Login
Main menu

ደብረዘይት

Featured

በስመ  አብ  ወወልድ  ወመንፈስ ቅዱስ  አሐዱ  አምላክ  አሜን!

የቀጠለ...

፭.ደብረዘይት፡- በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን ነገረ ምፅዓቱ ይታሰባል፡፡ ደብረዘይት ይህንኑ እውነታ ጌታ ለሐዋርያት ያስታወቀበት ተራራ ነው፡፡ ዳግመኛም መምጣቱ በዚሁ ተራራ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ምስባክ፡- እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመፅዕ

        ወአምላክነሂ አያረምም

        እሳት ይነድድ ቅድሜሁ

ትርጉም፡- እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል

        አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም

        እሳት በፊቱ ይቃጠላል      መዝ ፵፱፥፪

 

- ይህ ሀይለ ቃል ለቀዳማዊውም ለዳግም ምፅዓቱም ይነገራል፡፡

- በቀዳማዊ ምፅዓቱ ግልጥ ሆኖ ይመጣል ሲል፤ በባህርዩ የማይታይ የማይዳሰስ ሲሆን ከእመቤታችን በነሣው ሥጋ የሚታይ የሚዳሰስ ሆኖ ምጣቱን ሲያጠይቅ ነው፡፡ እሳት ይነዳል ማለቱ አልመለስ ካሉ ፈርዶ የሚያጠፋበት ሥልጣኑ የባህርዩ መሆኑን ያሳያል፡፡ ማቴ 23

- ለደዳግም ምፅዓቱ ግልጥ ሆኖ ይመጣል ሲል፤ በክበበ ትስብዕት በግርማ መለኮት የሚመጣ መሆኑን ነው፡፡ ሲመጣም ሁሉ ተካክሎ ያየዋል፡፡ ላንዱ ቅርብ ላንዱ ሩቅ አይሆንም፡፡ አንዱ ከፊት ሌላው ከኋላ አንዱ ከቀኝ ሌላው ከግራ በኩል ሆኜ አየሁት አይልም ሁሉ በእኩል ርቀት ለሁሉ በፊታቸው ይታያቸዋል፡፡ ይህም ግርማ መለኮትን ወይም ምሉዕነቱን ያሳያል፡፡ ሲመጣም ጻድቃን ኃጥአን ፣ያመኑ ያላመኑ ሁለ ያዩታል፡፡

ዝምም አይልም ማለቱ ጻድቃንን ንዐ ኀቤየ(ወደኔ ኑ) ይጠራል፡፡ ኃጥአንን (ሑሩ እምኔን) ከእኔ ሂዱ ብሎ ሲያሰናብት ይሰማልና ነው፡፡ እሳት በፉቱ ይቀጣጠላል የተባለ ፍርዱ ነው፡፡

ወገኖቼ ክርስቶስ በእርግጥ ይመጣል፡፡ በእድሜያችን ላይ በቸርነቱ የሚጨመሩልን ቀናት ዕለተ ሞታችንን እንድንዘነጋ እንደሚያደርጉን፤ዕለተ ምፅዐትንም የወራት መበርከት የዘመናት መርዘም እንድንዘነጋው አድርጎናል፡፡ ህመም፣የዘመድ የወዳጅ መርዶ፣ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ዜና ሁሉ እኛ ብንረሳውም ሞት እንደማይረሳን ማስታወሻ እንደሆኑ ዳግመኛ ምፅዓቱን እንዳንዘነጋ የተተውልን ምልክቶች አሉ፡፡ እነሆ፤-

ወንጌል ዘማቴዎስ ፳፬፥ ፩-ፍፃሜ፡-  በዙህ ምዕራፍ የተጠቀሱትን ሁሉ ለማብራራት ጊዜ ያጥርብኛል፡፡ ዋና ዋናዎቹን አጠር አድርገን እንመልከት፡፡

ሐዋርያት በደብረዘይት ሁለት ዓበይት ጥያቄዎች ጠይቀውታል፡፡

፩. ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ብሎቸው ነበርና በዚያ አስደናቂ ቤተመቅደስ ላይ ይህ መቼ እንደሚፈፀም ማወቅ ፈልገው ነበር፡፡ ይህም በ70ዓ.ም በጥጦስ ዘመን ሆኗል፡፡ ጌታ በቤተመቅደሱ ላይ የተናገረው ፈጥኖ መድረሱ ላላውም በጊዜው ጊዜ መፈፀሙ የማይቀር መሆኑን ያስረግጣል፡፡

፪.ዳግመኛ መምጣቱ መቼ እንደሚሆን፡-

ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? ሐዋርያት በተለያየ ጊዜ ግለሰባዊ ጥያቄዎች እየጠየቁ ከጌታችን ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘታቸው በአሁኑ አጠያየቃቸው ላይ ጥንቃቄ ወስደዋል፡፡ አሁንም ግን “መቼ” የምትልውን ጥያቄ ጌታችን በተለመደው የማይመረመር ጥበቡ አልፏታል፡፡ ቀኑን ቆጥሮ ጊዜውን ሠፍሮ መናገሩ ፍጡራኑን ለሁከት ለጭንቀት ቢዳርግ እንጂ አይጠቅምምና፤አንድም እውነተኛ ወዳጅ ከአስመሳዩ(ከግብዙ) ይለይበታልና፤አንድም ሰው ከዕለተ ሞቱ ይልቅ ለዳግም ምፅዓቱ ትኩረት በመስጠት ከዕለቲቱ በብዙ ዘመናት የሚርቁት በኃጢአት ተዘፍቀው በበደል ተገርኝተው በሞቱ ነበር፡፡ በዳግም ምፅዓት ይዘን የምንቀርበው በሞታችን ጊዜ የነበረንን ነውና እንዳይጎዱ ቀኒቱን ሠወራት፡፡ ከሞት በኋላ ክፉም ሆነ በጎ ለመሥራት፤ጻድቅም ሆነ ኃጥዕ ለመሆን፤ለማመንም ሆነ ለመካድ አይቻልምና፡፡ማቴ 24፥36 

ከዚያ ይልቅ ጌታችን የወደደው ምልክቶቹን መንገር ነው፡፡ ምልክቶቹ በጥቅል ሲታዩ በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡

ሀ. ሥጋዊ መከራዎች፡- ረሃብ፣ቸነፈር፣ጦርነት፣የተፈጥሮ አደጋዎች፣መንግስት በመንግስት ሕዝብም በሕዝብ ላይ መነሣት ወዘተ…በሥጋ ላይ የሚመጡ መከራዎች ነገር ግን መንፈሳዊነትም ጭምር የሚፈተንባቸው ናቸው፡፡ የሆነው ሁሉ ሊሆን ግድ ነውና ከመማረር ይልቅ ቀናቱ እንዲያጥሩ መፀለይ፡፡ ሌሎች በመከራው ተማረው ከሃይማኖት እንዳይወጡ በክፉ ምግባር እንዳይለወጡ መምከር ማስተማር የመንፈሳዊነት መገለጫ ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ ምህረት፣በረሃብ ወቅት ተካፍሎ መብላት ፤በቸነፈር የሞት ጥላ ውስጥ መራራት በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ የታየና የሚጠበቅም ነው፡፡

ለ. መንፈሳዊ ውጊያዎችን ይህም ዲያቢሎስ የክርስቶስ የሆኑትን ርትዕት ከሆነችው መንገድ ለማውጣት የሚከፍተው ነው፡፡ በዋናነት ከተጠቀሱት “እኔ ክርስቶስ ነኝ” እያለ በስሙ የሚመጡ እንዳሉና ሀሰተኞችም ነቢያትና መምህራንም እንደሚነሱ የተናገረው ነው፡፡ ይህም በየዘመናቱ ተፈፅሟል፡፡ ዛሬም አለ ነገ ይብስ ይመጣል፡፡ የዛሬ መልካምነቱ ከነገ የተሻለ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የሚብስውን መጠበቅ ማስተዋል ነው፡፡ መጽሀፍ ቢቻላቸው “የተመረጡትን እስኪያስቱ ድረስ” ማለቱ ስህተቱ ምን ያህል በከፋ ደረጃ እንደሚመጣ ያሳያል፡፡

ነገር ከመራን ዘንድ ዛሬም በአዱስ አበባ ሀሰተኞች መምህራን ነቢዩ ኤልያስ መጥቷል እያሉ ህዝቡን ማደናገራቸው የዚሁ እውነታ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ብቻውን ሳይሆን ከነቢዩ ሄኖክ ጋር እንደሚመጣ በኢየሩሳሌም አንደሚገለጡ ከሐሳዊው መሲህም ጋር ብርቱ ትግል አድርገውና ሀሰተኛነቱን ገልጠው ሕዝበ እግዚአብሔርን ካፅናኑ በኋላ በሰማዕትነት እንደሚሞቱ እናምናለን፡፡ ራዕይ 11፥1-13

ዛሬ መጥቷል የሚሉ ሀሰተኞች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን በቀላሉ ለማግኘት ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦችን ተጠቅመዋል፡፡ ነገ በሥጋ የሚጠብቃቸው ኃፍረት በነፍስ የሚያገኛቸው ሞት እያስጨነቀን ነብዩ ኤልያስ በእንዱህ ዓይነት ሁኔታ ይልቁም በአዱስ አበባ እንደማይመጣ ለመናገር የምናውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያሰገድደናል፡፡

ስለ ስሙ የተጠላን እንደምንሆንም ሌላ ምልክት ተሰጥቶናል፡፡ ማንም ሰው መጠላትን አይፈልግም፡፡መጠላት መገፋት፣ የመገለል፣ ያለመፈለግ፣ የብቸኝነት፣ ስሜት ውስጥ ስለሚከተን በራሳችን እርግጠኞች ወዳለመሆንም ጭምር ይወስደናል፡፡ ይህ ደግሞ ተስፋ ወደመቁረጥ ራስን ወደመጥላት ወይም በአንፃሩ ሌሎችን ወደመጥላትና ወደ መበቀል ይወስደናል ውጤቱም የከፋ ነው፡፡

እነሆ የክርስትና በረከት በዚህች ዓለም የክርስቶስ ተከታይ መሆን የሚያተርፍልን ነገር ቢኖር መገፋትን፤ መገረፍን፤ በወኅኒ መጣልን፣ በሰይፍ ተመትሮ በእሳት ተቃጥሎ መሞትን ወዘተ…ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የሚጠብቃቸው በረከት ይሄ ነው፡፡ ክርስቲያኖች በዚህ አልፈዋል፤ እኛም ክርስቲያኖች ከሆን በዚህ ማለፍ የሚጠበቅ እውነታ ነው፡፡ ወዳጄ ሆይ! ክርስቲያን በመሆንህ በዚህ ዓለም የምትጠብቀው ምንድር ነው? የተደላደለ ህይወት፣ ከበሬታ ሥፍራ፣ ከሁሉ በላይ መሆን…ምን? ፡፡ ከስህተት ተጠበቁ! ከክርስቶስ ጋር ቃልኪዲን ያደረግነው በክብር ሳይሆን በውርደት፣ በድሎት ያይደለ በመከራ፤ በመወደድ ሳይሆን በመጠላት፣ በህይወት ለመቆየት ያይደለ ስለ እውነት ለመሞት በተኩላዎች መካከል እንደበጎች ልንኖር ነው፡፡

ይህን የምንናገረው ያልመጣን መከራ ለመጥራት ሳይሆን ሲመጣ ክርስቶስ እንዴት ይህን ይፈቅዳል? ብለን እንዳንሰናከል ለማፅናት ነው፡፡ እርሱ የሆነውን አስቡ፤ እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርሱን አዝላ በውሃ ጥምና፣ በረሃብ፤ በወንበዴዎችና በወታደሮች ፍርሃት የደረሰባትን አስቡ፡፡ ሐዋርያት ነቢያት ጻድቃን ሰማዕታት ካህናት መነኮሳት የደረሰባቸውን አስቡ፡፡ የእነርሱ ወገኖች ከሆን በእነርሱ የደረሰ ይደርስብናል፡፡ ዮሐ 15፥18-24፣ዮሐ 16፥33 ማቴ10፥16-23፣ሮማ8፥35-36፤ 1ቆሮ4፥11-13 

- ሌላው የተሰጠው ምልክት "ለአሕዛብ ምስክር ይሆን ዘንድ ይህ የመንግስት ወንጌሌ በአለም ሁሉ ይሰበካል" የሚል ነው፡፡

 ወንጌል ስለሁለት ምክንያት ይሰበካል፡፡ ለጽድቅና ለፍርድ አምነው ለሚጠቀሙበት በቃሉ ለሚኖሩ በወንጌል የዘላለም ህይወትን እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው፡፡ በአንጻሩ ለራሳቸው ፍልስፍና የሚመቻቸውን ሃሳብ ለመምረጥ፤ ለዓለማዊ ድርሰታቸው ወግ ማሳመሪያ ቃላትንና ይትበሃሎችን ለመቃረም የሚነቅፈበትን ነገር ለማግኘት ወይም ልባቸውን ሳይከፍቱ በቸልታ የሚያነቡ ሁሉ ለፍርድ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ያነባሉ፡፡  ሳይኖሩበትም ላይኖሩበትም በአጋጣሚ በወንጌል ላይ የተሾሙም ሁሉ ለፍርድ ያነቡታል፡፡

አህዛብ የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ይፈታል፡፡ የተለያየ ቋንቋ የሆኑትን ሕዝብ ሲያበዛው (plural) እና በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ያላመኑ አረማውያንን (ኢ-ጥሙቃንን) አህዛብ ይላቸዋል፡፡ ዛሬ አብዛኛው ማህበረሰብ ሙስሊም (ኢ-ጥሙቅ) በሆነባቸው አገሮች እንኳ ወንጌል በራሳቸው ሼኮች እየተሰበከ ነው፡፡ መድረሳዎቻቸው የቁርዓን መቅሪያ ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጭምር ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡  ለዚህ ደግሞ ጉልህ ማስረጃ የሚሆኑን እንደ ዛኪር ናይክ እና አህመድ ዲዳት ያሉት የማያውቁት አገረ ገብተው የሚዛብሩ የዲያብሎስ መልዕክተኞች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ካለው EBS TV ጀምሮ በዓለም ባላቸው ቻናሎች ሁሉ ለተከታተለ ሰው ዛሬ የሚሰብኩት ከመሀመድ ይልቅ ክርስቶስን ከቁርዓን ይልቅ መጽፈፍ ቅዱስን ነው፡፡ ምንም እንኳ በአሉታዊ መልኩ ሊያቀርቡት ቢሞክሩም ትንቢቱ ግን ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አንድ ቀን እውነቱ ግልጽ ይሆናል መስቀል በጨረቃ ላይ ይቆማል ለእስማኤሌም ወንጌሌ ይሰበካል! እንፀልያለን !!! ያ ህዝብ ነጻ እንዲወጣና በጨለማ በጨረቃ ብርሃን በድንግዝግዝ ከሚያይ አጥርቶ ወደሚያይበት ወደ እውተኛው የጽድቅ ፀሐይ ብርሃን እንዲመጣ አንፀልያለን ኮከቡ እየማራ ቤተልሔም እንዲያደርሳቸውና ህፃኑን አሳይቶ ድንጋይ ማምለክን እንዲያስረሳቸው፡፡ አሜን! ለይኩን ለይኩን!

- በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ "ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ያልሆነ መከራ እንደሚሆን ካሳሰበ በኋላ ቀኖቹ ግን ስለተመረጡ ሰዎች ሲባል ያጥራሉ፡፡ ያ ባይሆንስ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር” በማለት የመከራውን ጽናት ገልጾታል፡፡ ያለ ተስፋ ግን አልተወንም ቅዱስ እግዚአብሔር ለመንግስቱ በልጁ ደም ስለዋጃቸው በእውነትና በመንፈስ ስለሚገዘት ቅደሳን ሲል ቀኖቹን ያሳጥራቸዋል፡፡

ዱያብሎስ ዛሬ እንኳን ለወንጌሌ ቸልተኞች የሆኑትን ቀርቶ በመንፈሳዊ ህይወት በመጋደል ላይ ያሉትን እንኳን በረቂቅ ስጋዊ ወጥመዶች ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ዝና ወዘተ . . . እየሳበ ንቀው ጠልተውት ወደ ተውት አለም መልሷቸዋል፡፡

የንጽህናና የቅድስና ህይወት በተለያዩ የማስመሰያ ምክንያቶች ተሸራሽሯል፡፡ ምላስ ጸድቃ ነፍስ ረክሳለች፡፡ አባቶቻችን የነፍሳቸው ቅድስናና ክብር ለሥጋቸው የሥጋቸው ለልብሳቸው፣ ለመቋሚያቸው ወዘተ . . . ተረፈ ፡፡ እነሱ ከክፉው ሠራዊት ጋር ላለባቸው ሰልፍ የለበሱት ልብስ እኛ በከንቱ ለመሞገስ ለበስነው፡፡ ልብሱ በእነሱ ከበረ እኛ በልብሱ ተከበርን፡፡ 

ይህ ሁለ ተንኮል ዱያብሎስ የመከራ ዘመን እንዲያጥር ምክንያት የሚሆኑ ምርጦች እንዳይኖሩ ለማድረግ ነው፡፡ ቅዱሳን ዋዕየ መከራን የሚከልሉ ደመናዎች፤ የደከመ ጉልበት የሚያፀኑ ምርኩዝች ናቸውና፡፡ ያለ ቅዱሳን ይህቺን ዓለምና የእኛን ህይወት ማሰብ ከባድ ነው፡፡ በከተማይቱ አስር ጻድቃን ቢኖሩ እምራለሁ ያለ እርሱ በፊቱ የሚቆም ከጠፊ  ሊሆን የሚችለውን መከራ በሰው አእምሮ ከመታሰብ በላይ ነው፡፡ ሰዶምና ገሞራን ይዘክሯል፡፡ ታላቁ ተስፋችን የአምላካችን ቸርነቱና የቅዱሳን ፀሎት ነው፡፡

የሥጋ ፈተና ይፈፀማል የምድርም ሥርዓት ያልፋል፡፡ ጠላቶቹ በዘላለም ጉስቁልና የሚኖሩበት የገሃነም ጨለማ ይገለጣል፡፡ ወዲጆቹ እንደተስፋ ቃሉ የጠበቋት የበጉ ከተማ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት በክብር ትታያለች፡፡የልባቸው ናፍቆት የነፍሳቸው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኔ ኑ ብሎ ሲጠራቸው ለዘላለም ደስታ ወደ ከተማይቱ ይገባሉ፡፡ ከእኔ ሂዱ የተባሉ ኃጥአንም ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይወርዲሉ፡፡ ምልጃ የለም ልመናም የለም መስዋዕት መሠዋት በንስሐም መማለል የለም፡፡“ አልቦ ምህረት በጊዜ ፍትህ” እንዱል ምህረት ይከለከላልና፡፡

 በገሃነም ያለውን ሥቃይ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት የሚፈሰውንም ደስታ መግለጥ የሚቻለው አንደበት የለም በጊዜው ጊዜ ሲገለጥ ከማየት በቀር ፡፡ማቴ 25፥31-46፣ ራዕይ 8፥13-17እና ራዕይ21፥1-4

በምድር ያለ ግፍ ጢሱ ያፈናቸው፤ የኃጢአት ክርፋት የገለማቸው ጊዜያቸው እስኪደርስ በዚህ የበደል ዓለም እንዲኖሩ ግድ የሆነባቸው ቅዱሳን ያቺን ዓለም ይናፍቃሉ፡፡

ሐዋርያት አዕማዶቿ አበው ደጀፎቿ አማናዊው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሷና ብርሃኗ የሆነችውን፤ ጽድቅና እውነት ብቻ የሚፈፀምባት የአምላካቸው ድንኳኑ የሚተከልባት ዙፋኑ የሚዘረጋባትን ብርህት ዓለም ይናፍቃሉ፡፡ ዛሬ ከሩቅ ያዩአታል ይሳለሟታል በመዓዛዋ ተመስጠው በናፍቆቷ አንብተው ዓለምን ይንቁባታል፡ ይቃትታሉ፣ ይጮሃሉ፣ ይጣራሉ "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!" እያሉ፡፡ ራዕይ 21፥9-14 ፣ ራዕይ 22፥20 ፣ 1ቆሮ 16፥22

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

2008 ዓ.ም

 

 

1 comment

  • selamawit dejene
    selamawit dejene Wednesday, 04 January 2017 12:31 Comment Link

    kesis egziabher yibarkot betam des yilal

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.

back to top

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ