnipresent
- ተወካፌ ጸሎት ወአኮቴት (የፍጡራንን ሁሉ ጸሎትና ምስጋና ለመቀበል የተገባው)
- ዘሥሉጥ ላዕለ ኵሉ(በሁሉ ላይ የሠለጠነ፡በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡
1. ሕያውንት(ዘላለማዊነት):- የዘላለማዊነት ጫፍ ከመገኘት በኋላ (ድኅረ ህላዌ) የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከፊትም የሚኖር ነው' የዘላለም ጫፍ ፊተኛ እና ኋለኛ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም "ኣልቦቱ ጥንተ ወኢተፍፃሜት" እንዲል በቀዳማዊነት ባይሆንም በድህራዊነት ግን ሰውና መላዕክት ይመስሉታል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሰው ምሳሌ ሆኖ የባርያውን መልክ ይዞ በመካከላችን ቢገለጥም እርሱ ዘላለማዊ ህያው አምላክ መሆኑን ከዚህ በታች የተጠቀስት ምንባባት ያስረዳሉ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች
v መዝ109(110) *3 :- ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀኝ በቅዱሳን ብርሃን ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ
v ምሳ 8 *2-36:- "…እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ በቀድሞ ሥራዉ መጀመሪያ@ ከጥንቱ ከዘላላም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርም አስቀድሞ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፡፡
v ትን.ኢሳ 48*16:- "…ወደ እኔ ቅርቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስዉር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል"
v ትን.ሚክ 5* 2:- "አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንደ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡ (ከማቴ 2፤5-6 ጋር ይገናዘብ)
v ዮሐ 1*1-3 :- "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአበሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር…ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳንች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም"
v ዮሐ 1*30 :- "አንድ ሰው ከኃላዬ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል" መጥምቁ ዮሐንስ ጌታን በሥጋ ልደት 6 ወር እንደሚቀድመዉ በግልፅ የታወቀ ሲሆን እንዴት እንዲህ አለ ቢሉ በቅድምና መኖሩን ማኅፀነ ማርያም የህላዌው መጀመርያ መገኛ አለመሆኑን ለማመልከት ነው፡፡
v ዮሐ 8* 55-59 :- "… ገና ሃምሳ አመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ኢየሱስም እዉነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" አላቸዉ፡፡
v ዩሐ17* 5 :- "… አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንደ በነበረኝ ክብር አክብረኝ
v ዕብ1*10:- "… ስለ ልጁ ግን ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናፀፍያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጠማል@ አንተ ግን አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም" ቅዱስ ጳዉሎስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት አንዱ ለመሰላቸው እርሱ የመላእክት ጌታ አምላክ እንጂ መልዐክ አለመሆኑን ሲያስረዳ የፃፈው ነው፡፡
v ራዕ5* 6-8:- "…እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትን ያዩታል… ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡
v ራዕይ 1*17-18:- "… አትፍራ ፊተኛዉና መጨረሻዉ ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያዉ ነኝ"፡፡
v ራዕይ 22*12:- "… እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራዉ መጠን እከፍል ዘንድ ወጋዬ ከአኔ ጋር አለ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው መጀመሪያዉና መጨረሻው እኔ ነኝ"፡፡
ተጨማሪ ጥቅሶች:- ሉቃ 1* 31-36 & ዮሐ 10* 30& ዮሐ14* 8-11& ቈላ 1*15-20
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቀሲስ ታምራት ውቤ
መስከረም 2005 ዓ.ም