ዐቢይ ፆም
Featured
፫. ምኩራብ፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ወደ ምኩራብ አይሁድ ገብቶ ገበያውን እንደፈታ በቤተክርስቲያን የምናስታውስብት ነው፡፡
ምስባክ-እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዓኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕለየ
ወቀዳዕክዋ በጾም ለነፍስየ
ትርጉም፤-የቤትህ ቅንዐት እንደ አሳት በላኝ
አንተን የተገዳደሩህ ተግዳሮት በእኔ ላይ ደረሰ
ነፍሴን በፆም ቀጣኋት መዝ ፷፰፥፱
ለጊዜው ለይሁዳ መቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው፡፡ በመቃቢስ ጊዜ አንጥያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ መከበርና መቀደስ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማያሰጉት ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡ ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑ ሥፍራዎች(ቤተመቅደስ) ታቦታት፣ንዋያተ ቅዱሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው፡፡ መጽሐፈ መቃብያን፣ትን.ዳን 5፥1-ፍፃሜ፣ መዝ104(5)፥14-15፣ ዘኁ 12፥1ፍፃሜ፣ማቴ 10፥40፤1ሳሙ 4-6
በክርስትና ስንኖር መጠንቀቅ ያለብን ልዑል አምላክ በሠራልን ሕግና ሥርዓት ለመሔድ ነው፡፡ እኛ ሕግ ሐጋጊዎች ሥርዓተ ደንጋጊዎች አይደለንም፡፡ በቤተክርስቲያንም ከሰው የሆነ ሥርዓት የለም፡፡ በጥምቀቱ በቁርባኑ በቅዳሴው በማሕሌቱ በጸሎት በፆም በበዓል አከባበር ሥርዓቱ ሁሉ በጥንቃቄ መጓዜ እንጂ "ምናለበት" በሚል የቸልታ መንፈስ፣ወይም በራስ ሕግ መመራት ከጸጋው ይለያል በመቅሠፍት ያስጎበኛል፡፡ ለመሆኑ ራስህ በሠራኸው ሕግና ሥርዓት በቤተእግዚአብሔር ልኑር የምትል አንተ ማነህ? ይህን ሥርዓት ለቤቱ ከሠራ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትወዳደር ዘንድስ ምንደር ነህ? የአባቶቻችን ህግና ሥርዓት የምትንቅስ ከእነርሱ የተሻልክ ሆነህ ተገኝተህ ነውን? እንደ እውነቱ የራስህን እንኳ ህይወት በህግና በሥርዓት መምራት ያልቻልክ፤እፈፅመዋለሁ ብለህ ቃል የገባኸውን ለመፈፀም በምክንያት ልምሾ ሆነህ የታሠርክ አንተ እንደምን የእግዚአብሔርን ቤት ህግ ለመተቸት የተሻለ ህግም ለማውጣት ትደፍራለህ?
የቤቱ፣የሥርዓቱ፣የአምልኮቱ፣የቅዱሳኑ፣ቅንዓት እንደ እሳት በሚበላው በሠራዊት ጌታ ፊት ድርሻህን እወቅ፡፡ ደርሻህ በተደነገገልህ ህግ በተሠራልህ ሥርዓት ፀንተህ መኖር ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግዳሮት ነው፡፡ አመድና ትቢያ መሆንህን አስብ!!
ሥጋ የነፍስ መሣሪያ ነው፡፡ መልካምም ክፉም ትፈፅምበታለች፡፡ ነፍስ ከተለየቸው ሥጋ ሀዘን፣ደስታ፣ፀፀት፣ህመም፣ሀፍረት፣ትዕቢት ሌላም ሌላም ስሜቶች አይኖሩትም በድን ነው፡፡ ሥጋ ሲጦም ረሃብ ሲሠማ ስሜቱን ነፍስና ሥጋ ይጋሩታል፡፡ ዳዊት ነፍሴን በፆም አስመረርኳት(ቀጣኋት) ያለው ለዚህ ነው፡፡ አስተውል ነቢዩ ፆምን ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አልሠጠም መሪዋ አንቀሳቃሿ ተጠቃሚዋ እርሷ ናትና፡፡ ነፍስ አልቦ ፆም የለም፡፡ ስለዚህ በፆም ነፍሳችንን እንቅጣ እንጂ በዓለም ድንቃ ድንቅ፣በወዘበሬታ፣በሥራ በመወጠር የረሃብ ስሜታችንን ለማጥፋት(ለመርሳት)አንሞክር፡፡ እኛ የረሳነውን(ትኩረት የነፈግነውን) እርሱ ይቀበል ዘንድ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ተረቱስ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይሸከመውም አይደል፡፡ ከረሃብ ስሜታችን ጋር በመቆየት ፆማችንን ማስባረክ ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡
ወንጌል ዮሐንስ ም፪፥፲፪—፳፭
ጌታ ኢየሱስ ራሱን ከገለጠ በኋላ ወደኢየሩሳሌም ሲወጣ የመጀመርያው ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ከቤተመቅደስ አስወጥቷቸዋል ሁለቴም ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ቀንና በዕለተ ሆሣዕና በቤተመቅደሱ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሰዱቃውያን ብዙ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚዎች ስለነበሩ ድርጊቱን ከመቃወም ይልቅ ያበረታቱ ነበር፡፡ የአንድ አገር መንግስት በሌላ አገር ግዛት ውስጥ የዜጎቹን ደኅንነት የሚከታተልበት ጉዳያቸውን የሚከታተልበት ወደራሱ አገር ለሚገቡ ሌሎች ዜጎች ፈቃድ የሚሠጥበት(ቪዛ) ቆንስላ(Embassy) እንደሚኖረው፤ቤተመቅደስም የሰዎች ነፃ ፈቃድ በሰለጠነበት ዓለም የምትገኝ የሰማያዊው መንግስት ቆንስላ(Embassy) ናት፡፡ የዜጎቿን መንፈሳዊ ድኅነት በጸሎት በትምህርት በመከራ ትጠብቃለች፤ አዲስ ለሚመጡት በጥምቀት የሰማያዊ ዜግነት ፈቃድ ትሠጣለች፡፡ ይህንንም በባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴዎች ካህናት ታስፈፅማለች፡፡ የቤተመቅደስም የካህናትም አገልግሎት ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ከወጣ ቤተመቅድሱንም በአሠራር ቅርፁ ብቻ ካህናቱንም በአለባበስ ካህናት ለማለት ይቸግረናል። በአውሮፓ በአሜሪካ ወደሙዝየምነት የተቀየሩ አብያተ መቅደሶች አንዳሉ እንሰማለን በአሠራር ቅርፃቸው ብቻ ግን አሁንም ቤተመቅደስ ብለን አንጠራቸውም፡፡ በትያትር በፊልም ካህናት መስለው የክህነት ልብስ ለብሰው የተወኑትም የእውነት ካህናት ናቸው ብለን አንወስድም የታላቁ ሰማዕት የአቡነ ጴጥሮስ ተውኔት አብራር አብዶ(ሙስሊም) መተወኑን የምናሰወታውሰው ነው፡፡ ስለዚህ ቤተመቅደስና ክህነት የይዘት አንጂ የቅርፅ የውስጥ እንጂ የአፍኣ አይደለም፡፡
ጌታ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት በመፈፀም ቤተመቅደሱን ሊያጠራው ወደ ዓላማው ሊመልሰው ፈቃደ ተቀባይ ስላላገኘ የተፈታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ጌታ ቤተመቅደሱን በተደጋጋሚ “ያባቴ ቤት” ብሎ ይጠራው ነበር በመጨረሻ ግን እሱን ባለማመን አምጸው ሲፀኑ “ቤታችሁ” ብሎታል፡፡ ክርስቶስ የሌለበት የእግዙአብሔር መቅደስ የለምና፡፡ሉቃ19፣ ማቴ 23፤ አንድም
በቤተመቅደሱ የነበሩት እንስሳት ለተለያየ ዓይነት መሥዋዕት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡ የአዲስኪዳን መሥዋዕት እና ሊቀካህናት የሆነው መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተመቅደሱ እንስሳቱንና ርግቦችን ማስወጣቱ መሥዋዕተ ኦሪት መሻሯን፤ ካህናተ ብሉይን መቃወሙም ለአዲስ ስርዓት የአዲስ ኪዳን ካህናት ይሾም ዘንድ እንዳለው ያጠይቃል፡፡
በዚህ ወቅት ጌታ የተጠየቀው ይህን ለማድረግ ስላለው ሥልጣን ምልክት እንዲያሳይ ነበር፡፡ እርሱም ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን አነሣዋለሁ ብሏቸዋል፡፡ አስተውል እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ፡፡ በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ፡፡ (የትንሣኤውን ምስጢር በጊዜው ጊዜ እናመጣዋለን)
በገለጠው ቃል ውስጥ ግን የሰውን አካል እንዴት ባለ ክብር እንዳከበረው አስታወቀ ቅዱስ እግዚአብሔር ቃሉን ከድንጋይ ድላት ይልቅ በልባችን ላይ ሊጽፍ፤በሸራ ድንኳንም ሆነ በድንጋይ፣በዕብነበረድ፣ በወርቅ፣ ከሚሠራ ቤተመቅደስም ከምናመልከው ይልቅ በሰውነታችን መቅደስ ብናከብረው ይወዳል፡፡
አባቶቻችን ወደ ሲና ተራራ ወጥተው ቃሉን የሕዝቡ ልብ አምሳል በሆነው በድንጋይ ድላት ይዘው ወረዱ፤በአዲስ ኪዳን ወደ ቀራንዮ ተራራ ወጥተን ቃሉን ፍቅሩን ቃልኪዳኑን በልባችን ጽላት ተሸክመን ወረድን፡፡
በተለያየ ዘመን የተሠሩት ቤተ መቅደሶች የመፍረስ ግዳጅ ደረሠባቸው፡፡ አሁን ግን ክፉዎች ደርሰው ሊያፈርሱት በማይችሉት መቅደስ ላይ ይመለክ ዘንድ የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይኸውም የምዕመናን ሰውነት ነው፡፡ የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕያው ቤተመቅደስ የሰው ልጅ፡፡
በዚህች ዕለት ቤተክርስቲያን ልጆቿን ራሳቸውን ህያውና ቅዱስ መሥዋዕት፣ዘላለማዊ መቅደስ አድርገው እንዲያቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ ትለምናለች፡፡ በእንዴት ያለ ክብር እንዳከበረን አስተውሉ፡፡ የኃያሉ ንጉስ የዘላለማዊው አምላክ መቅደስ የቅዱስ መንፈሱም ማደርያ እንሆን ዘንድ የተመረጥን እኛ ማን ነን? ከልባችን ከሕሊናችን ከሥጋችን ላይ የዓለምን ሸቀጥ ማራገፍ ዛሬ ይጠበቅብናል፡፡
ሥጋችን በክርስቶስ መዓዛ ከብሯል፣በቅዱስ ቅባቱ ወዝቷል፣ በንፅህና ልብስ አጊጧልና ሌላ አያስፈልገውም። ንፅኅናህን ባለመጠበቅ ግን ለሰዎች ምሬት ሁን እያልን አይደለም በፈቲው ጦር ሌሎችን ወግቶ ለመጣል ሁሉን ወደራስ ስቦ ለመደነቅ የተዘጋጀ መንፈስህን ለማውገዝ እንጂ፡፡ የነፍስ ክርፋት በሽቶ፤የሥጋ ርኩሰት በልብስ አይሠወርምና፡፡