Login
Main menu

Items filtered by date: June 2026

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ሁለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

          ባለፈዉ ትምህርታችን የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው ከዘላለም እስከ ዘላለም ህያው የሆነ አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል' በይቀጥላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውነታ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እናያለን፡፡

ሁሉን ቻይ :- ማለት እንዳሰበ የሚሠራ እንደፈቀደም የሚያከናዉን& ለሥራው ረዳት አጋዥ    አማካሪ የማይሻ& ሁሉን ከባህርይ የሚያከናውን& በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች በሁሉ የሚሠራ& በሁሉ የሚያዝ በሁሉ ላይ የሠለጠነ &ማንም ማን ለምን ይህን ታደርጋለህ ብሎ ሊከለክለዉ ሊያግደው ሊያስቆመው የማይቻል& በአጠቃላይ ይበልጥ ገላጭ በሆነ ቃል "የሚሳነው ነገር የሌለ" ማለት ነው፡፡ ጥያቄዉ ሁሉን ቻይ የሚለው የአምላካዊ ባህርይ መገላጫ ቅፅል ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋል ወይ? የሚል ነው፡፡ የኦርቶደክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም መልስ እንዴታ ይገባል ነው!!!

ማስረጃ

ትን.ኢሳ 9*6 ህፃን ተወልዶልናልና……ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት                  የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ኃያል አምላክ የሚለው ቃል የተወለደው በሥጋ የተገለጠው እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን የሚያስረግጥ ነው፡፡

ዮሐ 1*3 ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡

          በዚህ ቃልም በቅደምና የነበረው ቃል በኋለኛው ዘመን ሥጋን የተዋሃደው ቃል ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ያስገኘ ምንም ምን ያለእርሱ የሆነ እንደሌለ የሚያስረዳ ነው፡፡

ቆላ 1*15 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትንና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፡፡ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፡፡

የማይታ አምላክ ምላሌ ሲል አምላክ አይደለም ማለቱ አይደለም፡፡ "በሰው ምሳሌ ሆኖ" ሲል ሰው አልሆነም ለማለት እንዳለሆነ ሁሉ ፊል 2*6-8 ሁሉ በእርሱ እንደተገኘ ለእርሱ ክብርም እንደተፈጠረ በመግለጥ ሁሉን ቻይነቱን መሠከረ፡፡

      ፅንስቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ

       ምድር ያለ ዘር ሴት ያለወንድ ትፀንስ ዘንድ ሕገ-ተፈጥሮ አይፍቅድም፡፡ ሁሉ የተገኝ በዚሁ የተፈጥሮ ሥርዓት አልፎ ነው፡፡ የጌታ ፅንት ግን እንዲህ አይደለም ወንጌላዊው ማቴዎስ" ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች" እንዳለ የጌታ ፅንስ ከሦስት ግብራት ንፁህ ነው፡፡ ይኸውም ዘር&ሩካቤ&ሰስሎተ ድንግልና ነው፡፡ጌታችን ሲፀነስ ሩካቤ አልተፈፀም፡ዘርዐ ብእሲ አላስፈለገም የእመቤታችን ድንግልናም አልተለወጠም፡፡ በዚህ እውነትም የተወለደልን ህፃን ኃያል አምላክ ወይም ሁሉን ቻይ መሆኑን ገለጠልን፡፡       ማቴ 1*18-25 & ሉቃ 1*26-56

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ

      የጌታ ልደቱ እንደ ፅንሠቱ ሁሉ ልዩ ነው በልደቱ የእናቱን ድንግልና አልለወጠውም ምጥ ጭንቅ አላገኛትም፡፡ ሰው በር ከፍቶ ወጥቶ ከኋላዉ እንዲዘጋዉ የእርሱ ልደት እንዲህ አይደለም ማኅተመ ድንግልናዋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳን አልተለወጠም ይህ እንዴት ይሆናል? ለሚል

-ጌታ በተዘጋ ቤት ጣርያ ሳይነቅል ግድግዳ ሳያፈርስ መሠረት ሳየቆፍር በር መስኮት ሳይከፍት እንዴት ከሐዋርያት መካከል እንደተገኘ ይመርምር፡፡ ሉቃ 24

ትን.ሕዝ 44*1-3 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አምጣኝ ተዘግቶም ነበር እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡

             ምሥራቅ እመቤታችን የእውነተኛዉ ፀሐይ መውጫ ናትና& መቅደሰ የማኅፀንዋ 9ወር ከ5ቀን ተመስግኖበታልና& በር የማኅተመ ድንግልናዋ ተዘግቶ ይኖራል ማለቱ ለዘላለም እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ ፀንታ መኖርሯን ሲገልጥ ነው፡፡

መዝ.ዳዊ 146*1-2 ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ጽዮንም ሆይ ለአምላክሽ እልል በይ የደጆችሽን መወርመርያ አፅንቷልና፡፡ /በዚህ ጥቀስ ኢየሩሳሌም ጽዮን የተባለች እመቤታችን የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና& የደጆችሽ መወርወርያ የተባለ ማኀተመ ድንግልናዋ ነው አፅንቶ እንደሚጠብቀው ግልጽ ሆኗል፡፡

ኢሳ 66*7 ሳታምጥ ወለደች* ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጀን ወለደች ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶአል?

የህፃንነት እድሜው

           በተዐምረ ኢየሱስና በተለያዩ የቤ/ክ መፃህፍት እንደተገለጠው ጌታ በህፃንነቱ ይፈፅማቸው የነበሩ ተዐምራቶች ሁሉን ቻይ አምላክ ለመሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ከሩቅ ምሥራቅ የመጡትን የጥበብ ሰዋች በኮከብ መምራቱ ሊቃውንትን በሚጠይቀው ጥያቄና በሚሠጠው መልስ ማስደመሙ በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሥልጣን እውቀቱም የባህርይ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይቆየን!

                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                                    ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

                                    ጥቅምት 2005ዓ.ም

Read more...

ሰቆቃወ አርድእት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

‹‹ሰቆቃወ አርድእት››

ዙሪያችን ለመስበር በሚያስፈራ ዝምታ ታጥሯል፡፡ ሁሉም ሲያየው ባደረውና በዋለው ትዕይንት ልቡናው ተቧጦ መንፈሱ ደቆ ሰው በመሆኑ ሳይቀር ተሳቆ በየጥጋጥጉ ተቆራምዷል፡፡ በዚያች ጠባብ ክፍል የተቀመጠ ሁሉ ብቸኛ ነው፡፡ማንም ማንንም ለማዋራት ለማፅናናትም ሆነ ሰቆቃውን ለመጋራት አቅም አልነበረውም ፡፡አልፎ አልፎ ከደረቀ ማንቁርት የሚወጣ ሳግ፤ በስቃይ ከተመታ ልብ የሚገነፍል ትንፋሽ ይሰማል፡፡

የሚያፅናና፣ የሚያበረታታ፣የሚመክር፣ አይዟችሁ የሚል የለም፡፡ ፍርሃት ከቦናል ጨለማ ወድቆብናል፡፡ነፍሳችንን ሀዘን እንደመቃብር ተስፋ መቁረጥም እንደ መርግ ተጭኗታል፡፡

ያ ቃል ነፍስን ከዓለም አሳብ ለይቶ እንደ ንስር የሚያመጥቃት፤ ያ ድምፅ ልብን በሀሴት አስክሮ ከሰማያት ደጃፍ የሚያደርሳት፤ ያ ርኅራኄ በኃጢአት የደቀቀችን ዝንቦች በጭካኔ እንደወረሩት ገጣባ ጀርባ አጋንንት የተቀራመቷትን ሰውነት የሚያሳርፋት፤ ዛሬ ካጠገባችን ርቋል፡፡

አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ፣ እወዳለሁ ንፃ. . .፣እምነትሽ አድኖሻል. . .፣እኔም አልፈርድብሽም. . .፣ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል በሰላም ሒጂ. . .፣ ዛሬ በዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል . . .የሚሉት ከአድማስ ደንጊያ የበረቱ ቃላት ትዝታቸው ብቻ ቀርቶልናል፡፡

በርጅና ምክንያት አጥንትና ጅማት ብቻ የቀራቸውን እግሮቼን ካጠፍኩበት ለመዘርጋት ስታገል አንድ ሰው ቀስ ብሎ ረዳኝ፡፡ የልብሱ ሽታ ነፍሴ የለመደችውን መዓዛ ስላስታወሰኝ እርጅና የተጫነው ሰውነቴ በሀዘን ተርገፈገፈ::ዕንባዬ ወደ ውስጤ ሰርጎ አንጀቴን ሲያቃጥለው ተሰማኝ፡፡ ዋ! ለካስ ለሚወዱት ለማዘንም(በዕንባ ዘለላዎች ፍቅርን ለመግለፅም) አቅም ያንሳል፡፡

ከነፍሴ ጥልቅ ጮኽኩ፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም ሊሰማው የማይችል ዋይታዬን፤ የሰው ጭካኔ ካስደነገጣት ነፍሴ የተጨመቀ ሰቆቃዬን ወደ አርያም ላክሁ፡፡

እረኛችን ሆይ! መንጋህ እኮ ተበተነ፡፡ በአንዲት ቀን ብትለየን ውስጣችን በሀዘን ከሰሎ ነፍሳችን በተስፋ መቁረጥ ቆስሎ እንግዳ በሆንባት ምድር እንደ ሽኮኮ በፈረሰ ግንብ ውስጥ ተቅበዝብዘን፡፡ ነፍሴ የወደደችህ ሆይ ንገረኝ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ከድንጋጤ የተነሳ ልቤ በውስጤ እንደ ሰም ቀለጠ ጉልበቶቼ ሁሉ ደከሙ፡፡ ነፍሴ እንደ ምድረ በዳ ተጠማችህ፡፡ አቤቱ እረኛዬ ሆይ! የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፡፡

ውጋት የሚያሰቃየው ደረቴ በአንድ እጄ ደግፌ ጉልበቶቼን ለመዘርጋት የረዳኝን ሰው ለማየት ከተደገፍኩበት ቀና አልኩ፡፡ አልባሌ ልብስ የለበሰ ሰው እንዳልሆነ ስዳስሰው ታውቆኛል፡፡ የክፍሉ ብርሃን ማነስና እርጅና የተጫነው ዓይኔ ማን መሆኑን ለመለየት ግን አላስቻሉኝ፡፡ማን መሆኑን ለማወቅ መጓጓቴን ስላወቀ ክፍሉ ጠርዝ ጋር የነበረውን መቅረዝ አምጥቶ አጠገባችን አኖረው፡፡አፌን ብከፍትም ቃል ማውጣት ግን አልተቻለኝም፡፡ ሁኔታዬን ስለተረዳ‹‹አባባ ናታን እኔ ነኝ የቀን ቀን ፈሪሳዊ የሌሊት ክርስቶሳዊ የሆንኩት እኔ ኒቆዲሞስ ነኝ›› አለኝ፡፡

የለበሰውን የፈሪሳውያንና የአይሁድ መምህራን ካባ ስመለከት በዚህች የታወቀች ዕለት ይህ የለበሱ ሁሉ ይፈፅሙት የነበረው ጭካኔ የእንባዬን ቀላይ ነደለው፡፡ አጥንታቸው ብቻ በቀረ ጉንጮቼ ላይ እየወረዱ ፂሜ ውስጥ ሰርገው ቀሩ በልቅሶ የሚርገፈገፍ ሰውነቴን ለማስከን ኒቆዲሞስ ትከሻዬን ጫን አድርጎ ያዘኝ በደከመ ድምፅ ‹‹ ግን ለምን. . .? ያ ሁሉ ጭካኔ ያ ሁሉ መጠን ያለፈ ጥላቻ፤ ግን ለምን. . .?በንፁሑ ላይ፡፡ ግፋቸው እየጨመረ ሲሄድ የገዛ ጭካኔያቸው ሲያስፈራቸው ጥላቻቸውን ለመሸከም ሲከብዳቸው አይቻለሁ፡፡ አባባ ናታን ‹‹ክፋት መንስዔን ጥላቻም ምክንያት አይሻም፡፡የዚህን ዓለም ጠባይዕ መመርመር አሰቻጋሪ ነው፡፡ ፍቅሩም ሆነ ጥላቻው ከእውነት ይልቅ ስሜትን የሚከተል ነው፡፡ ከሚስቀው ጋር ለመሳቅ፣ ከሚያለቅሰውም ጋር ለማንባት፣ከሚጮኸው ጋር ጮኸን ከሚፈርደው ጋር ለመፍረድ ርትዕ አያስፈልገንም፡፡ በቁጥር መብለጥ ጩኸት ማብዛት ብቻ በቂ ነው፡፡ይልቁንም የአድማውን መለከት የነፉት የአመፁን ችቦ የለኮሱት በሥልጣን ወንበር የተቀመጡ በብልጥግና የቀበጡ በሽበት የተጌጡ የሕዝብ አውራዎች ከሆኑ እውነትን ለመርገጥ ፍትህን ለመደፍጠጥ ቀላል ነው፡፡

በዚህ ሰዓት በፍርድ ወንበር የተቀመጠው ማስተዋሉን ፣ መርማሪም ጥበቡን ይደብቃል፡፡ የገዘፈውን ለማየት የጎላውን ለመስማት አቅም አይኖረውም፡፡በሁከት መካከል የዝምታን ምሥጢር መለየት፣ ከአድመኞች ወጥመድ እውነትን ማውጣት ከጨካኞች ጉያ ፍትህን ነፃ ማውጣት እስከ ዛሬ ወደ ምድር የወረደውን የዝናብ ነጠብጣብ የመቁጠር ያክል የማይሞከር ነው፡፡

የገዛ ወገኖቹ ይዞ የመጣውን ፍቅር ሊያክል ትንሽ የቀረው ጥላቻ ይዘው ተቀበሉት፡፡ ፈጥሮ የሠጣቸውን ውኃ እስኪ ነፍጉት ድረስ፡፡ አባባ ናታን‹‹ ምን እላላሁ? ነፍሴን በምክራቸው ያልጨመረ በፍርዳቸው ልቤን ያላኖረ ሰውነቴንም ከሸንጎዋቸው የለየ የእስራኤል አምላክ ይመስገን፡፡ በቅዱሱ ብላቴና ላይ ሲሸምቁ እንደ ተኩላም ሲያደቡ ዓይኖቼን እንዲያዩ የከፈተ እርሱ የተመሰገነ ይሁን››፡፡

አስፈሪውን ጸጥታ ለመስበር ድፍረታችንን ያዩ በክፍሏ ውስጥ የነበሩ ሌሎችም ቀስ እያሉ መጥተው አብረውን ተቀመጡ፡፡

የመቅረዟን መብራት በእንባዬ ግርዶሽ እያየሁ መንፈሴ ወደ ኃሙስ ሌሊት ተነጠቀ፡፡ መምህሩን ይዘውታል የሚል መርዶ ከሰሎሜ እንደሰማሁ ልቤ ጉሮሮዬ ውስጥ ተሰንቅራ ጉልበቶቼ እየተብረከረኩ ወሰዱት ወደተባለበት የቀያፋ ጊቢ ተፋጠንኩ፡፡ እዚያ ስደርስ ሐና ወደተባለው የሊቀ ካህናቱ አማት ወስደውት ኑሯል ጊቢው ጭር ብሏል፡፡

አረጋዊ መሆኔና እንደ በረሃ ዓለት ባገጠጡ የጉንጮቼ አጥንቶች ላይ የሚወርደውን ዕንባ ጨለማውና ሀጫ በረዶ የመሰለውን ፂሜ ተረዳድተው ስለሸፈኑልኝ በረኞቹ አንዳእ ሳይሉኝ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡

ከብርዱ የተነሳ እዚህም እዚያም ከሚነደው እሳት በቀር እረጭ ብሏል ምን ያህል እንደቆየሁ አላስታውስም፡፡ ብቻ ግራ ገብቶኝ ዙሪያውን ሳማትር የጩኸትና የሁካታ የስድብና የዛቻ ድምፅ እየቀረበኝ መጣ፡፡ወዲያው በገመድ የደኃሪት አስረው ወደፊትና ወደኋላ እያዳፉ ይዘወት መጡ፡፡የማየውን አምኖ መቀበል ቸገረኝ፡፡ ሀይ ባይ ከልካይ የለም ሊመታው የፈለገ ይመታዋል ሌላው ይገፈትረዋል፤ገሚሱ ምራቁን ይተፋበታል መቅረብ ያልቻለ ከሩቅ ሆኖ ይረግመዋል፡፡

የሊቀ ካህናቱ ዘቦች ከአሁኑ እርሱ በመደብደብ መድከማቸው ያስታውቃል፡፡ ወላጆቹ እንደጠፋበት ህጻን በማየው ነገር ግራ ተጋብቼ መካከል ላይ እንደቆምኩ ደርቄ ቀረሁ፡፡ ዘቦቹ ህዝቡን እኔ ካለሁበት ጥቂት ሲቀር ገታ አድርገው እርሱን ብቻ ለይተው መሀል ላይ ለበቅሎ ማሰሪያ የቆመ ግንድ ጋር ጠፍረው አሰሩት፡፡

ልብሱ ተቦጫጭቋል፡፡ መደረቢያው የለም፡፡እጆቹና እግሮቹ ተጋግጠዋል፡፡ፊቱ ለማየት በሚዘገንን ሁኔታ በደም በላብና በምራቅ ተሸፍኗል፡፡በታሰረበት ቦታ ከጉልበቱ ሸብረክ አንገቱን ዘለስ አድርጎ ከብርቱ ድካም ጋር ይታገላል፡፡ጥቂት ቆይቶ ቀና ብሎ ሲመለከተኝ አሁንም ዓይኖቹ ውስጥ የተለመደውን ርኅራኄና ፍቅር የጀመረውን ለመጨረስ የተዘጋጀ ቁርጠኝነት አየሁ፡፡ ፍርሃትም ሆነ ጭንቀት አይታይበትም፤ፍቅር ሀዘንና ርኅራኄ ግን ከዓይንኖቹ አሁንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይረጫሉ፡፡ በደምና በምራቅ ካደፈ በጡጫ ብዛትም ካባበጠ ፊቱ መካከል ዓይኖቹ በድቅድቅ ጨለማ እንዳሉ ከዋክብት ያበራሉ፡፡ሁሉን በፍቅርና በሀዘኔታ ያያል፡፡አባት ሕፃናት ልጆቹን በሚያይበት ሁኔታ ያስተውላቸዋል፡፡ሲመቱትም ሆነ ሲተፉበት ፊቱን አይሰውርም እይታውም አይቀየርም፡፡

ከሆዴ አንዳች ጥላቻ ሲገነፍል አፌንም ምሬት ሲሰማኝ ሁሉን በቁጣ ተመለከትኳቸው፡፡እርጅናዬን ድካሜን ሁሉ ረገምኩት፡፡ወይኔ በጉብዝናዬ ወራት ቢሆን የቻልኩትን ጥዬ እወድቅ ነበር፡፡እኒህን ጭራቆች እኒህን የሰው ልጅ የጭካኔው ጫፍ መገለጫዎች ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አንዳች ኃይል ቢኖረኝ ስል ተመኘሁ፡፡በቁጣና በእልህ ጉሮሮዬ አብጦ ደም ሥሬ ተወጥሮ ዘወር ስል ዓይኖቼ ዓይኖቹ ላይ አረፉ፡፡

የማውቀው መዓዛ አወደኝ፡፡እናቱ ቀኝ እጇን ልቡ ላይ ጣለ ያደረገችበት ሕፃን በግርግም ሳለ ታየኝ የእናቱን ጡት ሽቶ ሲያለቅስ እርሷም በስስት እያየችው ለፈቃዱ ስትታዘዝ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ወዲያው ደግሞ በታላቅ ዙፋን ላይ እንደታደረ በግ ሆኖ አየሁት፡፡

ከዓይኖቹ የሚወጣው ብርሃን ዓይኖቼን ሲዳስሳቸው ጥላቻና በቀል ቁጣና እልህ ከውስጤ ሲጠፋ በምትካቸው ፍቅርና ርኅራኄ ሀዘኔታም ሲሰርፅ ተሰማኝ፡፡በእርሱ ዓይን ሳያቸው እነርሱን የመጥላት አቅም አነሰኝ ፡፡ ዕይታዬ ሲፈወስ በደም የራሰ ፊቱ ሲፈካ ከአይኑም የአልማዝ ፈርጥ የሚመስሉ ዕንባዎች ሲፈሱ ተመለከትኩ፡፡ እንባው እንደታላቅ ዥረት ሲፈስ ፍጥረት ሁሉ በሀሴት ሲታደስ ይታየኛል፡፡ዕፁብ ዕፁብ ኦ የዘላለም አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የነፍሳችን ዕረፍት ይህን ፍቅር ይረዳ ዘንድ ማን ይችላል? ይህ የማይመረመር ትዕግስት ይገልጡት ዘንድ የማይደፈር ትኅትና ምን ይደንቅ?

ኅሊናዬ በሰዎች ክፋትና ጭካኔ እየታመመ በጌታ ቸርነትና ፍቅር እየተደመመ እያለ በትንሹ ረገብ ብሎ የነበረው ጩኸትና ርግማን ድጋሚ ሲፈነዳ በድንጋጤ ዞርኩ፡፡ እነሆ የመድኅን እናቱ ከዮሐንስ ጋር በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል መጣች፡፡ ግማሹ ይራገማል ግማሹ ይጮኻል እርሷ በመካከላቸው ስታልፍ ምንም ዓይነት መረበሽ አይታይባትም፡፡ ወደ ማንም አትመለከትም፡፡ዓይኗ አንድዬ ልጇን ብቻ በመፈለግ ያማትራል፡፡ የምትፈልገውን እንዳገኘት ለጥቂት ደቂቃ ባለችበት ቆማ ታስተውለው ጀመር፡፡ ቀና ብሎ ወደርሷ ሲመለከት ቀስ እያለች ወደርሱ ቀረበች፡፡ የጠራ የጨረቃ ፀዳል የሚመስለው ፊቷ ለዘላለም የሚቆም በማይመስል ዕንባ ይታረሳል፡፡ ዕንባዋ በአንገቷ ወርዶ ደረቷን አርሶታል፡፡ አትጮኽም አትወራጭም፡፡ ፊቷ ላይ ብቻ አንዴ ሀዘን አንዴ መደነቅ ሲያረብበት ግንባሯ ቅጭም ደግሞም በርኅራኄ ጥንዝል ይላል፡፡ ማንም ሊያስቆማት የሞከረ የለም፡፡ ደርሳ በዕቅፏ ልትይዘው የጎልማሳ ርምጃ ያህል ሲቀራት አንድ ዘብ አስቆማት አልተቆጣችም አልተቃወመችም ባለችበት ቆማ ዕንባ ባረገዙ ዓይኖቿ ውዷን እያየችው እጇን ዘረጋች፡፡ቁስሉን ልታጥብለት ስቃዩን ልታስታግስለት የእናትነት አንጀቷ ናፈቀ፡፡ ሀዘን አንጀቷን ሲያኝከው በልጇ የደረሰ መጎሳቆል መንፈሷን ሲያቆስለው ምጥ እንዳስጨነቃት ወላድ ሆዷን እቅፍ አድርጋ የሠራ አካላቱን በዓይኖቿ ትዳስሰዋለች፡፡

ጌታችን እናቱን ሲያያት ልቧን የሚወጋትን ሕዋሳቷን የሚቧጥጣትን የሀዘን ሰይፍ ለመቻል ትታገል ነበር፡፡የዘረጋች እጆቿን ለመያዝ እጁን ለመዘርጋት ቢሞክርም አልቻለም፡፡ብርቱ ንፋስ እንደመታው ዛፍ በሲቃ የሚናጥ ሰውነቷን እያየ አናገራት፡፡ቃል ግን አላወጣም፡፡ሁለቱ በሚተዋወቁበት በዝምታው አናገራት በጽሞና አደመጠችው ለፈቃዱም ታዘዘች ልምዷ ነውና፡፡

ዘወር ብላ የምትቆምበት ጥግ ስትፈልግ ጻዕረ ሞት መስዬ በቆምኩበት ተመለከተችኝ፡፡የብርሃን እናት ከፊቴ ስትቆም ዓይኖቿን እያየሁ ለመናገር ሞከርኩ፡፡ምላሴ ከትናጋዬ ተጣብቋል ሰውነቴ ውስጥ አንዳች ፈሳሽ የቀረ አልመሰለኝም፡፡መናገር አቅቶኝ አፌን ለመክፈት ስታገል ቀረብ ብላ እጆቼን ያዘቻቸው፡፡የሀዘን ማዕበል ሲንጠኝ ከልቅሶዬ ሳግ ጋር እየታገልኩ‹‹ለምን?ግን ለምን የብርሃን እናት ሆይ?ይህ ሁሉ በእርሱ ላይ ለምን?ምን በደል ተገኘበት?ምንስ ክፋት ታየበት?. . .መቀጠል አልቻልኩም፡፡

የብርሃን እናት‹‹እርሱ ሁሉን ያውቃል መንገዱን ይመረምር ዘንድ ማን ይችላል፡፡እንዳሰበ ይሠራል እንደፈቀደም ይፈፅማል፡፡ ነቢያት የተናገሩት የመጻህፍትም ቃል ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው፡፡ይህ ሁሉ እንደሚሆን አስቀድሞ እንደነገረን ልብ በል ናታን››አለችኝ፡፡ እርግማንን ሲሽር የበደልን ሥራ ሲቆርጥ ስለዚች ሰዓት መጥቷልና፡፡ የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ተግሳፃችንን ሊሸከም በደላችንንም ሊያስወግድ ተገልጧል፡፡የጀመረውን ይፈፅመዋልና በጽናት እንቁም አይዞህ ስትልኝ በረታሁ፡፡አጽናንተሸኛል የጌታዬ እናቱ ሆይ ብያት ሌሊቱን እንገፋ ዘንድ አንዱ ጥግ ሔደን ተቀመጥን፡፡

ለቅፅበት እንኳ ለዓኖቿ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶቿ ዕረፍት ሳትሰጥ ዕንባዋ እንደ ክረምት ዥረት እየፈሰሰ አደርን፡፡እርሱ ላይ ዱላ ባረፈ ቁጥር እያንዳንዷ ሕዋሷ ሲታመም ይታወቀኝ ነበር፡፡ ዕለተ ዓርብን መግለጽ የሚችል ምን አንደበት ነው? ልብ ይታመማል አእምሮም ይዝላል፡፡ከጠዋት አንስተው እያንገላቱ ገዥው ጊቢ ወሰዱት አንዲት ፅዋ ውኃ እንኳ እናቀብለው ዘንድ የሚፈቅድ ርኅሩኅ ልብ አላገኘንም፡፡

በዚህች ዕለት የአዳም ልጆች ጭካኔ የእርሱ ይቅር ባይነቱ ተገለጠ፡፡የገዛ ወገኖቹ ያልራሩለትን እርሱን የሮማ ወታደሮች የደም ጥማታቸው ተወጡበት፡፡

የማይሆን ሲሆንበት ሊደረግ ማይገባ ሲደረግበት ሁላችን እናቱን ከበን እናይ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ መከራው የእርሷም አካል አብሮ እንደ ጽጌረዳ ይረግፍ ነበር፡፡

መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ መንገድ ሲጀምር እዚያው እንድቀር ሁሉም ግድ አሉኝ የብርሃን እናትን ግን ለመንኳት‹‹እባክሽን በተጓዘበት መንገድ ልጓዝ የደሙን ነጠብጣብ ተከትዬ ልሂድ፡፡ ከልቤ ናፍቆት ሰንፌ እንዳልቀር በጸጋሽ ደግፊኝ፡፡ እግሮቹ የቆሙበት ሥፍራ ልድረስ፤ ማዳንህን ዓይኖቼ አይተዋልና ባሪያህን አሰናብተኝ እለው ዘንድ በመስቀሉ ሥር ልዋል፡፡

የጌታዬ እናት‹‹እርሱ ከመከተል አትድከም የሁሉን ፍጻሜ ታይ ዘንድ ልብህን አበርታ›› አለችኝ በረታሁም፡፡

እነዚያ ጨካኞች እነርሱ ራሳቸውን ችለው መውጣት የከበዳቸውን መንገድ፤ውኃ እየጠጡና እያረፉ ሲጓዙ ከእርጥብ እንጨት የተሠራ መስቀል ተሸክሞ ለሚቃትተው ለእርሱ ግን ዕረፍትን ሊሰጡት አልወደዱም፡፡ ስለ እርሱ የእኔ ልብ በውስጤ ቀለጠች፡፡ ድንገት አንዱ ፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ ፍጠን ብሎ ቢረግጠው መስቀሉን እንደተሸከመ በግንባሩ ፍግም ብሎ ወደቀ፡፡ መስቀሉ ማጅራቱን ቀጥቅጦ ከዓለቱ ጋር ስላጣበቀው ፀጥ ብሎ ሲቀር ሁላችን በዋይታ ተሞላን፡፡

ወደ ማን እንጩኽ? ዕርዳታስ ከወዴት ይመጣ ዘንድ እንጣራ?

ወታደሮቹ ሁሉ ከመሰቀሉ በፊት የሞተ መስሏቸው ተደናገጡ፡፡ አንድ ዓይን ብቻ የነበረው የወታደሮች አለቃ በቁጣ ከጮኸ በኋላ ፣መስቀሉን ያነሱለት ዘንድ አዘዘ፡፡ ገልብጠው በጀርባው ሲያንጋልሉት ዓለቱ ከቀጠቀጠው አፍና አፍንጫው የእሾኽ አክሊል ከተጎነጎነበት ራስ ቅሉም ደም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ፊቱም በደምና በአቧራ ተሸፍኖ ለማየት ተሳነው፡፡

አንዲት በነፍሷ የቆረጠች ብላቴና በወታደሮቹ መካከል አፈትልካ አጠገቡ በመድረስ መጠምጠሚያዋን ፈትታ ሰጠችው፡፡ ከመሳቀቋ የተነሳ ደፍራ ልትጠርግለት እንኳ አልቻለችም፡፡ እርሱም ፊቱ ላይ ያለውን ደሙን ጠርጎ አንዳች ነገር ካናገራት በኋላ ለመነሳት መታገል ጀመረ፡፡

ውሎአችንን የሚሰሙ በጊዜው ያልደረሱ ወይም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ያልቀረቡ ራሳቸው እስኪፈርስ ሲያለቅሱ ሳጋቸው ይሰማኛል፡፡

በመካከል አንዲት ልጅ እግር ብላቴና በደም የተታታ ጨርቅ አቅፋ እያነባች ‹‹አባባ ናታን እነሆ ጌታችን ደሙን የጠረገበት ጨርቅ፡፡ አሁን እስኪያነሱት ድረስ የሆነውን ሁሉ ለማስታወስ የሚችል አቅል አልነበረኝም፡፡ እያንዳንዷ የደም ጠብታ ከሰማይና ከምድር የገዘፈ ዋጋ አላትና ለብርሃን እናት ወይም አእማድ ለሚመስሉ ደቀመዛሙርቱ አግኝተን እስክንሰጣቸው እነሆ›› አለችኝ፡፡

ጨርቁን ስቀበላት ያቀድሞ የማውቀው መዓዛ ሲያውደኝ ይታወቀኛል፡፡ እጀቼ እየተንቀጠቀጡ ቀስ አድርጌ የደከሙ ጉልበቶቼ ላይ ስዘረጋው ለማመን የሚከብድ ትዕይንት ገጠመን፡፡ ሁላችንም አፋችንን ከፍተን ዕንባ ባቆረዘዙ ዓይኖቻችን ለረዥም ሰዓት በአድናቆት ስናስተውለው ቆየን፡፡

መከራውን እንድናስብ የደሙን ዋጋ እንድንረዳ መልእክት ትቶልናል፡፡ ልክ መልካም ሰዓሊ እንደሚሥለው ሥዕል የመከራው ሰዓት መልኩ ጨርቁ ላይ በደሙ ታትሞበታል፡፡

ብላቴናይቱ‹‹ወንድሞቼና እህቶቼ ጌታ ይህን ጨርቅ ፊቱን ጠርጎ ሲመልስልኝ፤ ዓይኖቹን ትኩር ብዬ አየኋቸው ደም ጎርሰው ለማየት እንኳ እስኪቸግረው ቢደርስም እስከመጨረሻው ለመሔድ የነበረውን ጽናት እንድረዳው አደረገኝ በቃሉም ‹‹እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች ስለ ራሳችሁ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ፡፡ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጠቶች የተባረኩ ናቸው የሚባልበት ዘመን ይመጣልና፡፡ በእርጥቡ እንጨት ይህን ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?›› አለኝ ብላ በዚያች የመከራው ወቅት እንኳ ስለ መንጋው እንጂ ስለ ራሱ እንዳልተጨነቀ የፍቅሩን ጽናት አስታወሰችን፡፡

ጥግ ላይ ግዙፍ ሰውነቱን የሀዘን እሳት እንደ ጅማት ያኮማተረው አንድ ጎልማሳ መሬቱን በእጁ እየጫረ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል ድምፁን ሳግ እያነቀው‹‹ወታደሮቹ አጠገብ ስለነበርኩ የጭካኔያቸውን መጠን አይቼዋለሁ፡፡ ከእርሱ መከራ ይልቅ የስጨንቃቸው የነበረ ከቁማራቸው ላይ ተነስተው እርሱ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ለመፈጸም ያባከኑት ጊዜ ነው፡፡ጌታ ኢየሱስ ፊቱን በጨርቅ ካበሰ በኋላ ከወደቀበት ተነስቶ መስቀሉን ለመሸከም ረዥም ጊዜ ወሰደበት፡፡አንዳቸው እንኳ መስቀሉን አንስተው ለማሸከም ርኅራኄ አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንም ቆሎ በል እያሉ ባለ ኃይላቸው በአለንጋ ይገርፉት ነበር፡፡ እያንዳንዱ ግርፋት ሲያርፍበት ከሕመሙ የተነሳ ሰውነቱ ሲንቀጠቀጥ ይታየኝ ነበር፡፡ትንሽ ፋታ እንኳ ሳይሰጡ ያጣድፉታል፡፡ ጌታ ግን መስቀሉን ሊሸከም የሚችልበት አቅም ስላልነበረው ሰውነቱን ለአለንጋችው ትቶ ተንጋለለ፡፡ያለ ህኅራኄ ሲገርፉት አለንጋው ስለሚያርፍበት ቦታ እንኳ አይጨነቁም ነበር፡፡ ሰውነቱ ደም በሚተፋ ሰምበር ተዥጎርጉሮ ደም ግባቱም ጠፋ፡፡

ቀስ ብዬ ወደ ወታደሮቹ አለቃ ስቀርብ በዚህች ምድር ላይ ለመኖር አንዳች ፍላጎት ስላልነበረኝ ሞትን በደሰታ ለማቀፍ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ምድር ለአራዊት ለመሰጠቷ ከዚያ በላይ ምስክር አላስፈለገኝም፡፡

የወታደሮቹን አለቃ‹‹ፍርዱ ሳይፈጸም እዚሁ ከሚሞትባችሁ መስቀሉን ለመሸከም እንድረዳው ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡ እርሱም በቀረች አንድ አይኑ ውስጥ ያልጠበኩት የርኅራኄ ጥላ ውልብ ብሎ ፈቀደልኝ፡፡

መስቀሉ እንኳን በድካም ለዛለና በዱላ ብዛት ለደቀቀ ቀርቶ ጤነኛ ሰው ሊሸከመው ከሚችል በላይ ክብደቱ አስጨናቂ ነበር እንዴት ቻለው?

እንደምንም መስቀሉን አንስቼ ስቆም ከክብደቱ የተነሳ ጎኔን ውጋት ቀስፎ መተንፈስ አቃተኝ፡፡ከህዝቡ መካከል ሀዘን ያደቀቃት የጌታችን እናት በትኅትና እየተራመደች ሔዳ አጠገቡ በርከክ አለች፡፡እጆቹን አንስታ ደረቷ ላይ ስታደርገው ቀና ብሎ ሲያያት እርሱን በመውለዷ ስላገኛት መከራ ፊቱ በሀዘን ተመቶ ዕንባው ኮለል እያለ ወረደ ዕንባዎቹን ቀስ ብላ በጣቷ እየጠረገች በከንፈሮቿ መጠጠቻቸው ግንባሯ ቅጭም አድርጋ ራሷን ከፍ ዝቅ እያደረገች በዓኖቿ ስታናግረው አንደምንም አንገቷን አቅፎ ተነሳ፡፡ሀዘን ያደቀቀው መከራ የሰበረው ልብ ሰይፍ ያለፈባትም ነፍስ ምን እንደምትመስል እርሷ ፊት ላይ አነበብኩኝ፡፡

እኔ በስተቀኙ ሆኜ ትከሻ ለትከሻ ገጥመን መስቀሉን ለመሸከም ክንዶቻችን ሲቆላለፉ መስቀሉ ዓለት እንደወደቀበት ቁልቁል አጠፈኝ፡፡ይህ መስቀል ከእርሱ በቀር ፍጡር ሊሸከመው የማይችል መሆኑ የገባኝ ያኔ ነበር፡፡ ለካስ የተሸከመው ዓለምን ነበር፡፡ለካስ ጫንቃው ላይ የወደቀው መለኮታዊው ፍርድ ነበር ተሸክሞ እየቃተተ ኮረብታውን የሚወጣው የሰውን ልጆች ሁሉ ሸክም ነበር፡፡

መንቀሳቀስ ሲያቅተኝ ዘወር ብዬ ተመለከትኩት ወደ እኔ ሲዞር ፊታችን ስንዝር ያህል ርቀት ነበረው፡፡በምራቅ የተበከለ ፊቱ ፍቅርን፤ደም የጎረሱ ዓይኖቹም ርኅራኄን ሲረጩ አየኋቸው፡፡

ጌታ ሆይ ለዚህ የተገባሁ አይደሉምና ይቅር በለኝ፡፡ይህን መስቀል መሸከም የሚችል መቼም መች ካንተ በቀር አይኖርም፡፡ በልቤ ቅንነት ያደረግሁትን ተመልከት፤ላግዝህ እንደማልችል ባውቀውም እስከ ፍጻሜው ግን አብሬህ ልሒድ ሸክሜ በአንተ ጫንቃ እንደኖረ መተላለፌንም እንደተሸከምክ አሁን አወቅሁ፡፡ እባክህ ጌታ ሆይ ከጌታ ጋር መስቀሉን የተሸከመ ተብዬ እቆጠር ዘንድ የታሪኬም ፍጻሜ ካንተ ጋር ይሆን ዘንድ ይቺን ብቻ ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡

ያን ጊዜ መስቀሉ የርግብ ላባ ያህል ሲቀለኝ ክፋቴ ሁሉ ግን በእርሱ ሸክም ሲሆንበት ታወቀኝ፡፡ በጸጥታ እያነባሁ እስከዚህ ያደረስከኝ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ በፊትህ ምንድር ናት?እያልኩ መጨረሻው ድረስ አብሬው ተጓዝኩ፡፡

በዓይኖቹ ትኩር ብሎ ሲያየኝ ወደ ሞት እየሄደ መሆኑን ባውቅም አልተሰናበተኝም፡፡ይልቁንም ይበልጥ ሊቀርበኝ ከርሱም ጋር ፈፅሜ ስጣበቅ ተሰማኝ፡፡

ችንካሩን ስመለከት ሰውነቴ በፍርሃት ራደ ልበሶቹን ሲገፉት መከራ ያልደረሰበት አንዳች ሰውነት አልቀረውም፡፡በጎኑና በጀርባው ያሉ አጥንቶቹ እስኪቆረጡ ድረስ ፈጠዋል፡፡ሲቸነክሩት ያሰማ የነበረው የጣዕር ድምፅ የሕይወት ዘመኔ ሲቃ እንደሚሆን ታወቀኝ፡፡ጌታ ሆይ! ለምን?ሌላ መንገድ አልነበረምን? ለምን ይህን የጭንቅ መንገድ ትመርጥ ዘንድ ፈቃድህ ሆነ?

ሆዴ ሲገላበጥ አፌን ደም ደም ሲለኝ የብርሃናት ጌታን ዕርቃን ለማየትም ስላልደፈርኩ ፊቴን ሸፈንኩ፡፡ ግን አሁንም ይታየኛል፡፡ መከራው ሊረሱት ከሚችሉት በላይ ነበርና፡፡

ጎልማሳው ይህ ሲነግረን የነበረውን መቀጠል አልቻለም ፡፡ የተመለከተው ነገር የዕድሜ ዘመኑ ሸክም የሕይወቱም እንጉርጉሮ እንደሚሆን ከእኛ የተጠራጠረ አልነበረም፡፡

የአይሁድ መምህር የሆነው ኒቆዲሞስ ‹‹ወንድሞቼ እህቶቼ የሆነውን ሁላችን ዓይተናል፡፡ጌታችን ነፍሱን በሠጠባት ሰዓት ፀሐይ ስትጨልም፣ጨረቃ ደም ስትሆን፣ ከዋክብት ሲረግፉ፣የቤተመቅደሱ መጋረጃ ሲቀደድ፣የመሬት መናወጥ ሆኖ መቃብራት ሲከፈቱና ሙታን ሲነሱ ስመለከት በመጽሐፍ የተባለው የነብያቱ ሁሉ ጩኸታቸው የአበው ተስፋቸው እንደተፈፀመ አወቅሁ፡፡ እርሱ እውነተኛው መሲሕ የሕያው አምላክ የባሕርይ ልጁ የዓለሙ ቤዛ እንደሆነ ፍጹም አመንሁ፡፡

ጲላጦስ ቤተመንግሥት ስደርስ የካህናት አለቆች የአይሁድ ሽማግሌዎች ጲላጦስ ስላደረገላቸው ምስጋና ሊያቀርቡ ተሰብስበው ነበር፡፡ሁሉም በዓይነ መዓት ተመለከቱኝ፡፡ጥርሳቸውን የሚያፋጩም ነበሩበት፡፡

ገዥውን የጌታን ሥጋውን እንዲሰጠኝ ስለምን በቁጣ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ አስቀድሜ ስለተዘጋጀሁበት ነገ ሰንበት ነው ሰንበት ከመግባቱ በፊት ሥጋው ከመስቀል መውረድ አለበት ብዬ ስናገር የአርማትየሱ ዮሴፍም ሰንበት ሊሻር አይገባም ብሎ ደገፈኝ አይሁድ ስለ ሰንበታቸው እንጂ ስለጌታ ሥጋ ግድ ያልሰጠን ስለመሰላቸው ተስማሙ፡፡

ገዥው ሥጋውን እንዲሰጡን ፈቀደ፡፡አስቀድመን ግን መሞቱን እንድናረጋግጥ ጻፈበት፡፡ለወታደሮቹ አለቃ ትዕዛዙን ስንሰጠው ጠጋ ብሎ በጦር ጎኑን ወጋው፡፡ያልተቀላቀለ ውኃና ደም ከጎኑ ሲወጣ የወታደሮቹ አለቃ ጦሩን ጥሎ በምስጋና መጮኽ ጀመረ፡፡በዚያ ቅጽበት ጠፍቶ የነበረው አንድ ዓይኑ እንደተፈወሰ ተመለከትን፡፡መስቀሉ ሥር ተንበርክኮ ‹‹መስማትንስ ድምጽህን ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ›› ብሎ ሲያመሰግን እኔም የወጉትን ያዩታል የሚለውን የመጽሐፉን ቃል እያሰብኩ ነበር፡፡

ከመስቀሉ ስናወርደው እናቱ ከእኛ ጋር አብራ በእቅፏ ተቀበለችው፡፡ እኛ የግንዘቱን ሥርዓት ስናደርስም ራሱን ጭኗ ላይ አሳርፋ ዕንባዋ ሰውነቱ ላይ እየወረደ ያለማቋረጥ የተቸነከሩትን እጆቹ ትስማቸው ነበር፡፡ሥጋውን ያሸንበትን በደም የተነከረ ጨርቅ ከእጄ ስትቀበል ዓይኖቿ ውስጥ በቃላት የማይገለፅ ምስጋና ተመለከትሁ::

ወደ መቃብሩ ከመሄዳችን በፊት መስቀሉ ላይና መስቀሉ ሥር የፈሰሰ ደሙን በመጎናጸፊያዋ አብሳ ያዘችው፡፡

መቃብሩ በጲሊጦስ ማኅተም ሲዘጋ ከዮሐንስ ጋር ቁልቁል መውረድ ጀምሩ በየጥቂት እርምጃዎቿ ዘወር እያለች መቃብሩን ታየው ነበር፡፡ ልቧ በዚያ እንደቀረ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜም ከዚያ እንደማትለይ ያያት ሁሉ በቀላሉ እርግጠኛ ይሆናል፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ‹‹ጌታ በሕይወቱ ገና ሳለ የነገረን ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ የቀረን በሦስተኛው ቀን እነሳለው ያለንን ቃል በእምነትና በተስፋ ጸንተን መጠበቅ ነው፡፡ ለቃሉ የታመነ ነውና፡፡ በዚያ ያሉ አርድእት ሁሉ በስቅለቱና በመከራው ሰቆቃ እንደተዋጡ ትንሣኤውን በተስፋ ሊጠብቁ በቃሉ ፀኑ፡፡

‹‹ እሁድ ማለዳ ››

ዜናው ሰማን፡፡መላእክት ወደ መቃብሩ ለሔዱ ሴቶች ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትሹታላችሁ? እንደተናገረው ተነሥቷል፡፡ ወደ ገሊላም ይቀድማችኋል›› እንዳሏቸው አበሰሩን፡፡

መግደላዊት ማርያም እንዳየችው እንዳናገራትም ተረከችልን፡፡ ኬፋና ዮሐንስም መግነዙንና መጠምጠሚያውን ከመቃብሩ ይዘው መጡ፡፡

ወደ ገሊላ ስንሔድ ዓርብ በሀዘን የተቃጠሉ ዓይኖቻችን ዛሬ በትንሣኤው ደስታ ያነቡ ነበር፡፡

በዝግ ቤቶቻችን ሳለን‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› የሚለውን የእረኛችንን ድምጽ ዳግመኛ መስማት በዚያ ለነበርን ሁሉ ከአእምሮ ባለይ ነበር፡፡

እንዲህ ያለ ትኅትና እንደምን ያለ ትኅትና ነው፡፡

እንዲህ ያለ ትዕግሥት እንደምን ያለ ትዕግሥት ነው፡፡

እንዲህ ያለስ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፡፡ሰውን እስከሞት መውደድህ ከማለት በቀር ሌላ ልንለው የምንችል ነገር አልነበረንም፡፡

ጌታ በተደጋጋሚ ለእኛ በታየባቸው አርባ እለታት ያውደኝ የነበረ ያ የማውቀው መዓዛ በዕለተ ዓርብ ኒቆዲሞስ ሲቀርበኝ ለምን እንዳወደኝ አሁን ተገለጠለኝ፡፡ እስከሞቱ ተከትሎታል ቅዱስ ሥጋውንም ገንዞ ለመቅበር ተመርጧል፡፡ የቅድስናው መዓዛም በእርሱ ላይ የመቅረቱ ምሥጢር ያ ነበር፡፡ ተሰብስበን በአንድነት በዳዊት ቃል አመሰገንን "በምሽት የለቅሶ ዋይታ ከበበን ሲነጋ ደግሞ ፍስሐ፤ ክፉን ባየንበት ሕማምንም በተቀበልንበት ዘመን ፋንታ ደስታ በዛልን፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን ከሠራ ከእርሱ ነውና"፡፡

 

ከነገድን ከቋንቋ ከሕዝብም ለአባቱ መንግሥት የተባገባን እንሆን ዘንድ በደሙ የዋጀን የፍጥረታት ሁሉ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባው አሜን !





ሚያዝያ 2007

ዘመነ ሉቃስ

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 



Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል አንድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

       በ2005ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ቅዱስ እግዚአብሔር ባዘጋጀልን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መማር እንጀምራለን፡

ትምህርቱ የሚዳስሳቸዉ ነጥቦች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ

·         ቀዳማዊ ወድኅራዊ ሕያዉ ዘላለማዊ አምላክ ስለመሆኑ

·         ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት ስለመወለዱ(ስለ ሁለቱ ልደታት)

·         ስለ ድንቅ  ልደቱና የልጅነት ህይወቱ፣ ስለጥምቀቱ፣ ስለትምህርቱና፣ ስለተዓምራቱ፣ ስለህማሙ፣ስቅለቱ፣ ሞቱ፣ትንሣኤዉና ዕርገቱ፣ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ፣ ወዘተ…ይሆናል፡፡

 

       በቅድሚያ አንድን አካል "አምላክ" ነው ለማለት የአምላክነት ባህርያት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሁሉ ነገር የማንነቱ መገለጫ ወሰን ባህርዩ ነውና፡፡ ሰለዚህ የአምላክነት ባህርያት የሚባሉትና የየትኛዉንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም ፍልስፍና አራማጅ የሚያስማሙት፡-

-    ሕያዉነት(ዘላለማዊነት)    - ሁሉን ቻይነት(Omnipotent)   - ሁሉን አዋቂነት (Omniscient)

-    በሁሉ ስፍራ መገኘት(በቦታ አለመወሰን)Omnipresent

-    ተወካፌ ጸሎት ወአኮቴት (የፍጡራንን ሁሉ ጸሎትና ምስጋና ለመቀበል የተገባው)

-    ዘሥሉጥ ላዕለ ኵሉ(በሁሉ ላይ የሠለጠነ፡በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡

 

1.   ሕያውንት(ዘላለማዊነት):- የዘላለማዊነት ጫፍ ከመገኘት በኋላ (ድኅረ ህላዌ) የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከፊትም የሚኖር ነው' የዘላለም ጫፍ ፊተኛ እና ኋለኛ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም "ኣልቦቱ ጥንተ ወኢተፍፃሜት" እንዲል በቀዳማዊነት ባይሆንም በድህራዊነት ግን ሰውና መላዕክት ይመስሉታል፡፡

 

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሰው ምሳሌ ሆኖ የባርያውን መልክ ይዞ በመካከላችን ቢገለጥም እርሱ ዘላለማዊ ህያው አምላክ መሆኑን ከዚህ በታች የተጠቀስት ምንባባት ያስረዳሉ፡፡

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች

 

v  መዝ109(110) *3 :- ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀኝ በቅዱሳን ብርሃን ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ          ከሆድ ወለድሁህ

v  ምሳ 8 *2-36:- "…እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ በቀድሞ ሥራዉ መጀመሪያ@ ከጥንቱ ከዘላላም  ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርም አስቀድሞ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፡፡

v  ትን.ኢሳ 48*16:- "…ወደ እኔ ቅርቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስዉር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል"

v  ትን.ሚክ 5* 2:- "አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንደ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡ (ከማቴ 2፤5-6 ጋር ይገናዘብ)

v  ዮሐ 1*1-3 :- "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአበሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር…ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳንች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም"

v  ዮሐ 1*30 :- "አንድ ሰው ከኃላዬ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል" መጥምቁ ዮሐንስ ጌታን በሥጋ ልደት 6 ወር እንደሚቀድመዉ በግልፅ የታወቀ ሲሆን እንዴት እንዲህ አለ ቢሉ በቅድምና መኖሩን ማኅፀነ ማርያም የህላዌው መጀመርያ መገኛ አለመሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

v  ዮሐ 8* 55-59 :- "… ገና ሃምሳ አመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ኢየሱስም እዉነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" አላቸዉ፡፡

v  ዩሐ17* 5 :- "… አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንደ በነበረኝ ክብር አክብረኝ

v  ዕብ1*10:- "… ስለ ልጁ ግን ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናፀፍያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጠማል@ አንተ ግን አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም" ቅዱስ ጳዉሎስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት አንዱ ለመሰላቸው እርሱ የመላእክት ጌታ አምላክ እንጂ መልዐክ አለመሆኑን ሲያስረዳ የፃፈው ነው፡፡

v  ራዕ5* 6-8:- "…እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትን ያዩታል… ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡

v  ራዕይ 1*17-18:- "… አትፍራ ፊተኛዉና መጨረሻዉ ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያዉ ነኝ"፡፡

v  ራዕይ 22*12:- "… እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራዉ መጠን እከፍል ዘንድ ወጋዬ ከአኔ ጋር አለ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው መጀመሪያዉና መጨረሻው እኔ ነኝ"፡፡

 

ተጨማሪ ጥቅሶች:- ሉቃ 1* 31-36 & ዮሐ 10* 30& ዮሐ14* 8-11& ቈላ 1*15-20

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

መስከረም 2005 ዓ.ም

Read more...

ሆሣዕና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሆሣዕና፡- በዚህ ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ቀን እናስባለን፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከጌታችን ፱ቱ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ከሌሊት ጀምሮ በታላቅ መንፈሣዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በሌሊቱና በዑደቱ ሥርዓት ላይ ብቻ ከዘጠኝ ያላነሱ ምስባኮች ስለሚደርሱ ሁሉን መተርጐምን ለጊዜው ታግሠን የትኞቹ እንደሆኑ እንድናውቅ ብቻ ማመላከቻ እንሰጣለን፡፡

ምስባክ፡-መዝ፹፥፫፤መዝ፻፲፯፥፳፮፤መዝ፻፳፩፥፩፤መዝ፻፵፯፥፩፤መዝ፻፲፯፥፳፯፤መዝ፱፥፲፩፤መዝ ፰፥፪፤መዝ፵፱፥፩፤መዝ፷፯፥፴፬

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ አራቱም ወንጌላውያን ተባብረው ጽፈውታል፡፡ በማቴ 21፥1-17፤በማር11፥1-10፤ሉቃ19፥29-38፤በዮሐ12፥12-19 በመሆኑም አንዱ ወንጌላዊ የመዘገበውን ብቻ የጽሑፋችን መነሻ ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ወንጌላት መዳሰስን መርጠናል፡፡

ጌታችን ራሱን ለዓለም ገልጦ ማስተማር ከጀመረ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይኽ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚሁም ጊዜ ቤዛነትን ፈጽሟል፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በአህያናበውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈፀም ነው፡፡

ትንቢቱ “ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ትን.ዘካ 9፥9

ምሳሌውም፡- በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመነ ጸብዕ(ጦርነት) መምጣቱን ለማመልከት በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታዩ፤ ዘመነ ሰላም መምጣቱን ለማመልከት ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ለአራተኛ ጊዜ የመጣው በደሙ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በመካከላችን ፍፁም ሰላምን(ዕርቅን) ለማድረግ ነውና ይህንኑ ሲያመለክት ነው፡፡ በመከራዬ፣ደሜን በማፍሰሴ፣በስቅለቴ፣በሞቴ ሰላም የሚሆንላችሁ ጊዜ ቀርቧል ሲለን ነው፡፡

“ፈትታችሁ አምጡልኝ ለጌታ ያስፈልጉታል”

ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ወደምትባል መንደር ሲደርስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ሲልክ የሰጣቸው ትዕዛዝ ነው፡፡ የታሠሩ አህያና የአህያይቱን ግልገል ሲያገኙ የሚያደርጉትንና ለሚጠይቋቸው የሚሠጡት መልስ፡፡

ነባቢት ነፍስ ያለችው ሰውም ሆነ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታት መታሠርን አይወዱም፡፡ምክንያቱም በተፈጥሮ ያገኙትን የመንቀሳቀስ መብት ይፃረራልና ነው፡፡መታሠር ነፃነትን፣ መታሠር ፈቃድን ይጋፋል፡፡ እኒያ እንስሳት የታሠሩበት የራሱ ምክንያት ይኖራል፡፡ እንስሳት እንዳይጠፉ፣ሌባ እንዳይሠርቃቸው ወይም የሚያጠፉት ነገር ሲኖር እንዳይደርሱበት ለማድረግ ይታሠራሉ ወይም በሌላ አነጋገር ነፃነታቸው ይገደባል፡፡

ሰውንም እንደአስፈላጊነቱ ከጥፋት ለመጠበቅ በሕግና በደንቦች ይታሠራል፡፡ አስተዋይ የሆነ በኅሊና ህግ ይጠበቃል፡፡ እኒህን ሁሉ ያልተጠቀመባቸው በቦታ እንዲገደብ ያደረጋል፡፡በሰው ላይ በጫና ሳይሆን በስምምነት የሚወጡ አብዛኛዎቹ ሕጎች ነፃነቱን አይነጥቁትም፡፡ በኅሊናው ሕግ የሚመራ ግን በአፍአ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ከሚኖርበት ሙግት ነፃ ስለሚሆን ፍፁም ሰላም ይኖረዋል፡፡ ከራሱ ከመሰሎቹ፣ከተፈጥሮና ከኒህ ሁሉ ገዢ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ህብረት፣ስምምነት፣ፍቅር፣አንድነት ይኖረዋል፡፡

ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ሲልክ “ ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱን መተርጉማን ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት(ከኃጢአት ማሠርያ) የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሠ ለማጠየቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ተመልከት)

ከእስራታቸው ተፈትተው ለጌታ ያስፈልጉታል እንደተባለ ጌታ ተቀመጠባቸው፡፡

- አዳምና ዘሩ ከሞት እስራት ነፃ ወጥተው የትንሣኤ ጌታ የሆነው የእርሱ ማደርያ ሆኑ፡፡

-አዳምና ዘሩ ሞትን ከሚያስከትል የሕግ እስራት ተለቀው፤ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ላወረደው አምላክ ዙፋን ሆኑ፡፡ በኦሪት የተሠጡን ትዕዛዛት ደገኛ ነበሩ፡፡ በማናቸውም ምክንያት እነዚያን ትዕዛዛት የሚተላለፍ ቢኖር ቅጣቱ በሞት ይፈፀማል፡፡ ይህም ሰውን ከሕጉ መልካምነት ይልቅ የቅጣቱን ክፋት እያሰበ በባርነት መንፈስ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

ሰውም የእግዚአብሔርን አሳብ መረዳት ስላልቻለ ግንኙነታቸውን በፍርሃትና በሕግ ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሰብረው መውጣት የቻሉ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ሕጉን መተላለፍ በድንጋይ መወገርና በእሳት መቃጠልን ሳይሆን ከፍቅሩ መለየትን እንደሚያስከትል አስተማረ፡፡ አሁን ሕጉን የምንጠብቀው የሞት ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን የአባታችንን ፍቅር ላለማጣት ነው፡፡ ሕጎቹ አልተሻሩም ቀድሞም ደገኛ ሕግ ነበሩና፡፡ ጌታችን ያሻሻለው እኛ ለሕግጋቱ ያለንን ግንዛቤ ነው፡፡ ሕጉን የምንፈፅምበትን መንፈስ ነው በውስጣችን ያደሰው፡፡ሕጉ በፍቅር ይጠብቀናል እኛም ሕጉን በፍቅር እንፈፅማለን፡፡ የአዲስ ኪዳን መንፈስ የወንጌል የምስራች ይኸው ነው፡፡ ዮሐ 14፥15፣ዮሐ15፥9-11 ሮሜ 7፥1-20

ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “እግዚአብሔርን ስንወድ ትዕዛዛቱን ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድበዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፡፡ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” 1ዮሐ 5፥2-4

ፈታችሁ አምጡልኝ በማለቱ የእስር ሠንሰለታችን ተቆረጠ፡፡ ሞት በሰው ላይ የሠለጠነው ኃጢአትን ምክንያት አድርጎ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ዓለምን የገዛው ኃጢአትንና ሞትን መውጊያው በማድረግ ነበር፡፡ ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋህዶ ኃጢአትን ባለመስራት ኃጢአትን፤ በሥጋ ሞቶ በመነሣት ሞትን፤በደመሰሰ ጊዜ የዲያብሎስ ግዛት ፈረሰ፡፡ ምክንያት የሚያደርግ ኃጢአትን ነበርና ጌታችን ግን “የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች የለውም” በማለቱ የሰው ልጅ ለባርነት ምክንያት የሆነው የኃጢአት መርዝ እንደተወገዱለት አረጋገጠልን፡፡ ይህን የተናገረ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የሚጠራ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ዮሐ14፥30፤1ቆሮ 15፥54-57

ይህ ብቻ ያይደለ በጸሎት በተመስጦ ከዚህ ዓለም ጭንቅና ፈተና፤በፆምና በተጋድሎ ከፍትወታትና ከእኩያት፤እውነትን በማወቅ ከወግና ከልማድ ትብታብ መፈታትን አደለን፡፡ ጥንትም ሰው የተፈጠረ በገዢነት መንፈስ እንጂ በተገዢነት ሁኔታ አልነበረም፡፡ሰው ሁሉን ይገዛል እርሱ የሚገዛው ግን ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛትም ነፃነት ነው፡፡  ለጌታ እግዚአብሔር ከመገዛት በራቅን ቁጥር ራሳችንን መግዛት አቃተንና ከእንስሳት እንኳ በግብር አንሰን እስክንታይ ተዋረድን፡፡ ሕግጋት ይመሩን ይደግፉን ዘንድ ቢሰጡንም ለመፈፀም አቅም አጣን፡፡ በመሆኑም ሕግጋቱ ኃጢአታችንን እየገለጡ እንደገና ዕዳ ሆኑብን፡፡ ቅ.ጳውሎስ “ነገር ግን በህግ ባይሆን ኃጢአትን ባለወቅሁም ነበር” እንዳለ ሮሜ 7፥9-10

ጌታችን ሰውነታችንን በወደዳትና በተዋሀዳት ጊዜ ከጸጋው ብዛት የተነሣ ከሕግ በላይ አደረግን፡፡ ከጌታችን ጋር ፍፁም ህብረት ያደረጉ ሁሉ ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋው በታች ይሆኑ ዘንድ ተባለላቸው፡፡ በሕግ ቢኖሩም ሕግ እንዳለባቸው አያስቡም በጸጋው ይደነቃሉ እንጂ፡፡

ይህ ሁሉ ነፃ የመሆን የመፈታት ማሳያ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ ነው “በነፃነት እንድንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን” ያለው፡፡ ሮሜ 3፥21-31፤ሮሜ 6፥12-19፤ገላ 5-1

አስተውሉ “ፈትታችሁ ልቀቋቸው” አላለም “ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁም ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ”አለ እንጂ፡፡ ከኃጢአት፣ከዓለም፣ከምኞት፣ከወግና ከልማድ ወዘተ…መፈታትን ወደርሱ ቀርበን ማደርያው ለመሆን ከእርሱ ጋር ለመሆን እንጂ ልንባዝን አይደለም፡፡

ወደ ሕይወታችን የተላኩ ካህናት ከእስራት የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡የሚፈቱን ወደ ጌታችን ለማቅረብ ነው፡፡ ከጌታችን ጋር የምንዋሃደውም ቅዱስ ሥጋውንና ክብሩ ደሙን በመቀበል ነው፡፡ ማንም በራሱ ሥልጣን ከኃጢአት እስራት መፈታት አይችልም፡፡ በራሴ ወደ ጌታ እቀርባለሁ በማለት የድፍረት ቃል መናገርም የተገባ አይደለም፡፡ እነሆ ሂዱ በማለት የሚፈቱንን የመንግስቱን ካህናት ልኳል፡፡ እነርሱም ከኃጢአት የምንፈታበትን ትምህርት ሥርዓት ጸሎትና ሥልጣን ይዘው እንፈታ ዘንድ ይጋብዙናል፡፡ ለምን? ለሚል መልሳቸው ለጌታ ታስፈልጉታላችሁ! ነው፡፡ ማቴ 18፥18፤ዮሐ 20፥23

ሰው ሆይ የተሰጠህን ክብር ተመልከት፡፡ ፍጡር ሳይኖር በፈጣሪነቱ፤ተገዢ ሳይኖር በአምላክነቱ፣ አመስጋኝ ሳይኖር በአኰቴቱቅድመ ዓለም ነግሦ ለሚኖር፤እልፍ አእላፋት ወትልፊት አእላፋት መላእክት፤የሚታየውና  የማይታየው ሁሉ ለሚገዛለት ለእርሱ ታስፈልጉታላችሁ መባላችን እንዴት ያለ ክብር ነው?፡፡ ፈጣሪነቱ በእኛ ታወቀ አንል ከእኛ ይልቅ ብዙ ፍጥረት ተዘርግቷል፤ያለእኛ ተገዢነት ጌትነቱ አይሟላም እንዳንል ሳንፈጠርም በጌትነቱ ኑሯል፤ ታዲያ “ለጌታ ያስፈልጉታል”መባላችን ስለ ምንድር ነው?/ቅዳሴ ዲዮስቆርስ/


 

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ልዑሉ ሲናገር “የእኛ ሕዝብህ መሆን ላንተ አያስፈልግህም ያንተ ጌትነት ለእኛ ያስፈልገናል እንጂ፤የእኛ ልጅነት ላንተ አይጠቅምህም ያንተ አባትነት ለእኛ ይጠቅመናል እንጂ” በማለት ገልፆታል፡፡ አባትነቱ በእኛ ልጅነት አይደነቅም፤ጌትነቱም በእኛ ተገዢነት አይከብርም፡፡ ዛዲያ “ታስፈልጉኛላችሁ” መባሉ ስለምንድር ነው?

እንመርምረው ዘንድ አይቻለንም! መልስ እናገኝለት ዘንድም ቅጥነተ አእምሯችን አይወስነውም! እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለ ርኅራኄስ እንደምን ያለ ርኅራኄ ነው ብለን ከማድነቅ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?/ ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ/

ጌታ ሆይ ልትፈልገን መጥተሃልና፤ታስፈልጉኛለችሁ ብለህም በክብር ጠርተኸናልና፤በአፈ አበው ቀደምት፣በልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት፣ጻድቃን ወሰማዕታት፣አእሩግ ወሕፃናት፤በአኰቴተ መላእክት ወሊቃናት እናመሰግንሃለን፡፡ ምስጋናና ክብር ኃይልና ባለጠግነት ጌትነትም በመታረዱ ለፈለገን ለበጉና ለአባቱ ለመንፈስ ቅዱስም ይገባል መቼም መች ለዘላለሙ አሜን! ራዕይ 4፥6-14

ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ ይመጣል

ለጽዮን ንጉሷ እንዲሚመጣ በአፈ ነቢያት ተነግሯታል፡፡ የሚመጣው ግን እንደነ ሰሎሞን በዝሆን ጥርስ በብርና በወርቅ ባጌጠ፤በሀምራዊ ግምጃ በተሸፈነ ሠረገላ ሳይሆን በአህያና በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ የዋህ ሆኖ ነው፡፡

የዋህ የሚለው ኀዳጌ በቀል መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጌታችን የመጣው አንገተ ደንዳና ወደ ሆነ የነቢያቱንና የካህናቱን ደም ወዳፈሰሰ ሕጉንም በወግና በልማድ  ወደ አፈረሰ ሕዝብ ነው፡፡ መጻሕፍቱን የነቢያቱንም ቃል ያነባሉ ለመቀበል ግን አይፈልጉም፡፡ ምንም እንኳ ሰይፈ በቀል በእጁ ቢሆንና ፍርድ ቢገባቸውም ሰው የመሆኑ ዓላማ ሁሉን ለማዳን እንጂ በአንድ ስንኳ ለመፍረድ ስላልሆነ በየዋህነት ተገለጠ፡፡ የነቢያትን ደም ባፈሰሰ እጃቸው የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ በመስቀል ሰቅለው ጽዋቸውን ቢሞሉም “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለቱ የምህረት እንጂ የበቀል ጊዜ አለመሆኑን አሳያቸው፡፡ የምህረት የይቅርታ ጊዜ አለ፤ከወዳጆቹ ከነቢያት ጀምሮ ላፈሰሱት ደም የበቀል ጊዜ ደግሞ ይኖራል፡፡ ዮሐ 3፥16፤ማቴ21፥33-46፤ማቴ 23፥29-36

“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው”

ሆሣዕና በዕብራውያን ቋንቋ “አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” የሚል ትርጉም አንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ሆሣዕና የሚለው ቃል ሰው ሲደነቅ ወይም ሲደሰት ከሚያወጣው ድምፅ ጋር በማመሳሰል በሌላ ቋንቋ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው እንደማይቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱም ትርጓሜ አይጣላም፡፡

አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው ቢሉ ጉዞው ወደ መስቀል ነበርና እውነተኛ መድኃኒትም እርሱ ነውና የተገባ ምስጋና ነው፡፡

ቃለ አንክሮ ቃለ ትፍስሕት ነው ቢሉም በዚያ የተሰበሰቡ አብዛኞቹ ያደረገውን ተዐምራቶች እያወሱ ይመሰክሩም ስለነበር፡፡ አንድም ከነበረው የአቀባበል ሁኔታ አንድም እንደ ኢትዮጵያ ሊቃውንት ትርጓሜ የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት ይታይ ነበርና አድናቆቱ የተገባ ነው፡፡

ሆሣዕና እያሉ የሚያመስግኑት ሁሉ“የዳዊት ልጅ” እና “ጌታ” ብለው ጠርተውታል፡፡ በዚህም የዳዊት ልጅ በማለታቸው ፍፁም ሰው መሆኑን አንድም“እግዚአብሔር ማለ አይፀፀትም ከወገብህ ከሚወጣ ከዘርህ በዙፋንህ አኖራለሁ” የተባለው ትንቢት መፈፀሙን ያጠይቃል፡፡አይሁድም በገዛ አፋቸው ክርስቶስ ማነው? ብሎ ሲጠይቃቸው የዳዊት ልጅ ነው ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ አሁን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ላለማመን ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ 2ሳሙ7፥12-14፤ማቴ22፥41-46

በ“ጌታ” ስም የሚመጣ ማለት እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሎ የሚመጣ የተባረከ ነው ብለዋል፡፡ አይሁድ “YHWH” የሚለውን በአብዛኛው የሥነ-መለኮት ሊቃውንት “ያህዌ” የሚል ግምት የሚሠጠውን በኮሬብ ለሙሴ የተገለጠ ስመ አምላክ ለመጥራት ሰለማይደፍሩ “Adonai” ወይም “ጌታ” በሚል ቀይረውታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጌታ የሚለው ቅፅል በቀጥታ ለእስራኤል አምላክ የሚነገር በመሆኑ “በጌታ ስም” “የሚመጣ” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ገልፀዋል፡፡ ማቴ 22፥41-46

ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በዕለተ ሆሣዕና ይመሰክሩ የነበሩ መጻሕፍት አንብበው ከሊቃውንት አፍ ተምረው ትንቢት የተረጎሙ ሱባዔ የቆጠሩ አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጭምር ነበሩ፡፡ አይሁድንም ይበልጥ ያስቆጣው ህፃናቱ ያመሰገኑበት መንፈስ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ተዐምር ነውና፡፡

ምንጊዜም ንፁህ ምስጋና ፣ ንፁህ ጸሎት፣ንፁህ መሥዋዕት፣ንፁህ ልቡና፣ ንፁህ አገልግሎት ይበልጡንንፁህ ሕይወት አጋንንትን፣ ክፍዎችን፣ ተንሎለኞችን፣ ተረፈ አይሁድን፣መናፍቃንን፣ አረማውያንን ያስቆጣል፡፡ ይህ እንዲቋረጥ የማያኖሩት እንቅፋት የማይፈፅሙት ድርጊት አይኖርም፡፡ ንጹሐ ባህርይ ከሆነው ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ በንፁህ ህይወት የኖሩ በንፁህ አገልግሎት የፀኑ ሁሉ ተገፍተዋል ተዋርደዋል፤ለሞትም ወደ መታረጃቸው ተነድተዋል፡፡ ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ንፁህ ሁን በዓለም ወደ ኋላ ትቀራለህ ትዋረድማለህ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ግን ትቀድማለህ ትከብርማለህ፡፡ ማቴ 14፥1-4 ዮሐ15፥18-21

ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁሉ ይዘው የተቀበሉት የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ወደ መስቀል የሚወጣ ለድል ነውና፡፡ ይህ ሁሉ የሰው አቀባበልና ምስጋና ጌታችንን ለአመል ከዓላማው አላዘናጋውም፤ ለመጣባት ለዚያች ሰዓት አዘጋጀው እንጂ፡፡ አድናቆት ሊያጅበን ምስጋና ሊነጠፍልን ይችላል፤ዓላማችን ምን መሆኑን ግን ልንረሳ አይገባንም፡፡ ከሰዎች ክብርን ብንቀበል ከእግዚአብሔር ከሆነው ክብር ከተጣልን ምን ይጠቅመናል፡፡ ሊጠቀምብህ የሚፈልግ ያወድስሃል ሊጠቅምህ የቆረጠ ግን ይገሥፅሃል፡፡ ወዳጀህን መምረጥ ያንተ ድርሻ ነው፡፡

የአይሁድ ሊቃናት እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻለችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል“ ይባባሉ ነበር፡፡ ቅንዐት ጥላቻን ይወልዳል ጥላቻ ደግሞ ሞትን፡፡ ጌታችን እንደቃሉ ወደ ትክክለኛዋ ሰዓት ቢመጣም በቁሙ ሲታይ ግን የሆሣዕና ትዕይንት በአይሁድ ሊቃናት ላይ ያሳደረው ቅንዐትና ቁጣ በሞቱ ላይ እንዲቆርጡ በከፍተኛ ሁኔታ አነሣስቷቸዋል፡፡እርሱ ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንደ ሰዓቱ ደርሶአል፡፡እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ብትሞትም ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች”በማለት በሞቱ ይበልጡ ብዙዎችን እንደሚያድንና ወደ ራሱ እንደሚስብ ነግሯቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር መንግስት ከጥንት ጀምሮ የሚጋፏት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን ከመጨመር ልዑለ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከመከተል አላስቆሙትም፡፡ ገና በሃይማኖቱ ጠንክሮ እየቆመ በኅሊና ትንሣኤ ኃጢአትን ድል አድርጎ እየዘመረ ይከተለዋል፡፡ የታመነ መሪ ነውና፡፡“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ መከተል ማለት በግብር መምሰል በአርአያነቱ መጽናት ነው፡፡ በህይወታችን በኑሮአችን ከመሰልነው በሞቱ እንመስለዋለን በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን፡፡ ክርስትና ማለት ቅሉ ይኸው ነውና፡፡ የበዓሉ ጌታ ቸርነቱ ይደረግልን! ማቴ11፥12፤ዮሐ10፥1-18፤ሮሜ 6፥5

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት

ሚያዚያ፣2008 ዓ.ም

 

 

Read more...

ስቅለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ በወልድ ስም  አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብዬ በማመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ሳያደርጉ እማር አስተምር እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና፡፡

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት አደረሳችሁ!

አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!

      ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ታላቅ ቃል የተናገረው በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም እንኳ በነቢዩ በኢሳይያስ እለተ ዓርብን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት " በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" ያለው፤ የጌታን ትዕግስቱን ሲያጠይቅ፤ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ እንጂ ለምዕመናን ጥቅም የሚሆን ቃላቶችን አልተናገረም ለማለት አይደለም፡፡

     ጌታ በመስቀል ሆኖ የተናገራቸውን ቃላት በቤተክርስቲያን "ሰባቱ አጽራሐ መስቀል" ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእኒህ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል ደግሞ ቀዳሚው(የመጀመርያው) " አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዚኢየአምሩ ይገብሩ" የሚለው ነው፡፡

ስለምን ጌታ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል በቀዳሚነት ይህን ተናገረ ቢሉ፡-

ሀ. ወደዚህ ዓለም የመጣው ለዚሁ ነውና ነው፡፡ ይኸውም ትዕዛዝን በማፍረስ ከእግዚአብሔር የተጣላውን(የራቀውን) አዳምን ካሣ ከፍሎና ቤዛ ሆኖ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ነውና ይኽንኑ መፈፀምን ከሁሉ አስቀድሞ ጌታችን ስለዚሁ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ የሚበላ ሲያቀርቡለት " እናንተ የማታውቁት የምበላው አለኝ" በማለት ሲመልስ፤ ሌላ ሰው የሚበላ ያመጣለት ሲመስላቸው ድግሞ "የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው" በማለት አስረድቷቸዋል " ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል" በሚል አስተምህሮውም ምን ያህል ለዚህች ሰዓት ዝግጁ እንደነበር አስረግጧል፡፡ ዮሐ 4፥ ፣ዮሐ 9፥

      ጌታችን የሰውን ድኅነት የመጣበትን ዕርቅ የመፈፀም ሥራ ከመደብደቡ፣ከመገረፉ፣ከመንቸንከሩ በአጠቃላይ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራም ይበልጥ ቅድሚያ ትኩረት ይሠጠው እንደነበር በዚህ እናውቃለን፡፡ ከህማሙ ይልቅ ቅድሚያ የሰጠው የሰውን ድኅነት መሆኑ በዚህ ቃል ተረጋግጧል፡፡ የመቁሰሉ የሞቱ ዓላማ ይኸው ነውና፡፡

ለ. ጠላትን መውደድን በተግባር ለማስተማር ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር " ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ ፣ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ" እንዳለ፤ ጠላቶቹ ሳለን ለወደደን ለእኛ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ለሰቃልያኑም ራርቶ ይቅርታን ለመነልን፡፡ ይህን የሚፈፅሙ ማን መሆኔን ባያውቁ ነው ሲል ይቅርታውን አበዛልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር" እንዳለ በዚህም ሰው በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ቢተላለፍ ንስሐ ከገባ ስርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኝ አስታወቀን፡፡ ለእኛም ስለይቅርታ በቃል ያስተማረንን በተግባር ፈጽሞ አብነት ሆነን እኛም እርሱን አብነት አድርገን ምን ቢበድሉን ፈጽመን ይቅር እንድንል በተግባር አሳየን ሰማዕታትም አርአያውን ተከተሉ፡፡የሐዋ.ሥራ 7፥60

. ጌታ ሌሎቹን ስድስቱን ተናግሮ ይህን ትቶ ቢሆን ኖሮ በኋላ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ወልደ ማርያም ሲሰቀል ወልደ እግዚአብሔር ተለይቶት ነበር ለሚል የስህተት ትምህርታቸው ይመቻቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመስቀል የተሰቀለው፣ መከራን በነሣው ሥጋ የተቀበለው እርሱ በመስቀሉ ላይ ሳለ በመከራው ሰዓት "አባት ሆይ" ብሎ በመጣራቱ መለኮት በለበሰው ሥጋ መከራን ተቀበለ ሞተ…ወዘተ የሚለውን እውነተኛ ትምህርት አጸና፡፡ ይህን ትቶ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" "ተጠማሁ" ወዘተ…የሚለውን ብቻ ተናግሮ ቢሆን ለስህተት ትምህርታቸው ማስረጃ ባደረጉት ነበር፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ከሥጋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳ እንዳልተለየ በዚህ አውቀን ተረዳን፡፡ዕሩቅ ብእሲ(ፍጡር) እግዚአብሔርን " አባት ሆይ" ብሎ ይጠራ ዘንድ አይቻልምና፡፡ እርሱም ተከሶ የተሰቀለበት ምክንያት ይኸው ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል" እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሐር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡" ዮሐ 5፥18

በተጨማሪም ያቺ ሰዓት የይቅርታ የምህረት እንጂ የክስና የፍርድ ሰዓት አልነበረችምና ለሰቃልያኑ እንኳ ምህረትን አደላቸው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ" እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ከቁጣም የራቀ ምህረቱም የበዛ ነው ሁልጊዜም አይቀስፍም ለዘላለምም አይቆጣም እንደ ኃጢአታችንም አላደረገብንም፤ እንደበደላችንም አልከፈለንም " እንዳለ፤ በዮሐንስ ወንጌልም " በእርሱ የሚያምን ሁለ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና፡፡" ጌታም " ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም" በማለት ያቺ የይቅርታ ሰዓት በእርሱም ሆነ ከርሱ ርቀው በኖሩ ፍጥረቶቹ በጽኑ ናፍቆት ትጠበቅ ስለነበር ነው ይቅርታውን የገለፀባት፡፡ ዮሐ 3፡16

     ለሰቃልያኑም ዕድሜ ለንስሐ ሰጣቸው፡፡ ምናልባት በጊዜ ስቅለቱ የተፈፀመውን ዓይተው ሊድኑ ለሚችሉ የመዳን ዕድልን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም የሆነውን ዓይተው ፍፁም አምላክነቱን የተረዱ ፈያታዊ ዘየማንና የጭፍሮች አለቃ የነበረው አምነው መስክረዋል፡ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እና "ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር" በማለት፡፡ ሉቃ 23፥39-43፤ ማር 15፥39

    ለሌሎቹም በስቅለቱና በሞቱ ባያምኑ ዜና ትንሣኤውን ሲሰሙ ምናልባት አምነው ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ 40 ዘመን ታገሣቸው፡፡ ይህም የይቅርታውን ስፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ተጠቅመውበታል፡፡ ያልተጠቀሙበት ግን በ70 ዘመን ጥጦስን አስነስቶ ቀጥቷቸዋል፡፡


 

        ጌታ " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" በሚለው ቃሉ በመስቀሉ ላይ" ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ ጌታ በልደቱ ተፈጥሯችንን፣ በጥምቀቱ ጥምቀትን፣ በፆሙ ፆምን፣ጸልዮ ጸሎትን አንዳች ሳይኖረው ኑሮ መንኖ ጥሪትን፣የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ትህትናን፣ታግሦ ትዕግስትን፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሰማዕትነትን ወዘተ…ፍፁም እንዳደረጋቸው ይቅር ብሎም ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ እርሱ በዚያ ሰዓት የፈፀመው የይቅርታ ሥራ ተከታይ ተቀፅላ የማያስፈልገው የማይደገም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው፡፡

      የአዳም በደል(ኃጢአት) ፍፁም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትን የሠራው ከባህርዩ አንቅቶ ሳይሆን በዲያብሎስ ተታሎ ነውና፡፡ የዲያብሎስና የአዳም በደል ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የኃጢአት የስህተት የሐሰት ሁሉ ነቅዑ ዲያቢሎስ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ዲያብሎስን "…እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ  የሐሰትም አባት ነውና" በማለት የክፋት ሁሉ ምንጩ መነሻው ዲያብሎስ እንደሆነ መስክሮበታል፡፡ ሰው ከዲያብሎስ ያልተማረው ከራሱ አንቅቶ የሠራው ወደፊትም የሚሠራው ኃጢአት የለም አይኖርምም፡፡ ዮሐ 8፡፡  ጌታ የተንኮል ምክሩን እስኪያፈርስበት ድረስ የዲያብሎስ ጥረትም ይኸው ነበር፡፡ ሰውን አዘቅት ውስጥና፤ አምላኩንና የቀደመን መልኩን(ክብሩን) በመርሳት በድንቁርና ጨለማ ተውጦ በመዳኑም ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር ቅዱስ እግዚአብሔርም አዳምን እንደ ዲያብሎስ ይህስ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ከሚጨምር በቀር የቀደመ ሕይወቱ ናፍቆት አይደለም የመዳን ምኞት የሌለው ነው በማለት ከማዳኑ ቸል እንዲለው ተመኝቶ ነበር፡፡

      ምንም እንኳ በመጽሐፍ "በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም " ቢባልም በየዘመናቱ የአዳምን ዘር ወክለው የድኅነትን ምኞትና ተስፋ አንግበው በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት የሚታዩ ቅዱሳን አልጠፉም፡፡ መዝ 13፡ 1-3

     ይልቁንም ዲያብሎስ በአዳም ዘር ውስጥ ከርሱ ባህርይ ከምትገኝ ንጽህት ዘር ተወልዶ እንደሚያድነው የሰጠው ተስፋ፤ያቺ ንጽህት ዘርም እንደ ሚያበራ ንፁህ ዕንቁ በአበው አካልና ባህርይ ውስጥ ስትፋለስ መምጣቷ ኃጢአት በአዳም ላይ ባህርያዊ እንዳይሆንና ዲያብሎስም የተመኘው እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ" ተፈፀመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል"(የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ) ያለው እኛም "ምክሀ ዘመድነ" ምክንያተ ድኂን (የባህርያችን መመኪያ የድኅነታችን ምክንያት) የምንላት፡፡

    በመሆኑም ፈፅሞ በበደል ከእግዚአብሔር የይቅርታ ድንበር ውጪ ያልሆነውን አዳምን የበደለው በምክረ ከይሲ ተታሎ እንጂ ከባህርይ አንቅቶ እንዳልሆነ ጌታ ሲመሰክርለት " የሚሠሩትን አያውቁምና" አለ፡፡ አውቆ አጥፊ እና በስህተት የሚበድል እኩል አይሆንምና በዲያብሎስ ቅጣት ለአዳም ድኅነት ተፈረደ፡፡ አንድም

      አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ፍፃሜውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልዓ" እንዳለ፣ ዲያብሎስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን እንዳያስተውሉ ቢጋርድባቸው ነው እንጂ፤ ኃጢአት ምን ፍዳ እንደሚያመጣባቸው ፈፅመው ጠንቅቀው ቢረዱ አሁን የሚሠሩትን አይሠሩትም ነበር ሲል ነው:: ዛሬም ጊዜ እንኳ ሰው ይህን ቢያውቅ ዘላለማዊው ቅጣትም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ቢረዳ ዛሬ የሚሠራውን ባልሠራው ነበር፡፡ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑ በራሱ እጅግ አስጨናቂ ነውና፡፡ ቅዱሳን ኃጢአትን ብቻ ያይደለ በዓለም ያለ ግብርን ሁሉ እንደ ምናምን ቆጥረው እርግፍ አድርገው ትተው በፍፁም ኃይላቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸውና በፍፁም ልባቸው ጌታን የሚከተሉ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትንና ምረረ ገሃነምን በመረዳታቸው ነው፡፡

      ጌታ በመስቀል በነበረባት በዚያች ሰዓት ራሱን ፍፁም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት፤ ዘላለማዊ ካህን (አስታራቂ) እና ይቅር ባይ(ታራቂ) በመሆን አቀረበ፡፡

      አዳም ከፈጣሪ ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ጸጋው በመገፈፉ ጠባዩ በማደፉና ባህርይው በመጎስቆሉ የተነሳ ይኸው በዘሩ ተጋብቶ የጠብን ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ሊገኝ አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉ በኃጢአት ስለተያዘና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው እርቅን ማምጣት አልቻለም፡፡ከአዳም ጀምሮ የነበሩ  ታላላቅ አበው፣ከሙሴ ጀምሮ የተነሱ ነቢያት ከአሮን አንስቶ የነበሩ ካህናትና ከእያሱ ኋላ የተነሱ መሣፍንት ዳዊትንም የተከተሉ ነገሥት በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት መሥዋዕት ኃጢአትን በደልን ማራቅ ህዝቡንም ከህዝቡ ማስታረቅ አልቻሉም ነበር፡፡

     በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ስለህዝቡ ኃጢአት መስዋዕትና ምልጃ ከማቅረባቸው በፊት ስለራሳቸው ኃጢአት መስዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ ድኅነት ጊዜያዊ እርቅ ከማምጣት ያለፈ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እነርሱም ህዝቡን እንደጥላ(ምሳሌ) በነበረችው ድንኳንና የኦሪት ሥርዓት ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተከትሏቸው ይወርዱ ነበር፡፡ እነርሱም የበለጠ ሊያድናቸው ወደሚችል በብርቱ ጸሎትና ምልጃ ይቃትቱ ነበር፡፡ " አንሥዕ ኃይለከ ወነአ አድኀነነ"(ኃይልህን ግለጥና መጥተህ አድነን) እያሉ በዘመናቸው ሁሉ ይጮኹ ነበር፡፡

    ከዚያም በላይ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ድረስ በኩላብ ተቸንክረው በመጋዝ ተተርትረው ደማቸው ቢፈስም ለዓለም አይደለም ለራሳቸውም ቤዛ መሆን አልቻለም የኒህ ሁሉ ደም ይካሰስ ይፈራረድ እንደሆን እንጂ ይቅርታን ሰላምን ሕይወትን አንድነትን አላመጣም፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ "እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡ጽድቁንም እንደ ጥሩር ለበሰ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ…" እንዳለ የተፈረደውን ፍርድ ሊያስቀር የሚችል እንደሌለ ባወቀ ራሱ ወደዚህ ዓለም መጣ ሥጋንም ለብሶ ተገለጠ፡፡    ኢሳ 59፡ 15-17

     ጌታ ዓለሙን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ሲገለጥ ክህነቱ(የማስታረቅ አገልግሎቱ) ከብሉይ ኪዳን ካህናት በእጅጉ የራቀና የመጠቀ ነበር፡፡

፩. የብሉይ ካህናት መሥዋዕት ሲያቀርቡ መጀመርያ ለራሳቸው ቀጥሎ ለህዝቡ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለ ኃጢአት ያለ ነውር ስለተገለጠ  ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሲናገር " ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ዕብ 5፥5-4

፪. የብሉይ ካህን በዘር ጨምሮም በቅዱስ ቅባት ተቀብቶ የክህነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ሰያሜ ካህናት የሆነው ጌታ ግን ከማንም አልተቀበለውም፡፡ ስለ እርሱ እንደተባለ" አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ" ሿሚ የለበትም፡፡ዕብ 5፥5-6

፫. የብሉይ ካህን ጊዜአዊ እርቅን የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሊያሰጥ የሚችል የፍየልና የኮርማዎች ደም ያቀርብ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሥጋን ነፍስን ደመ ነፍስን የሚቀድስ ክቡር ደሙን አፍስሶና ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ አስታረቀን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ" የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ፤ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?" በማለት ገልፆታል፡፡ ዕብ9፥13-14 

     ጨምሮም "…የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ "መስዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ፡፡በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተፃፈ አምላኬ ሆይ ፍቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ" ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትና ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደህግ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህ ላደርግ መጥቻለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም ፊተኛውን ይሽራል በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡" በዚህም ቃል በግልፅ ቃል መሥዋዕተ ኦሪት ተሽሮ መስዋዕተ ሐዲስ እንደተተካ ይህ የሆነበት ምክንያትም የኃጢአት ሥርየት ማምጣት አለመቻሉና መለኮታዊውንም ፍርድ አለማርካቱ መሆኑን አትቷል፡፡ዕብ 10፥4-10

     የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የእውነተኛይቱ ምሳሌ በምትሆን ቅድስተ ቅዱሳን በዕለትና በዓመት ኃጢአትን ሊያስወግዱ የማይችሉበትን መስዋዕቶች ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ምሳሌይቱ ሳይሆን አማናዊ ወደሆነችው ቅድስት አንድን መስዋዕት አንድ ጊዜ አቅርቦ ኃጢአትን በማስወገድ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "… ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሰዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ  ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሺር አንድ ጊዜ ተገልጦአል…" ጨምሮም  " ሊቀ ካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡" በማለት ጽፏል፡፡ዕብ 9፥24-28፤ ዕብ 10፥11-12

      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የማስታረቅ አገልግሎቱን በራሱ ብቻ አላስቀረውም ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደራሴው በመሆን በእርሱ ተገብተው በሚሠውት የእርሱ ሥጋና ደም በእምነት ለሚቀርቡ ሁሉ ጊዜአዊ ያይደለ ዘላለማዊ ድኅነትን ፍፁም ይቅርታን ለምዕመናን ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ"…ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤ በደላቸውም አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ " በማለት የአዲስ ኪዳን ካህናት ከብሉይ ካህናት ምን ያህል የሚበልጥ የክህነትን ክብር እንደተቀዳጁ ጽፏል፡፡ 2ቆሮ 5፥18-21

     ከላይ በተብራራው ላይ መሥዋዕቱ እርሱ መሥዋዕቱን አቅራቢውም እራሱ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ ሌላው በዚሁ የምናየው ነጥብ ተወካፌ መሥዋዕቱ እርሱ ራሱ መሆኑንም ነው፡፡ በአዳም የሞትን ፍርድ የፈረደበት እርሱ፤የይቀርታን የድኅነትን ቃል " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቀር በላቸው" በማለት አወጀልን፡፡ በዚህ ቃል የጠብ ግድግዳ ፈረሰ የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ለሰው ዘር ፍፁም ካሣ ተክሶ አዳምም ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም" እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው" ብሏል፡፡ አክሎም " እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግደግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡" በማለት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንዴት እንደታረቀን አስተምሯል፡፡ኤፌ 2፥13-16፤ቆላ 2፥13-15

     በአዲስ ሥርዓት በሆነ ደሙ ላጠበን ከበደላችንም ሁሉ ላነፃን ይቀርታውንና ምህረቱን ላበዛልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም መቼም መች ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!

ይቆየን!

ጥር 2005 ዓ.ም

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 

Read more...

ኒቆዲሞስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ኒቆዲሞስ፡- ጌታችን ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ መምህር ጋር የነበረውን ቆይታ የምናስብበት ሰንበት ነው፡፡

ምስባክ፡- ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ

        አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመጻ በላዕሌየ

        ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለእመሕያው፡፡

ትርጉም፡- ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ

        ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም

        የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፡፡

- ክቡር ዳዊት ከንጉሡ ሳዖል ጋር በነበረው ጠብ የተናገረው ነው፡፡ ምንም እንኳ ሳዖል ቢከፋብኝም ካንዴም ሁለቴ በእጄ ጥለኽው ፈተንኸኝ፡፡ እኔ ግን እንደሆነብኝ ልሁንበት እንዳደረገብኝ ላድርግበት የሚል ክፋትን፣ ቂም፣ በቀልን በልቤ አላገኘኸብኝም፡፡ በአፌም እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም ከማለት በቀር ጠላትህን በእጅህ ጥሎልሃል ከሚሉ ጋር ተባብሬ አልተገኘሁም ሲል ነው፡፡

         ዳዊት ምን ያህል የዋህና ኃዳጌ በቀል መሆኑን መጽሐፍ “ዳዊት ከሳዖል ልብስ ዘርፉን በመቁረጡ አዘነ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ የስንት ወንድሙን አንገት በሰይፍ፣ የስንት ወገኑን አንጀት በረሃብ፣ የስንት ባልንጀራውን ተስፋ የተሞላ ሕይወት በመድኃኒት፣ስንቱን ትዳር በነገር ቆርጦ ሲጥል ቅንጣት የማይሠማው ጨካኝ በሞላበት ዓለም እንዲህ ዓይነት ልብ እንደምን ያለ ነው?

          ሊገድለው ሠራዊት አስከትሎ የወጣ በተደጋጋሚ ጦር ወርውሮ የሳተ ለመግደል ቁርጥ ህሊና ያለው ጠላት ላይ የማይጨክን ክንድ እንዴት የተባረከ ነው? በዚህ ዓለም ስንቱ በጠላቱ ያይደለ በወዳጁ፣ በባዕድ ያይደለ በዘመዱ፣በመጻተኛ ያይደለ በወገኑ ላይ ግፍ ሠራ፡፡ ዳቦ ሲጠብቅ ድንጋይ፣ ዓሣ ሲለምን እባብ አቀረበለት፡፡

         ቅዱስ እግዚአብሔር ማዕምረ ኅቡዓት ልብ የሠወረውን ኩላሊት የሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ከኅሊና አስቀድሞ የሚመረምር ከሀሳብ አስቀድሞ የሚፈትን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሰው ከሰው ተሠውሮ እንዲሠራ አይደለም፡፡ጽድቃችን ይሁን ኃጢአታችን፣ነውራችን ይሁን ክብራችን በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ የቦታ ርቀት የጨለማ ጽናት ልዑሉን አይጋርደውም፡፡ ሁሉን ያያል ሁሉን ያውቃል ሁሉን ይመረምራል፡፡ ኪዳን ዘነግህ

         የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ” ያለ በግብፅም ምድር ሆነ በከነዓን የእግዚአብሔር ዓይኖች የተገለጡ መሆናቸውን በማወቁ ነው፡፡ በፍትወት ተቃጥላ በኃጢአት ሠክራ የነበረች የጲጥፋራ ሚስት ግን ይህን ማስተዋል የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ዘፍ 39፥7-11

        ሰው ኅሊናው በፍትወት ሲሸነፍ በኃጢአት ፍቅር ሲማረክ ጌታ እግዚአብሔር በሁሉ የሚገኝ መሆኑን ለማየት አዕምሮው ይጨልማል፡፡ ቅዱስ አምላኩን በሥራ ለመካድ ደግሞ የሚመርጠው ጨለማን ነው፡፡ ይህም ኅሊናው ከእግዚአብሔር በመለየቱ የወደቀበትን ጨለማ ያሳያል፡፡ ጌታም “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም” በማለት ኃጢአትንና ክፉ ሥራን የሚወዱ ከጨለማ ጋር ያላቸውን ዝምድና አስታውቋል፡፡ ዮሐ3፥20

        ህፃናት ጥፋት ሠርተው የሚቀጡ መሆናቸውን ሲያውቁ ከቤተሰብ ይደበቃሉ፡፡ሲደበቁ በዋናነት የሚሠውሩት ከሌላው ሰውነታቸው ይልቅ ፊታቸውን ነው፡፡ በእነርሱ የአስተሳሰብ ደረጃ እነርሱ የማያዩት ሁሉ ሊያያቸው አይችልም፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

        ነቢዩ ዳዊት ግን “ዓይንን የፈጠረ አያይምን ጆሮንስ የፈጠረ አይሰማምን…” በማለት ልዑሉን ይገልፀዋል፡፡ በእኛ አነጋገር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ፡፡ መዝ 93፥7-10 በቅዳሴም “እግዚአብሔር ያያል ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” በማለት ማወጁ ወደ ኅሊናችን እንድንመለስ አይደለምን? ቅዳሴ እግዚእ ቁ.፲፫

ስለ ኒቆዲሞስም “በሌሊት ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም” ማለቱ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ በሌሊት ሲመጣ ሁሉን በሚያውቅ በእርሱ ፊት በተንኮል እንዳልቀረበ ያጠይቃል፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደጌታ የሄደ በተንኰል ሊያጠምደው ወይም እንደ ሌሎቹ ረበናተ አይሁድ በጥያቄ ሊፈትነው አልነበረም፡፡ የእስራኤል መጽናናት በእርግጥ ጊዜው እንደደረሰ ለማወቅ እንጂ፡፡

እንደሌሎችም “ይህ የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? የሚል ቃል በአንደበቴ እናገር ዘንድ አልወደድሁም፡፡ ይልቁን “… እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን በማለት ከመመስከር በቀር፡፡ አመጣጡ መልካም ስለነበር ጌታችን ታላቅ የሆነ ከእግዚአብሔር ልጅነት የሚገኝበትን ምሥጢር ገልፆለታል፡፡ ዮሐ 3


 

ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ፡- ፫

       እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደመራን መፍቀሬ ሰብዕ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሥጢር ላይ ቆይታ እናደርጋለን፡፡

            ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነበር፡፡ ስለጌታችን በሚያየውና በሚሰማው ነገር ልቡናው ስለተቀሰቀሰ በሌሊት ይመጣ ዘንድ መንፈሱ ግድ አለው፡፡ በቀን ያልመጣው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡

፩. በሌሊት ኅሊና በሚታዩና በሚሰሙ ነገሮች ስለማይታወክ ክት(ይሰሰባል) ይሆናል፡፡ ስለሆነም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በሚኖረው ቆይታ ኅሊናን በሚከፍሉ ነገሮች ላለመረበሽና በሚሠማው ለመጠቀም ሰዓተ ሌሊቱን መርጧል፡፡ አበው ለጸሎትም ቢሉ መጻሕፍት ለመመልከት የሌሊቱን ጊዜ መምረጣቸው ለዚሁ ነው፡፡ አንድም

፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነው፡፡ በዕድሜ ከሚያንሰውና ከማንኛው ረቢ(መምህር) የት እንደተማረ ከማይታወቀው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ቃልን ሊጠይቅ ሲሔድ የሚያዩት ሁሉ፤ይህ ሰው ትምህርት ሳይጠነቅቅ ቀርቶ ኑሯልን ብለው እንዳይተቹት ስሙን(ደረጃውን) ለመጠበቅ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይመስላል፡፡ ለባለስልጣኑም ሆነ ለተራው፤ለባለጠጋውም ሆነ ለድሀው፤ ለትንሹም ለትልቁም መለኮታዊው ጥሪ(ግብዣ) በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቀርቧል መልስ መስጠት የየራሳችን ድርሻ ነው፡፡ ማቴ 22፥1-8

         ስንቶችን የሥልጣን ደረጃቸው ወይም አዋቂዎች ተብለው የተሠጣቸው ወንበር ወደ ሕይወት ለመቅረብ ግድግዳ እንደሆነባቸው እናውቃለን፡፡ የተማረ ወይም ባለስልጣን ወይም ታዋቂ ከሆነ በእግዚአብሔር ቤት መገኘት በካህናት እግር ሥር ተቀምጦ መማርን ራስን ከማዋረድ እንደሚቆጥር ግልጽ ነው፡፡

       የምድራችን መሪዎችና ታላላቆች በምክረ ካህን ሲኖሩ በአደባባይ በፀሐይ ፊት ለጌታ እግዚአብሔር ሲሰግዱ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይሾምና፣ ይሽር፣ያከብርና ያዋርድ ባለጠጋም ሆነ ነዳይ ያደርግ ዘንድ ሁሉን ቻይ ነውና፡፡ በእግዚአብሔር መታመናችን ከክብር ውርደት ወይም የፖለቲካ ክሰረት የሚያመጣብን አይደለም፡፡

        ባለመድኃኒት ራስህን ፈውስ ነውና በቤተክህነቱም ላሉ የሕዝብ አለቆች የሚበጅ የኒቆዲሞስ መንፈስ ነው፡፡ ትምህርት የማያስፈልገው ምክር የማያሻው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ ወንበሩ ታላቅ ቢሆንም ተቀማጩ ሰው መሆኑን ያስብ፡፡

፫. አይሁድ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር(የሚያምን) ቢገኝ ከምኩራባቸው ሊያወጡት ተስማምተው ስለነበር፤ ኒቆዲሞስ በግልጥ ለመምጣት ያልደፈረው አንድም በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ዮሐ 9፡ 22

        ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ በሕይወቱ ላይ የታየው ለውጥ በወንጌላቱ ተመስክሯል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳዊያን የዳስ በዓል በሚከበርበት ዕለት ጌታችንን እንዲይዙት የላኳቸው ሎሌዎች በትምህርቱ ከመደነቃቸው የተነሣ የተላኩበትን መፈፀም ተስኗቸው በተመለሱ ወቅት ሲበሳጩ ኒቆዲሞስ “… ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ተከራክሯል፡፡ ዮሐ7፥50-52

      ይህም በአይሁድ ሸንጎ ስለጌታችን የተከራከረ የመጀመሪያው ሰው ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ ጌታ በተሰቀለባት ዕለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ሥጋውን ከመስቀል አውርዶ የገነዘ ይህ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚያች ደቀመዛሙርቱ እንኳ አይሁድን ፈርተው በተበተኑባት ዕለት በድፍረት የጌታን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር መምጣቱ እርሱ መሢህ መሆኑን በፍፁም ልቡ አምኖ ለመቀበሉ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዮሐ 19፥38-42

       ከአይሁድ ሊቃናት መካከል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመንና በድፍረት ለመጋፈጥ የመጀመሪያ የሆነው ኒቆዲሞስ ከጌታችን ጋር በተነጋገረባት በዚያች ሌሊት “የእስራኤል መምህር ተብሎ መጠራቱ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

      ኒቆዲሞስ የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር በግልፅ ከተነገራቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ደረጃውን ከደቀመዛሙርት መካከል እንደ አንዱ ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔርን በንፁህ ልብ መከተል ምንኛ መልካም እንደሆነ በዚህ እናያለን፡፡

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲነጋገር እንደሳምራዊቷ ሴት ወይም እንደ ስምዖን ፈሪሳዊ ወዘተ… በተለመደ ቃላትና ቀለል በሚል ሀሳብ አልጀመረም ታላቅ በሆነ ምሥጢርና ተሰምቶ በማያውቅ ቃል እንጂ፡፡ ይህም ከእኛ ወዲያ ላሳር ለሚሉ ፈሪሳውያን አላዋቂነታቸውን የገለጠ ነው፡፡

አንድም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፡፡ ነገር ግን የዚህችን ዓለም ጥበብ አይደለም፤የሚሻሩትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን፡፡” እንዲል ከእውቀቱ ብስለት የተነሣ የአይሁድ ሸንጎ አባል የእስራኤል መምህር ለሆነ ለእርሱ ምስጢር መናገርን የተገባ ሆኖ ስላገኘው ነው፡፡ 1ቆሮ 2፡ 6


 

መድኃኒታችን “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ” በማለት በእግዚአብሔርና በምዕመናን ዘንድ የሚደረገውን የአዲስ ኪዳን ማሠሪያ ውል ነግሮታል፡፡ምሥጢሩም ከአእምሮው በላይ መሆኑ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በሚል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ ምሥጢራት ምስጢር መባለቸው ቅሉ ከሰው አእምሮ በላይ በመሆናቸው እንጂ የተሸሸገ ነገር ኖሯቸው አይደለም፡፡

         በምሥጢረ ጥምቀት ሰው በካህኑ እጅ ጸሎት ተደርጎ ሲጠመቅ የሚታይ አገልግሎት ይፈፀማል በቅዱስ ቅባትም(ሜሮን) ይታተማል፡፡ በዚህ ወቅት በሚታይ አገልግሎት(ሥርዓት) የማይታይ ጸጋን እናገኛለን ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅነት ነው፡፡

        ከእግዚአብሔር መወለዳችንን በምን እናውቃለን ቢሉ በእምነት ነው፡፡ በሥጋ የወለዱንን በእምነት እንደተቀበልን መንፈሳዊውም ይኸው ነው፡፡ ወላጅ መውለዱን ያውቃል ልጅ መወለዱን ያምናል፡፡

          በእናቱ ማኅፀን ያለ ተወልዶ ካልሆነ በቀር የዚህን ዓለም ብርሃን ማየት አይችልም፡፡ወላጆቹን ዘመዶቹን ሁሉ ማወቅ መገናኘት አይሆንለትም፡፡ እኛም በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለድን የእግዚአብሔርን መንግስት ብርሃን ማየት አይቻለንም፡፡እንደ ወላጅ ሥሉስ ቅዱስን እንደ ዘመድ የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑ ቅዱሳንን መገናኘት አይሆንልንም፡፡ መወለድ ወደዚህ ዓለም መግቢያ በር እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ለመንፈሳዊው ዓለም(ለእግዚአብሔር መንግሥት) መግቢያ በር ነው፡፡

      ጌታችን ይኽን ምሥጢር በነፋስም ምሳሌ ቢነግረው ሊረዳው ስላልቻለ “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታቸንን አትቀበሉትም፡፡ ስለ ምድራዊው ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” የሚል ተግሣፅ ተነግሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ በአእምሮው ሊገነዘበው ያልቻለን ነገር ለማመን አለመፈለጉን ጌታ አውቆበታል ሃይማኖት ግን ከሥጋዊ ደማዊ አእምሮ እጅግ የራቀና የረቀቀ ምሥጢር ስለሆነ ከእውቀቱ ማነስ የተነሣ ከማመን እንዳይዘገይ የተሠነዘረ ተግሣፅ ነው፡፡

      በልዑል እግዚአብሔር ባህርይና በሀልዎቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም በሃይማኖት የሚፈፀሙ ምሥጢራትና ተዐምራቶች ሁሉ ከአእምሮ በላይ ናቸው፡፡ በእኔ የእውቀት ልክ ስላልሆኑ አልቀበልም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ይህን የሚል የራሱን ሁኔታ ጭምር መካድ ውስጥ ይገባልና፡፡ ምክንያቱ የሰው ተፈጥሮና ማንነት በራሱ ከሰው አእምሮ በላይ ነውና፡፡

- ለኒቆዲሞስ የነፋስን ምድራዊ ምሳሌ አቅርቦ ሲያስረዳው ስላልገባው ከነፋስ ይልቅ ረቂቅ የሆነ የመንፈስን ነገር ቢነግረው እንደማያምን አስረግጦለታል፡፡ አንድም

በምድር የሚፈፀመውን የጥምቀት ሥርዓት አምነህ መቀበል ካልቻልክ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊና መንፈሣዊ ልደት አምነህ መቀበል እንዴት ይቻልሃል? ሲለው ነው፡፡ አንድም በአፈ ነቢያት በቃለ መፅሐፍት የተነገረውን በኅቱም ድንግልና የሆነ ምድራዊ ልደቴን ብነግራችሁ ካላመናችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያለመቀዳደም ያለመበላለጥ የሆነ ሰማያዊ ልደቴን ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ሲል ነው፡፡

          ለጥቆም “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ ማንም የለም፤እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት የሚነግረው ሁሉ እንደነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በሚል ከባህርይ እውቀት ባልመነጨ ሁኔታ ሳይሆን በባህርዩ የሚያውቀውን በጌትነቱ ያዘጋጀውን መሆኑን ነግሮታል፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ንግግር ሲጀምር “…እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለት ወደ እስራኤል በተለያየ ጊዜ እንደሚላኩ ነቢያት ወይም መምህራን ቆጥሮት ነበርና ለዚያ የተሠጠ መልስ ነው፡፡ እኔ ነቢይ ወይም መምህር ብቻ ያይደለሁ የነቢያት ጌታ የመምህራን እውቀት ነኝ፡፡ እነርሱ በሰሙት ቃል በተገለጠላቸው ራዕይ ይናገራሉ እኔ ግን የሰማያት ምሥጢር ባለቤት እንደመሆኔ በባህርይ እውቀት እነግርሃለው፡፡ አንድም

ከሰማያት(ከልዕልና) በፈቃዱ ሰውን ለማዳን የወረደ፤ኋላም ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞ በሥልጣኑ በክብር ወደ ሰማይ የሚወጣ ከእኔ በቀር የለም ሲለው ነው፡፡ በውሱን አካል ቢገለጥም ምሉዕነቱ እንዳልተለወጠ ያጠይቃል፡፡ ውሱን የሰው አካል ምሉዕ ሆነ፤ምሉዕ(የማይወስነው) መለኮት በሥጋ ተወሰነ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ቦታውን ሳይለቅ ምድር ደርሶ ጨለማን እንደሚገልጥ፤በልቡና ያለም ሀሳብ ከልብ ሳይለይ በቃል በጹሑፍ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥም እንዲሁ ነው፡፡

       አያይዞ “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” በማለት ተናገረ፡፡ ኒቆዲሞስ በአጭር ቆይታ የአዲስ ኪዳን መልክ ምን እንደሚመስል ተስሎለታል ሁለቱ ቁልፍ ነገሮች በጥምቀት የእግዚአብሔር መንግስት ዜግነት የሚገኝበትንና፤በጌታችን ሞት የዓለም ድኅነት የሚፈፀም መሆኑን ገለጠለት፡፡

    ጌታችን እንደሚሞትና ሞቱም በምን ዓይነት መንገድ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጥ የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡ የሞቱም ዓላማ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መሆኑን ጭምር አስረዳው፡፡

ወገኖቼ እነሆ የክርስትና መልክ፡- በክርስትና ምንጊዜም ማመንን መከራ፣ጥምቀትን ሞት፣ሞትን ትንሣኤ ይከተለዋል፡፡ ይህ ከሌለ መንገዱ ላይ አይደለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀትን ምንነት ሲገልጥ “…ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?... ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡” ብሎታል፡፡ በግልጥ በስሙ የተጠመቅን በሞቱ ልንመስለው ቃልኪዳን ገብተናል፡፡ በሞቱ ያልመሰሉት በትንሣኤው አይመስሉትምና፡፡ሮሜ 6፥1-23፤ቈላ 2፥8-15

በጥምቀት ለኃጢአት እንሞታለን፣አሮጌው ሰውነታችንን እንሰቅላለን፣በሕግ ከሚመጣ እርግማን ነፃ እንወጣለን፡፡ በአንፃሩ በሕይወት እንኖራለን፣አዲሱን ሰው እንለብሳለን፣ከጸጋው በታች እንሆናለን፡፡

      ቤተክርስቲያን ለዚያ ነው ወዲያው እንደተጠመቅን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በማቀበል ሞቱን እንድናስብና በሞቱ መተባበራችንን እንድናትም የምታደርገን፡፡ ያልተጠመቀ የጌታን ሥጋውን ደሙን መቀበል እንደማይችል ሁሉ ተጠምቆም የጌታችን ሥጋና ደም ሳይቀበል የሚሄድ ክርስቲያን ሆኗል ልንል አንችልም፡፡ ሊነጣጠሉ አይችሉምና፡፡

          ይህንኑ ለማመስጠር ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለጥምቀት ሲነግረው ከቆየ በኋላ አከታትሎም ስለ ስቅለቱ የነገረው፡፡ ለጥምቀታችን የሆነው ማየ ገቦና ለቁርባናችን የሆነ ደሙ የፈሰሰ በመስቀል ላይ በስቅለቱ ጊዜ ነውና፡፡ ከአዳም ጎን ሙሽራው ሔዋን እንደተገኘች ከዳግማዊው አዳም ከክርስቶስም ጎን ሙሽራው ቤተክርስቲያን ተገኘች፡፡ ዮሐ 19፥33-35

          ክርስቲያኖች ሆይ በወላጆቻችን ክንድ በዮርዳኖስ ለመጠመቅ ስንቀርብ ተቀብሎን ልጅነትን ሰጥቶናል፡፡ ቀጥሎ የሚጠብቀን የቀራንዮ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ቀራንዮ የሚኬደው ግን በራስ ጽናትና በፍፁም እምነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተጠምቂያለሁ ብቻ ብለን የምንቆመው ለዚህ ነው፡፡ ክርስቶስን በፍፁም ኑሯችን ልንመስለው ግድ ነው፡፡ እኛን መስሎ የተገለጠ እርሱን በመምሰል እንከብር ዘንድ ነውና፡፡

        ወገኖች ሆይ የአንድ ሰው በጨለማ ወደ ጌታችን መሔድ ለስንቶች በሕይወት ብርሃን የሚሆን መንገድ እንደገለጠ ተመልከቱ፡፡ የአንድ ሰውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያደርገው የልብ ግንኙነት ለዓለም ጥቅም እንደሚሆን አስተውሉ፡፡

በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት በክህደት፤ጽድቃችንን በኃጢአት፣ንፅሕናችንን በርኵሰት ሳናጎድፍ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሠጠች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይደግፈን! አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Read more...

ዐቢይ ፆም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

እስከ ቅርቡ ጽሑፍ አነሣው የነበረውን አሳብ ተግ አድርጌ፤አዲስ የምጽፈውንም ሚያዝያ እስኪብት አቆይቼ በያዝነው የፆም ጉዳይ ላይ ልጽፍላችሁ መልካም መስሎ ታየኝ፡፡

በቀኖና ቤተክርስቲያን ከተደነገጉት ዓበይት አፅዋማት አንዱ ፆመ ኢየሱስ (ዐቢይ ፆም ወይም ሁዳዴ) አንዱ ነው፡፡ ጌታ ስለፆመው ፆመ ኢየሱስ ወይም ዐብይ ፆም፤ ሁሉ ተስተካክሎ ስለሚፆመውም “ሁዳዴ” ተብሏል፡፡ የሁዳድ እርሻን ሁሉ በህብረት እንዲሰራው በዚሁ አንፃር ነው፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እፀድቅ  አይል ጻድቅ፣ እቀደስ አይል ቅዱስ፣እነፃ አይል ንፁህ፣ ኃይል መንፈሳዊ አገኝ አይል ኃይል የባህርዩ የሆነ፣ ከኃጢአት ሥርየት ለማግኘት አይል “የዓለምን ኃጢአት የሚያስተሠርይ የእግዚአብሔር በግ” የተባለለት መስተሥርዬ ኃጢአት፣ፍትወታት እኩያትን አስታግስ አይል ከድቀት በፊት የነበረ የቀዳማዊውን አዳም ክብር ይመልስ ዘንድ የተገለጠ ዳግማዊ አዳም ስለምን ፆመ? ቢሉ መልሱ እንዲህ ነው፡፡

ጌታ ሥጋን ተዋህዶ በዚህ ምድር ሳለ የሠራውን ሁሉ ሰለ ዐራት ምክንያት አድርጎታል፡፡

፩. ለቤዛ(ለካሣ) ዓለም

፪.ለአጽድቆተ ትስብዕት( ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ)

፫.ለአቅርቦተ ሰይጣን(ሰይጣን አቅርቦ ለማሠር)

፬. ለአርአያነት ነው፡፡

ሦስቱን ጊዜ በፈቀደ እስኪገልጣቸው  የፆሙን እንመልከት ተያያዥነቱ ከአራተኛው ጋር ነውና፡፡

፩. ጌታ የፆመው “ለአርአያነት” ነው፡፡ ፈጽሞ ቅሉ “ከመዝ ግበሩ”(እንዲህ አድርጉ)” ማለት የተመቸ ነውና፡፡ መልካም መምህር ተናግሮ ማስረዳት ፈፅሞ ማሳየት አርአያ ትቶ መምራት  መገለጫው ነውና፡፡ ከዚህ የወጣ መምርነት የለም፡፡ በአፍ ብቻ ቢለፈልፉ ኪያስፈርድ በቀር ረብ ጥቅም አይገኝበትም፡፡ ስለጌታችን ግን ቅዱስ ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና” ሲል ገልፆታል፡፡ ይህም ጹሞ ሙ፣ጸልዮ ጸልዩ፣ ታግሦ ታገሡ፣ አፍቅሮ ተፋቀሩ… ወዘተ፡ ማለቱ አይደለምን? 1ጴጥ 2፥21

፪. ጌታችን የመጣ ኦሪትንና ነቢያትን ሊፈፅም ነውና ትንቢታቸውን ፈጽሞ ኑሯቸውን ኑሮ የነቢያቱን እውነተኛነት አተመ፡፡ ክቡደ መዝራዕት ሙሴ በሲና ኤልያስም በቀርሜሎስ ሌሎችም ዓበይትና ደቂቀ ነቢያት ፆምን አብዝተው ይፆሙ ነበርና “ተቸግረው ወይንም የማያስበላና የማያስጠጣ ጋኔን አድሮባቸው ሳይሆን ከፈጣሪያቸው ኃይል መንፈሳዊን የተቀበሉበት አምላካዊ ምስጢራትን ያዩበት ረቂቀ መንገድ መሆኑን ለማስረገጥ ጌታም ፆሞታል፡፡ በዚህም የነቢያቱን ፆማቸውን አተመ መንገዳቸውንም አፀደቀ፡፡ ማቴ 5፥17 ማቴ 11፥18

፫. አጋንንትን ፍትወታት እኩያትን ድል የምንነሣበትን ኃይል መንፈሣዊ እንዴት እንድናገኝ ሲያመለክተን ፆመ ፡፡ ጌታን በፆሙ ወቅት ዲያቢሎስ በስስት ቢመጣበት በትዕግስት፣በፍቅረ ነዋይ ቢመጣበት በጸሊዓ ነዋይ፣ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ድል ነስቶታል፡፡ በዚህም ከዲያቢሎስም ሆነ ከባህርያችን የሚመጡብንን ፈተናዎች እንዴት ባለ መንፈሳዊ ጥበብ እንደምናሸነፍ ገልፆልናል መንፈሳዊው ትጥቅና የጦር አሠላለፍ መልኩ ይህ ነው፡፡ በድካም ውስጥ ያለ ኃይል፡፡ ጥበብ በዚህ አለ ልብ ያለው ልብ ይበል! 2ቆሮ 102-5

፬. መምራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፆሙን በምድረ በዳ አደረገው፡፡ ይህም ህሊናችንን ከምግብና ከመጠጥ በሥጋ ከሚሆንም ተድላ ደስታ ሀሳብ ሁሉ ለዩት ሲለን ነው፡፡ መዓዛ መባልዕቱን በአጼንዎ ህሊና እያሸተቱ ፤ የማዕዱን ዓይነት በዓይነ ህሊና እየላሱ መፆም “ቁጭት” እንደሆን እንጂ ፆም አይሆንም፡፡ በፆም የምንማረው አምላካዊ ታላቅ ምሥጢር “ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር” ነውና፡፡ በዚህ ወቅት ሰውነት(ነፍስና ሥጋ) ከመብል ከመጠጥ ርቆ በመንፈስ ሠረገላ መጥቆ የእግዚአብሔር መንግሥቱንና ጽድቁን በመመኘት ሀሴት ያደርጋል፡፡ ጊዜው ላመሉ ሲደርስ ለቁመተ ሥጋ ያህል ያለ ሀሳብ ብዛት ያስተናግዱታል፡፡ ስለ እንጀራ ብቻ የሚያስብ ከዲያቢሎስ ስለፆም፣ ስለጸሎት ስለተጋድሎ የሚያስብ ከክርስቶስ መሆኑ በገዳመ ቆሮንቶስ ተለይቷል፡፡

ጌታችን ምድረ በዳውን ለመናንያን ባርኮ ሠጣቸው ይህ ባይሆን ቅሉ ምድራውያን መላእክት የበረሃ ከዋክብት የተባሉ አበው ባልተገኙም ነበር፡፡ እነርሱም በዓለም ያለ መብል መጠጥ ሹመት ባለጠግነት ሳያምራቸው በፆም በጸሎት ጽሙዳን ሆነው ባለቤቱን እርሱን መስለው ኖሩ በመንግስቱም ባለሟሎች ይሆኑ ዘንድ ተገባቸው፡፡

እንስሳትም ሆኑ አራዊት ከተወለዱባት ደቂቃ ጀምረው የሚያስቡ ስለ ምግባቸው(ሆዳቸው) ነው፡፡ ያለፈ ታሪክ አይጠይቁም ከእነርሱ በፊት የነበሩት በምን ተጠቀሙ በምንስ ተጎዱ ብለው አይመረምሩም፡፡ ለወደፊትም ፈጣሪያችን የሚደሠትበት የበጀ ሥራ እንሥራ ብለው አይጨነቁም፡፡ እንግዲህ ሰውም ነጋ ጠባ ስለሆዱ ብቻ የሚያስብ ከሆነና ያለፈን መርምሮ ለወደፊቱ ተምሮ የማይኖር ከሆነ ከእንስሳት በምን ይለያል? ልጆቹም በምግበ ሥጋ ብቻ የሚያሳድግ ቤተሰብ ሥራው እንስሳት ከማርባት በምን ይሻላል?

ወደ ሕይወት መድኃኒት እንቀርብበት ዘንድ ቀድሶ የሠጠንን ፆም እንደተለመደው ያይደለ እንደሚገባው ፆመን ዋጋ የምናገኝበት ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱን ደጅ እየጠናን በዐቢይ ፆም ውስጥ ሰለምናሳልፋቸው(ሰለምናከብራቸው) ሰንበታት በድርበቡ እንመልከት፡፡

በዓቢይ ፆም ውስጥ የሚገኙ ተሰዓቱ ሰንበታት የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው...


 

፩.ዘወረደ፡- በሌላ ስሙ ፆመ ሕርቃል በማለት ይታወቃል፡፡ ንጉሥ ሕርቃል/Heraklis/ በፋርስ ንጉሥ መከራ የፀናባቸውን ክርስቲያኖች ነፃ ለማውጣት ሲዘምት በፆም በጸሎት እንዲያስቡት በመጠየቁና ዘመቻውም በስኬት ሰለተጠናቀቀ ያን ለማዘከር ይፆማል፡፡

በዋናነት ግን ዘወረደ በተባለው ሳምንት የምናስበው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት መውረድና በሥጋ መገለጥ ነው፡፡ በዚህ ዕለት የሚሰበከው ምስባክና የሚነበበው ወንጌል እንደሚከተለው ነው፡፡

ምስባክ፡- ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት

        ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ

        አፅንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዓዕ እግዚአብሐር መዝ ፪፥፲፩

ምክር፡- ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ የመከረን ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ”ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ” አለ የተገባ ነውና፡፡ በሌላው ዝርዝር ሳንገባ የመግደልም ሆነ የማዳን ፈርዶ ሲዖል የማውረድም ሆነ ይቅር ብሎ ለዘላለም ደስ ማሰኘት የልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡ እኔ እገድላለሁ አድንማለሁ፤እቀስፋለሁም ይቅርም እላለሁ ከእጄ የሚያድን የለም ጨምሮም እርሱን ፍሩት ነፍስንና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሃነም ሊያጠፉ የሚችለውን ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዘዳ 32፥39፣ማቴ 10፥28

ፍርሃት የልቡና ድንጋፄ የናላ ረዓድ የጉልበት ነው፡፡ ለጌታ እግዚአብሔር በፍርሃትና በረዓድ ሆናችሁ በመገዛታችሁ ደስ ይበላችሁ፡፡ አንድም ኃይል ከጉልበት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ በፆም በጸሎት በስግደት በውስጥ(በልብ) በአፍአ(በጉልበት) እየተገዛችሁ ኃይል ሥጋዊን በማድከማችሁ ደስ ይበላችሁ እርሱ ኃይል መንፈሳዊን ያድላችኋልና፡፡ “ኃይሌ በድካም ይፈፀማልና” ጸጋዬ ይበቃሃል እንዲል፡፡ 2ቆሮ12፥9

የጌታ እግዚአብሔር ቁጣ በላያችሁ እንዳይሆን ጥበብ መንፈሳዊን አጽንታችሁ ያዙ፡፡ ጥበብ መንፈሣዊ የተባለውም ፈሪሃ እግዚአብሔር፣አምልኮ ሠናይ፣ጸሊዓ እኩይ፣ተፋቅሮ፣ትህትና ጾም ጸሎት ምፅዋት ወዘተ… እና ከከርሠ መጻሕፍት ከከናፍረ ሊቃውንት የሚገኝ ምክር ሁሉ ነው፡፡ አንድም ጥበብ የተባለ ጌታችን ነው፡፡ አጽንታችሁ ያዙ አለ በእርሱ ማመንን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱንና እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የማያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ አያመልጥም፡፡ በአድስ ኪዳን ታላቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ልጅ አለማመን ነው፡፡ ዩሐ 3፥16-21 ፣ ዩሐ16፥7-11፣1ዩሐ 5፥10-12፣ 1ዩሐ4-2 ተመልከት በእርሱ ማመን ማለትም ወረደ ተወለደ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ ዐረገ ዳግም ይመጣል ብቻ ብሎ መናገር ሳይሆን ለምን ወረደ? ተወለደ? ለማንስ ተሰቅሎ ሞተ? በትንሣኤውስ ምን አገኘን? እኔስ የትንሣኤው በርሃን(ድል) ተካፈይ ነኝ ወይ? ወዘተ----እያሉ በውሳጣዊ ህሊና በማስተንተን በህይወት መግለጥ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በእኛ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ካላመጣ ስመን ብቻ ክርስቲያን ተብሎ መሸከም ከፍርድ አያስጥልም፡፡

የሚነበበው ወንጌል ዩሐ 3፥10-24

በዚህ ምንባብ ውስጥ ያለውን ተዝቆ የማያልቅ ምስጢር ለጊዜው ታግሠን በሁለት ነጥቦች ላይ እናተኩር፡፡

፩. የሰማያዊው ልደት ምሥጢር ምስክርነት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ በስሙ ያመንን የእኛ ሰማያዊ ልደት ምሥጢር የተገለጠው በጌታችን ምድራዊ ልደት ነው፡፡ እርሱ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት ተወልዶ ቅድም ዓለም ያለእናት ከአብ የተወለደውን ሰማያዊ ልደት ገለፅልን፡፡ ጌታችን በኒቆዲሞስ በተናገረው ቃል ላይ “ስለምድራዊ ነገር ስነግራችሁ ያለመናችሁ ስለሰማያዊው ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ? ሲል ምድራውያን ስለሆናችሁ ስለእናንተ ሰማያዊ ልደት ስነግራችሁ ያለመናችሁ ከዓለም አስቀድሞ ስለሆነ ስለእኔ ልደት ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ ሲል ነው? አንድም ሰለምድራዊ ልደቴ ስነግራችሁ ካለመናችሁ ስለሰማያዊው ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ? ሲል ነው፡፡

ሰማያዊውን ምሥጢር ሊገልጥ የተገለጠ ብቸኛው ከሰማይ የወረደው በሰማይም ያለው እርሱ ነው፡፡ በዚህ ቃሉም በሥጋ ቢወሰንም ምሉዕ ሰፋሕ ከመሆን እንዳልተለወጠ አስረዳ ምስክርነቱ ግን አልታመነም፡፡ ኢሳያስም“ ምስክርነታችንን ማን አመነ?“ ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ያየነውንና የሰማነውን እውነት መመስከር ግድ ነው፡፡ ይኸውም ህይወት ተገለጠ ዓይተንማል ሰምተንማል ሕይወት እንዲበዛላችሁ በእርሱ ፍቅር ኑሩ ብሎ መመስከር ነው፡፡ በምስክርነታችን በሰዎች ዘንድ አክራሪ፣ ሥራ ፈት ወይም ሌላ እነደሆንን ተቆጥረን መላገጃ ልንሆን እንችላለን፡፡ ክብራችንም ይኸው ነው፡፡

፪.የእግዚአብሔር ፈቃድ በልጁ መገለጥ:- የጌታ እግዚአብሔር የዘመናት ዕቅድ ሁሉ ይድኑ የክብሩም ወራሾች ይሆኑ ዘንድ ነው፡፡ ይህም በአንድያ ልጁ ሞት ተረጋገጠ፡፡ ይህን ፍቅር ለመግለጥ ልብ ይደክማል፣አእምሮ በአንከሮ የሸነፋል፣አንደበት በዝምታ ይታሠራል፣ቃለትም ይፈራሉ፡፡ የባርባሮስ ጥልቀት የሰማያትም ምጥቀት የረቂቁም ሆነ የግዙፉ ዓለም ስፋት ይህን ፍቅር ሊሸከመው ሊገልፀው አይችልም ምትክ ከሌለው ልጅ በላይ ጠላትን መውደድ በአብ ዘንድ፤ከራስ በላይ ጠላትን መውደድ በልጁ ዘንድ ምን ይደንቅ? በወንጀለኛ ተገብቶ ካሣ ሞትን ወስዶ ህይወትን ማደል እኔም በአባቶቼ መንፈስ ጌታ ሆይ እጠይቅሃለው ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ከሌሎች ይልቅ እስከዚህ ትደርስለት ዘንድ ሰው የመሆን ምሥጢር ምንድር ነው?

*በዘወረደ በትህትና ወርደን በመንፈስ መጥቀን የምናስበው ይሔን ነው!


 

፪. ቅድስት፡- በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባባት የቅድስና ህይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ስለመሆኑና እኛም እንዴት መኖር እንዳለብን የምንመካከርበት ነው፡፡

ምስባክ፡- እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ

        አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ

        ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤የሚል ነው፡፡ መዝ ፺፭፡፭

ሲተረጎም፡- እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ

          ሃይማኖትና ምግባር በፊቱ ነው

          ቅድስናና ታላቅ ምስጋናም በመቅደሱ ውስጥ ማለት ነው፡፡

-እውነት ነው ከእርሱ በቀር ሰማያትን የሠራ በክብርም ያስጌጣቸው የለም፡፡ የተሠሩትም ለጥቅማችን ነው፡፡ ለፍጡራን መኖሪያና(እርሱ ባወቀ) ለብርሃናት መመላለሻ ከመሆንም ባለፈ የቃሉን ብርታት የክብሩን ገናንነት የሚመሰክሩ ኃይላት ናቸው፡፡“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ“ እንዲል ዳዊት፡፡ የልዑል እግዚአብሔርን ታላቅነት በጥቂቱ እንኳ ለመረዳት ብትሻ በሌሊት በጠፈር ሰምይ እንደስንዴ የተዘሩትን ከዋክብት ተመልከት፡፡ መዝ 18፥1

በህዋሳይንስ known Universe(የታወቀ ዓለም(ህዋ)) እና Unknown Universe(ያልተደረሰበት ዓለም(ህዋ)) የሚባል አለ፡፡ በታወቀው ዓለም(ህዋ) ከመቶ ቢልዩን በላይ የሆኑ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከእንዚያ  አንዱ የእኛይቱ ያለችበት ጋላክሲ ሚልክዌይ ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ጋላክሲ ብቻ ከ300-500 ቢሊዮን የሚደርሱ ከዋክብት እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከመቶ ቢልዮን በላይ ባሉ ጋለክሲዎች ስንት ከዋክብት ሊኖር እንደሚችል ገምት ለዚያውም በታወቀው(በተደረሰበት) ህዋ (Known Universe)፡፡ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ትችሉ እንደሆነ የሰማይ ከዋክብትን ቁጠሩ፤እርሱ ግን ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድ  ስንኳ አይታጣውም፡፡ኢዩብ 38-39፣ ኢሳ 40፥18-26፤መዝ

ልብ በል እኒህ ሁሉ ሰማያትን፣ለማሰብ እንኳ የሚከብዱን ግዙፍ ዓለማት በልዑሉ ዘንድ ግን እፍኝ እንኳ አይሞሉም፡፡ ለዚህ ነው ኤሊሁም“ እነሆ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤እኛም አናውቀውም“ ቅዱስ አጲፋንስዩስም “ከሰማነው በላይ ግሩም ነህ፤ከተነገረንም በላይ ድንቅ ነህ“ በማለት በአንክሮ የቃተቱት፡፡ ኢዩብ 36፥26 ቅዳሴ ኤጲፋንዩስ

-ገናንነቱን እንዲህ ነው ብለን ልንናገረው የማንችለው አምላክ ሃይማኖት ምግባር በፊቱ ነው ይህ ማለት የሰው ሁሉ ሃይማኖትና ምግባር በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ የሚሠወረው የለም ሲል ነው፡፡ አንድም ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብረው በቅድስና በምስጋና በመቅደሱ ፀንተው የሚኖሩ በፊቱ በክብር ናቸው ሲል ነው፡፡ አንድም በሃይማኖት በምግባር የጸኑ ሰዎች የእግዚአብሔር መቅደስ የሆነ ሰውነታቸው በቅድስናና በክብር ምስጋና የተጌጠ ነው፡፡

ሃይማኖትና ምግባር እንደነፍስና ሥጋ የተዋሃዱ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ነፍስ እንዳለው የሚታወቀው የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋውን ስታንቀሳቅሰው ነው፡፡ እርሷ ባትታይም በሥራዋ ሀልዎቷ ይታወቃል፡፡ ሃይማኖትም የሚታይ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ ሃይማኖት የሚታይ የሚዳሰሰው በምግባር ግዘፍ ሲነሣ ነው፡፡ ፆም ደግሞ የትሩፋት መግቢያ በር ነው፡፡ የአንዲት ሃይማኖት ተከታይ የሆነም በራሱ ፍልስፍና መጓዝ አይገባውም፡፡ ይልቁን የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና በመጠበቅና በመፈፀም ሃይማኖቱን በምግባር ይገልፃል እንጂ ፡፡ ያዕ 2፥14-26

የሚነበበው ወንጌል ማቴ፮፥፮-፳፬

ምንባቡን አንዱት ኃይለ ቃልን ማዕከል አድርገን እንመልከተው፡፡

-እንግድህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ይበረታ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ኃይለ ቃል እንደ ማሠሪያ ነው የተጠቀመው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ለነፍስ ብርሃንነት የሚጠቅሙ ዋና ነገሮችን አስተምሯል፤፤ ምፅዋት ፆምና ጸሎት ዛሬ ስለሆዳቸው አብዝተው በሚጨነቁ ሰዎች እንደሚነሣው ፆም ያስፍጋል አያስፈልግም? መቼ እንፁም? ከምን እንፁም? ወዘተ… ዓይነት ጥያቄዎችን በጌታ ጊዜ አልተንሡም፡፡

ጸሎት ምፅዋት አስፈላጊነታቸው እንደማያጠያይቅ ሁሉ ፆምም አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ ስለሆነ በምን ዓይነት መንፈሣዊ ይዘት መፆም እንዳለብን ብቻ ነው መመሪያ የተሠጠን፡፡

ፆምን ስንፆም ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንድናሟላ ተነግሮናል፡፡

፩. ለታይታ እንዳናደርገው፡፡ ሰው ጦመኛ መሆናችን ቢያውቅ ከማድነቅ ባለፈ ዋጋ አይሠጠንም የጦማችንን መስዋዕት በረሃብ እሳት ተቀብሎ ዋጋ የሚሠጠን በስውር የሚያየን የሰማይ አባታቸን ብቻ ነው፡፡ ለሚጦሙ ለሚፀልዩና ምፅዋትን ለሚወዱ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ የሰማይ አባታችሁ ዋጋችሁን በግልጥ ይከፍላችኋል በማለት ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ያለቸውን ሕብረት አረጋግጧል፡፡ ጦምን የሚነቅፉ ህብረታቸው ከማን ጋር ይሆን? እኒህን ድንጋይ ዳቦ እንዲሆኑ በል ከሚል ጋር ወይስ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በማለት ድል ከነሣ ጋር?

፪.በጦማችን ወቅት ለሌሎች መራራትን ስንጦም ለምግባችን ይውል የነበረውን ገንዘብ በከርሠ ነዳያን ውስጥ ከማኖር ይልቅ የጦሙ ወራት ሲያልቅ ለመጠቀም በሚል ብናኖረው ጦማችን ረብ ጥቅም አይኖረውም፡፡ እኛ ወደን ፈቅደን ከምግበ ሥጋ ስንከለከል ሳይወዱ በምግብ እጦት የሚጨነቁትን ማሰብ የክርስትና ግዴታ ነው፡፡

ሰውነታችን ከምግብ ሊከለል ነፍሳችን ከስስት፣ከፍቅረ ነዋይ፣ከጭካኔ፣ከትዕቢት ወዘተ…ካልጦመች እየተገዛን ያለነው ለገንዘብ(በቁሙ) እና በገንዘብ ተገዝቶ ሆድን ለሚሞላ ምግብ እንጂ ለእግዚአብሔር አይሆንም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት እንደማይቻል በፆምና ለስስት፣ለምፅዋትና ለፍቅረነዋይ፣ለትህትናና ለትዕቢት ወዘተ…ባንዴ ማደር አይቻልም፡፡

ይህን ከመከረ በኋላ ጌታችን ዓይን የሰውነት ብርሃን መሆኗን፤ዓይን ታማሚ ከሆነች ሰውነት ሁሉ እንደሚጨልም አይነተኛ ምሳሌ ከተናገረ በኋላ፤የሰውነት ብርሃን የምትሆን ነፍስም በመስገብገብ በግብዝነት በሀኬተኛነት ጉድፍ ከተበላሸች የከፋ ጨላማ እንደሚሆንብን አስጠንቅቋል፡፡ ነፍስ ብሩህ የምትሆነው ጦምን ጸሎትን ምፅዋትን ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ተዘክሮተ ሞትን አፅንታ ስትይዝ ነው፡፡ ነፍስ በቅድስና ብርሃን ካጌጠች የነፍስ ለሥጋ የሥጋ ቅድስና በአፍአ ላለው ሁሉ ይተርፋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን የህይወታችን ብርሃን ይጨልማል፡፡ ለሥጋ ብርሃን ሕይወት የምትሆነው ነፍስ እንደሆነች፤ለነፍስ ብርሃኗ ሕይወቷ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሥጋ ነፍስ ስትለየው ይሞታል፡ነፍስ ደግሞ ጌታ እግዚአብሔር ሲለያት ትሞታለች፡፡


 

፫. ምኩራብ፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ወደ ምኩራብ አይሁድ ገብቶ ገበያውን እንደፈታ በቤተክርስቲያን የምናስታውስብት ነው፡፡

ምስባክ-እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዓኒ

      ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕለየ

      ወቀዳዕክዋ በጾም ለነፍስየ

ትርጉም፤-የቤትህ ቅንዐት እንደ አሳት በላኝ

        አንተን የተገዳደሩህ ተግዳሮት በእኔ ላይ ደረሰ

        ነፍሴን በፆም ቀጣኋት      መዝ ፷፰፥፱

ለጊዜው ለይሁዳ መቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው፡፡ በመቃቢስ ጊዜ አንጥያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ መከበርና መቀደስ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማያሰጉት ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡ ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑ ሥፍራዎች(ቤተመቅደስ) ታቦታት፣ንዋያተ ቅዱሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው፡፡ መጽሐፈ መቃብያን፣ትን.ዳን 5፥1-ፍፃሜ፣ መዝ104(5)፥14-15፣ ዘኁ 12፥1ፍፃሜ፣ማቴ 10፥40፤1ሳሙ 4-6

በክርስትና ስንኖር መጠንቀቅ ያለብን ልዑል አምላክ በሠራልን ሕግና ሥርዓት ለመሔድ ነው፡፡ እኛ ሕግ ሐጋጊዎች ሥርዓተ ደንጋጊዎች አይደለንም፡፡ በቤተክርስቲያንም ከሰው የሆነ ሥርዓት የለም፡፡ በጥምቀቱ በቁርባኑ በቅዳሴው በማሕሌቱ በጸሎት በፆም በበዓል አከባበር ሥርዓቱ ሁሉ በጥንቃቄ መጓዜ እንጂ "ምናለበት" በሚል የቸልታ መንፈስ፣ወይም በራስ ሕግ መመራት ከጸጋው ይለያል በመቅሠፍት ያስጎበኛል፡፡ ለመሆኑ ራስህ በሠራኸው ሕግና ሥርዓት በቤተእግዚአብሔር ልኑር የምትል አንተ ማነህ? ይህን ሥርዓት ለቤቱ ከሠራ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትወዳደር ዘንድስ ምንደር ነህ? የአባቶቻችን ህግና ሥርዓት የምትንቅስ ከእነርሱ የተሻልክ ሆነህ ተገኝተህ ነውን? እንደ እውነቱ የራስህን እንኳ ህይወት በህግና በሥርዓት መምራት ያልቻልክ፤እፈፅመዋለሁ ብለህ ቃል የገባኸውን ለመፈፀም በምክንያት ልምሾ ሆነህ የታሠርክ አንተ እንደምን የእግዚአብሔርን ቤት ህግ ለመተቸት የተሻለ ህግም ለማውጣት ትደፍራለህ?

የቤቱ፣የሥርዓቱ፣የአምልኮቱ፣የቅዱሳኑ፣ቅንዓት እንደ እሳት በሚበላው በሠራዊት ጌታ ፊት ድርሻህን እወቅ፡፡ ደርሻህ በተደነገገልህ ህግ በተሠራልህ ሥርዓት ፀንተህ መኖር ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግዳሮት ነው፡፡ አመድና ትቢያ መሆንህን አስብ!!

ሥጋ የነፍስ መሣሪያ ነው፡፡ መልካምም ክፉም ትፈፅምበታለች፡፡ ነፍስ ከተለየቸው ሥጋ ሀዘን፣ደስታ፣ፀፀት፣ህመም፣ሀፍረት፣ትዕቢት ሌላም ሌላም ስሜቶች አይኖሩትም በድን ነው፡፡ ሥጋ ሲጦም ረሃብ ሲሠማ ስሜቱን ነፍስና ሥጋ ይጋሩታል፡፡ ዳዊት ነፍሴን በፆም አስመረርኳት(ቀጣኋት) ያለው ለዚህ ነው፡፡ አስተውል ነቢዩ ፆምን ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አልሠጠም መሪዋ አንቀሳቃሿ ተጠቃሚዋ እርሷ ናትና፡፡ ነፍስ አልቦ ፆም የለም፡፡ ስለዚህ በፆም ነፍሳችንን እንቅጣ እንጂ በዓለም ድንቃ ድንቅ፣በወዘበሬታ፣በሥራ በመወጠር የረሃብ ስሜታችንን ለማጥፋት(ለመርሳት)አንሞክር፡፡ እኛ የረሳነውን(ትኩረት የነፈግነውን) እርሱ ይቀበል ዘንድ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ተረቱስ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይሸከመውም አይደል፡፡ ከረሃብ ስሜታችን ጋር በመቆየት ፆማችንን ማስባረክ ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡

ወንጌል ዮሐንስ ም፥፲፪—፳፭

ጌታ ኢየሱስ ራሱን ከገለጠ በኋላ ወደኢየሩሳሌም ሲወጣ የመጀመርያው ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ከቤተመቅደስ አስወጥቷቸዋል ሁለቴም ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ቀንና በዕለተ ሆሣዕና በቤተመቅደሱ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሰዱቃውያን ብዙ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚዎች ስለነበሩ ድርጊቱን ከመቃወም ይልቅ ያበረታቱ ነበር፡፡ የአንድ አገር መንግስት በሌላ አገር ግዛት ውስጥ የዜጎቹን ደኅንነት የሚከታተልበት ጉዳያቸውን የሚከታተልበት ወደራሱ አገር ለሚገቡ ሌሎች ዜጎች ፈቃድ የሚሠጥበት(ቪዛ) ቆንስላ(Embassy) እንደሚኖረው፤ቤተመቅደስም የሰዎች ነፃ ፈቃድ በሰለጠነበት ዓለም የምትገኝ የሰማያዊው መንግስት ቆንስላ(Embassy) ናት፡፡ የዜጎቿን መንፈሳዊ ድኅነት በጸሎት በትምህርት በመከራ ትጠብቃለች፤ አዲስ ለሚመጡት በጥምቀት የሰማያዊ ዜግነት ፈቃድ ትሠጣለች፡፡ ይህንንም በባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴዎች ካህናት ታስፈፅማለች፡፡ የቤተመቅደስም የካህናትም አገልግሎት ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ከወጣ ቤተመቅድሱንም በአሠራር ቅርፁ ብቻ ካህናቱንም በአለባበስ ካህናት ለማለት ይቸግረናል። በአውሮፓ በአሜሪካ ወደሙዝየምነት የተቀየሩ አብያተ መቅደሶች አንዳሉ እንሰማለን በአሠራር ቅርፃቸው ብቻ ግን አሁንም ቤተመቅደስ ብለን አንጠራቸውም፡፡ በትያትር በፊልም ካህናት መስለው የክህነት ልብስ ለብሰው የተወኑትም የእውነት ካህናት ናቸው ብለን አንወስድም የታላቁ ሰማዕት የአቡነ ጴጥሮስ ተውኔት አብራር አብዶ(ሙስሊም) መተወኑን የምናሰወታውሰው ነው፡፡ ስለዚህ ቤተመቅደስና ክህነት የይዘት አንጂ የቅርፅ የውስጥ እንጂ የአፍኣ አይደለም፡፡

ጌታ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት በመፈፀም ቤተመቅደሱን ሊያጠራው ወደ ዓላማው ሊመልሰው ፈቃደ ተቀባይ ስላላገኘ የተፈታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ጌታ ቤተመቅደሱን በተደጋጋሚ “ያባቴ ቤት” ብሎ ይጠራው ነበር በመጨረሻ ግን እሱን ባለማመን አምጸው ሲፀኑ “ቤታችሁ” ብሎታል፡፡ ክርስቶስ የሌለበት የእግዙአብሔር መቅደስ የለምና፡፡ሉቃ19፣ ማቴ 23፤ አንድም

በቤተመቅደሱ የነበሩት እንስሳት ለተለያየ ዓይነት መሥዋዕት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡ የአዲስኪዳን መሥዋዕት እና ሊቀካህናት የሆነው መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተመቅደሱ እንስሳቱንና ርግቦችን ማስወጣቱ መሥዋዕተ ኦሪት መሻሯን፤ ካህናተ ብሉይን መቃወሙም ለአዲስ ስርዓት የአዲስ ኪዳን ካህናት ይሾም ዘንድ እንዳለው ያጠይቃል፡፡

በዚህ ወቅት ጌታ የተጠየቀው ይህን ለማድረግ ስላለው ሥልጣን ምልክት እንዲያሳይ ነበር፡፡ እርሱም ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን አነሣዋለሁ ብሏቸዋል፡፡ አስተውል እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ፡፡ በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ፡፡ (የትንሣኤውን ምስጢር በጊዜው ጊዜ እናመጣዋለን)

በገለጠው ቃል ውስጥ ግን የሰውን አካል እንዴት ባለ ክብር እንዳከበረው አስታወቀ ቅዱስ እግዚአብሔር ቃሉን ከድንጋይ ድላት ይልቅ በልባችን ላይ ሊጽፍ፤በሸራ ድንኳንም ሆነ በድንጋይ፣በዕብነበረድ፣ በወርቅ፣ ከሚሠራ ቤተመቅደስም ከምናመልከው ይልቅ በሰውነታችን መቅደስ ብናከብረው ይወዳል፡፡

አባቶቻችን ወደ ሲና ተራራ ወጥተው ቃሉን የሕዝቡ ልብ አምሳል በሆነው በድንጋይ ድላት ይዘው ወረዱ፤በአዲስ ኪዳን ወደ ቀራንዮ ተራራ ወጥተን ቃሉን ፍቅሩን ቃልኪዳኑን በልባችን ጽላት ተሸክመን ወረድን፡፡

በተለያየ ዘመን የተሠሩት ቤተ መቅደሶች የመፍረስ ግዳጅ ደረሠባቸው፡፡ አሁን ግን ክፉዎች ደርሰው ሊያፈርሱት በማይችሉት መቅደስ ላይ ይመለክ ዘንድ የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይኸውም የምዕመናን ሰውነት ነው፡፡ የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕያው ቤተመቅደስ የሰው ልጅ፡፡ 

በዚህች ዕለት ቤተክርስቲያን ልጆቿን ራሳቸውን ህያውና ቅዱስ መሥዋዕት፣ዘላለማዊ መቅደስ አድርገው እንዲያቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ ትለምናለች፡፡ በእንዴት ያለ ክብር እንዳከበረን አስተውሉ፡፡ የኃያሉ ንጉስ የዘላለማዊው አምላክ መቅደስ የቅዱስ መንፈሱም ማደርያ እንሆን ዘንድ የተመረጥን እኛ ማን ነን? ከልባችን ሕሊናችን ከሥጋችን ላይ የዓለምን ሸቀጥ ማራገፍ ዛሬ ይጠበቅብናል፡፡

ሥጋችን በክርስቶስ መዓዛ ከብሯል፣በቅዱስ ቅባቱ ወዝቷል፣ በንፅህና ልብስ አጊጧልና ሌላ አያስፈልገውም። ንፅኅናህን ባለመጠበቅ ግን ለሰዎች ምሬት ሁን እያልን አይደለም በፈቲው ጦር ሌሎችን ወግቶ ለመጣል ሁሉን ወደራስ ስቦ ለመደነቅ የተዘጋጀ መንፈስህን ለማውገዝ እንጂ፡፡ የነፍስ ክርፋት በሽቶ፤የሥጋ ርኩሰት በልብስ አይሠወርምና፡፡


 

፬ መፃጉዕ፤- በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማንን ስለመጎብኘቱና ከብዙ ዘመን ጀምሮ በደዌ ተይዞ የኖረ ሰውን ስለማዳኑ ይተርካል፡፡

ምስባክ፡- እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ

        ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምጸዌሁ

        አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሀለኒ፡፡

ትርጉም፡- በሕማሙ አልጋ ሳል እግዚአብሔር ይረዳዋል

ከደዌውም ምንጣፉን ሁሉ ይመልስለታል

አቤቱ እኔ ይቅር በለኝ አልሁ

ነቢ ዳዊት በመዝሙሩ ብዙ ጥልቅ ነገሮችን ያነሣል አበው በአጭሩ ሲገልፁት መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አፍ አድሮ ያልተናገረው ነገር የለም ይላሉ፡፡ በቤተክርስቲያን ብርቱ ጸሎት ተደርጎ የሚታመነውም ለዚሁ ነው፡፡

ነጠላ ትርጉሙን ስናየው ለድኆች የሚራራ ሰው ከሚገጥመው ችግር እንዴት እንደሚታደገው የሚናገር ነው፡፡ ቢታመም ይረዳዋል ፈውስንም ልኮለት የደዌ ሽታ ያለበትን ምንጣፉን ሁሉ የጤና መዓዛ በሚያውደው ምንጣፍ ይለውጥለታል፡፡ በምንጣፉ እያለ የእግዚአብሔርን ይቅርታ ደጅ ጠንቷልና፡፡ 

አንድም፡-አንደ ኢዮብ ያለ ጻድቅ በዲያብሎስ ተንኮል በሕመም በቁስል ተመትቶ በአልጋው ቢተኛ እግዚአብሐር ይረዳዋል አለ ያስችለዋል፡ ያስታግሠዋል ሲል ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ሃይማኖቱን ተመልክቶም ከደዌው ይፈውሰዋል፡፡ የደዌ ሽታ ያለበትን ምንጣፍ ለውጦ በጤና በሀሴት የሚተኛበት ምንጣፍ ይሠጠዋል፡፡ ኢዩብ በድያለሁ ይቅር በለኝ ከማለት ውጪ ክፉ አልተገኘበትምና፡፡

አንድም፡-አዳም ባለመታዘዝ ደዌ ተይዞ ሳለ እግዚአብሔር ወልድ አካሉን አካል ባህርዩን ባህርይ አድርጎ“ ነሣዓ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ”እንዲል ታሞና ካሣ ክሶ ይረዳዋል ማለት ያድነዋል፡፡ በኃጢአት መርዝ ታሞ የተኛበት አልጋም ጠረኑ መልካም አልነበረም፡፡ ሰው በጽኑ ደዌ ተይዞ ሲተኛ ከሰውነቱ በሚወጣ የተለያየ ፈሳሽ የአልጋው ምንጣፍ እንደሚበላሽ፤ጠረኑም እንደሚከፋ አዳም በበደለ ገዜ መዓዛ እግዚአብሔር ተለየው ጸጋው ራቀው በፍትወታትና እኩያት በኃጢአትና በርኩሰት መዓዛ ቅድስናው ተበላሸ፡፡

በመሆኑም ያደፈ ጠባዩን የጎሰቆለ ባህርዩን አድሶ ቀድሞ ወደተፈጠረበት አርአያ እግዚአብሔር ሊመልሰው እሱኑ(አዳምን) ሆነ፡፡ ሰው በመሆኑም በኃጢአት፣በርኩሰት፣በሞት በመቃብር፣በመፍረስ በመበስበስ በሲዖል ምንጣፍ ላይ ወድቆ አቤቱ ይቅር በለኝ ይል የነበረ አዳምን በንፅህና በቅደስና አስጊጦ ሞትን መፍረስና መበስበስን በትንሣኤ ድል ሽሮና በህያውነት አክብሮ የቀደመ ምንጣፉን መለሰለት ይህችውም“ልጅነት“ ናት፡፡

የነፍስ ጤናም በዚህ ይታወቃል፡፡ ሰው በደዌ ካልተያዘ በቀር ጥንካሬ ደስታ ሰላም እንደማይለዩት፤ ነፍሱ በመልካም ሁኔታ ያለች ሰው መንፈሳዊ ህይወቱ፣ጸሎቱ ፆሙ ወዘተ…ጥንካሬና ትጋት ያልተለየው፣ሁልጊዜ  ከመንፈስ ቅዱስ በሆነ ደስታ የተሞላና፤ከህሊናው፤አንስቶ ህዋሳቱ ሁሉ በእግዚአብሔር ሰላም የታጠረ ነው፡፡ ኃጥአን ግን እንዲህ አይደሉም፡፡

 ወንጌል ዘዩሐንስ ፭፥፩—፩፲ በወንጌሉ የተጠቀሰው ታሪክ ዩሐንስ ከጠቀሳቸው ሰባት የጌታችን ታላላቅ ተዓምራቶች አንዱ ነው፡፡ እጅግ መሳጭና ዕምቅ ምሥጢራትን ያቀፈ ነው፡፡ የተወሰኑ ነጥቦች ለማየት ያክል፡፡

፩.በታሪኩ ውስጥ አምላካዊ ድኂንና(direct salivation) ምክንያታዊ ድኂን(Indirect salivation) መሳ ለመሳ  ሢሠሩ እናያለን በአንድም በሌላም መንገድ መናገርም ሆነ መሥራት ፈቃዱ የሆነ አምላክ ዋናው ዓላማው ሰውን ማዳን ነውና፡፡

በቤተሳይዳ የነበሩ ህሙማን የእግዚአብሔር መልዓክ በሚያንቀሳቅሰው ውኃ(ጸበል) ይፈወሱ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይህ ምክንያታዊ ድኂን ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር በታቦቱ፣በመስቀሉ፣በጸበሉ፣በእምነቱ፣ በገድላቱ፣ በቅዱሳኑ ወ.ዘ.ተ…አድሮ የሚሰጠው ድኅነት ከዚህ የሚመደብ ነው፡፡

በሌላ አንፃር ጌታ ራሱ“እወዳለሁ ንፃ” ተነሣና አልጋህን ተሸክመኅ ተመላለስ“ እያለ በቃሉ መልሶ በእጁ ዳሶ የሠጠው ድኅነት አምላካዊ ድኅነት ይባላል፡፡ ይልቁንም በቀራንዮ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ጸዋትዎ መከራን ታግሦ የሰጠን ድኅነት በማንም ፍጡር ሊፈፀም ያልቻለና የማይችል አምላካዊ ድኂን ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ምዕመናን የሁለቱም መንገድ ተጠቃሚዎች የሆኑትም ለዚህ ነው፡፡

፪.“ሰው የለኝም” የምትለዋ በወንጌሉ የተጠቀሰች ቃል መፃጉዕ በምን ዓይነት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ እንደነበር ታሳያለች፡፡ በኃያሉ በእግዚአብሔር የፈውስ ሥፍራ ተኝቶ በተስፋ ይጠብቅ የነበረው የሰውን እርዳታ ነበር ጌታም ሲያናግረው ጎልማሳነቱን ዓይቶ ተስፋ ያደረገው ይህንኑ ነበር፡፡ ተስፋ ያደረጋቸው ሰዎች ግን ሠላሳ ስምንት ዓመት አልደረሱለትም፡፡ ሀብት ሥልጣን ጉልበት ወዘተ… ባላቸው ሰዎች የተመኩ ፍፃሜውን አይተዋል፡፡ ሌላው ይቅርና በሰው ፍቅር እንኳ ፍፁም ተስፋ አይጣልም፡፡ የሰው ፍቅር ከአቅምና ከፍቃድ ጋር የተገናኘ ነውና፡፡ በመንገድ ወድቀው ወይም ራቁታቸውን ላይ ታች ሲባዝኑ የምናያቸው የአካልና የአዕምሮ ህሙማን ከሰው ያልተፈጠሩ ሆነው አይደለም፡፡ ችግራቸው ከሰው የፍቅር አቅም በላይ ሆኖ አንጂ፡፡

ፍቅሩ በአቅም ውሱንነት ፈቃዱ በመሰልቸት የማይዳፈን እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ ምንኛ መልካም ነው፡፡ ክቡር ዳዊት “እናትና አባቴ ረሱኝ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ ለእኛ ያለውን ውዴታ ይገልፅልናል፡፡ ጨምሮም ሴት ከማኀፀንዋ ለወጣው ልጅ አስከማትራራ ትረሣ ይሆናል እኔ ግን አልረሣችሁም” የሚል ለርኅራኄው በእኛ ጨካኝ ህሊና መስፈርት ልናበጅለት የማንችለው አባት ነው፡፡ በእርሱ ታመኑ! መዝ ኢሳ49፥14-16

፫.ለሰው ልጅ የእግዚአብሔር ምህረት የተቋረጠበት ጊዜ የለም፡፡ ከህሊና በላይ የሆነው ርኅራኀሄው ምንግዜም ህዝቡን ይጎበኛል፡፡ ብንተወው አይተወንም እኛ ፈጣሪነቱን ብንክድ እንኳ እርሱ ፍጡራኑ መሆናችንን አይክድም፡፡ አምላካዊ መጎብኘት መቼና እንዴት እንደሚሆን የሚያውቀው ጌታ እግዚአብሔርና እርሱ በመንፈሱ ያመለከታቸው ብቻ ናቸው፡፡

መፃጉዕ የተጎበኘው ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ይህ ለመፃጉዕ የዘገየ ለጌታ እግዚአብሔር ግን ትክክለኛው ሰዓት ነበር፡፡ መፃጉዕ መጎብኘቱን ይጠብቅ የነበረው መልዓኩ ውኃውን ሲያናውጠው በነበረው ሂደት እንጂ አምላክ በአካል አጠገቤ ቆሞ በቃሉ አዝዞ ይፈውሰኛል የሚል እምነቱ አይደለም ሀሳቡ አልነበረውም፡፡ የሆነው ግን እንዲህ ነበር አንድ መልከመልካም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ፍፁም ጤነኛ ጠንካራ የሚመስል ድንገት በመፃጉዕ አልጋ አጠገብ ቆመ፡፡ የተለየ የሚጠይቀው ዘመድ አልነበረውም፤የተጠቁት ሁሉ ዘመዶቹ ነበሩ፡፡ መፃጉዕ የተረጋጋና ፍጹም የሚመስጥ “ልትድን ትወዳለህ?“ የሚል ቃል ወደሰማበት ሲዞር የተመለከተው ነው፡፡ መልሱ ሰው የለኝም ነበር፡፡እዚህ ቦታ መጥቶ ከወደቀ እንዲህ ቀርቦ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ከዚህ ጎልማሳ በቀር መኖሩን ማስታወስ አልቻለም፡፡ የሚያዋራውም ሰው ናፍቋል ብሶቱን ተነፈሰ፡፡ ቀጥሎ የተሰማው ቃል ግን አጥንቱን ሲያበረታው፣ ጡንቻውን ሲያፀናው፣ ጅማቱን ሲፈታው፣ ድካሙን  ሲያነቃው እርሱም ሊገነዘበው በማይችል ፍጥነት እመር ብሎ ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ መዝለል ጀመረ፡፡

ይህን ያደረገለትን ከሞት እንኳ ከከፋ ኑሮ ውስጥ ትንሣኤ የሰጠውን ማን መሆኑን ለማሰተዋል ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ብቻ ተጓዘ ነጎደ…

ሰው ይኸው ነው ካደረገለት ይልቅ ለተደረገለት፤ከሠጠው ይልቅ ለተሰጠው ነገር የበለጠ ክብርና ትኩረት ይሰጣል፡፡

ሥጋው እንጂ ህሊናው አካሉ እንጂ መንፈሱ ያልተፈወሰው መፃጉዕ በአይሁድ ጥያቄ ደስታው ሲቋረጥ ነው ማን እንደፈወሰው እንኳ ለማስታወስ የሞከረው፡፡ የጎበኘው ግን ካጠገቡ ርቋል፡፡ መልሶ ሲያገኘውም የተያዘበትን ትብታብ ስላየ የሚብስ እንዳያገኝህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው፡፡ በዚህም ደዌው ቀድሞም በኃጢአት ምክንያት እንዳገኘው ወደፊትም መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገው አመለከተው፡፡ ግን አልተጠቀመበትም ሂዶ በሰንበት የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ተናገረ፡፡ ልብ በሉ“መሰከረ” አላለም“ተናገረ“ እንጂ፡፡ ስለዚህ ስሙ መፃጉዕ መሆኑ የተገባ ሆነ ከደዌ ሥጋ እንጂ ከደዌ ነፍስ አልተፈወሰምና፡፡

ወንድሞቼ ክርስቲያኖች መጎብኘታችን ለሚበልጠው እንዲሆን ጸልዩ፡፡ ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምናደርገው ግንኙነት በሥጋ ጉዳይ(Agenda) ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ ምን ይጠቅመናል? መጎብኘታችን በነፍስ በሥጋ እንዲሆን ጸልዩ! የመጎብኘታችንን ወራት ማስተዋል እንድንችል ጸልዩ ሲጎበኘን እርሱ መሆኑን ማወቅ እንድንችል ጸልዩ! በቀራንዮ ኮረብታ እጆቹን መስቀል ላይ ሲዘረጋ ሁላችንን ጎበኘን “ልትድን ትወዳለህን” እያለ በውኃ ጥም በደረቀ አንደበቱ ላቀረበልን ግብዣ መልሳችን ምን ይሆን?

፬.ጌታችን ከቃሉ እንደምንረዳው አምላክነቱን የገለፀው በቃሉ(በትምህርቱ) ብቻ ሳይሆን በሥራው ጭምር ነው፡፡ መፃጉዕን ከፈወሰው በኋላ ከአይሁድ ለቀረበለት ጥያቄ የሠጠው መልስ “አባቴ እስከዛሬ ይሠራል፤እኔም ደግሞ እሠራለሁ” የሚል ነው፡፡

የእኛም ክርስትና ቃል ከግብር መስማማት ያስፈልገዋል፡፡ እንግዲህ ምን እንላለን ታላቅ የሆነ ስም ተሸክመናል፡፡ በዚህ ዓለም ሰዎች ሊጠሩበት የሚችሉ ከዚህ የሚልቅ ስም የለም ስሙ ቃል ከግብር ተስማምቶ ካልተገለጠ ከራስ አልፎ ለሌሎች መዘበቻ ከመሆን አያልፍም፡፡ ነን ስላልን ብቻ መሆን አንችልም፡፡

ታለቁ ምሥጢር፡- መፃጉዕ የአዳምና የዘሩ ምሳሌ ነው፡፡ አዳም በኃጢአት ደዌ ተጠቅቶ ወደቀ ይህ የኃጢአት ደዌ ከክብደቱ የተነሣ ማንም ሊያርቅለት አልቻለም፡፡ ዘመኑ ሲርቅ የሰዎች ቀቢፀ ተስፋ እየጨመረ ወርጄ ተወልጄ አድናችኋለው የሚለው አምላካዊ ቃል ኪዳን እየተዘነጋ በብዙ ሰው ሰራሽ ምልከታዎች ከል ለበሰ፡፡ በጣም ጥቂቶች ትንቢት እየተረጎሙ ሱባዔ እየቆጠሩ ተቀመጡ፡፡ በመካከላቸው ሲገለጥም እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ስላልሆነ ሊያውቁትም ሊቀበሉትም አልቻሉም፡፡ተቆራምደው ከተኙበት የውርስ ኃጢአት ምንጣፍ ባለመታዘዝ ከመጣባቸው የኃጢአት ደዌ ፈውሷቸው ሲሔድ አላወቁትም፡፡ አምላክነቱን በቃልም በሥራም እያሳያቸው ሌላ የሚያድን ይጠብቃሉ፡፡ ሐሳዊ መሲህ ሲገለጥም እርሱን የመቀበላችው ስህተት የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ ኢሳ 59፥16፤ዮሐ 1፥10-12

አዳነን“ከዚህ የባሰ እንዳያገኛችሁ ዳግመኛ ኃጢአትን አትስሩ” ብሎንም ዐረገ፡፡ ምክንያቱም አዳም ቢስት ወርጄ ተወልጄ አድንሃለው በሚል ተስፋ የቀደመ ርስቱን አግኝቷል፡፡ የህያው እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነቱን ፈጣሪነቱን አዳኝነቱን ጌትነቱን የማያምኑ ግን የድኅነት ተስፋ የላቸውም፡፡ የአዳም ቅጣት በዘመን ተገድቧል በእግዚአብሔር ልጅ የማያምኑ ግን ዘላለማዊ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ የሚብስ የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ዮሐ3፥16፤21፤ዮሐ16፥7-11 

ይቅጥላል ....

 ውስብሐት ለእግዚአብሔር! 

Read more...

ታሪከ አበው: አቤል እና ቃኤል

Download
Name
Play
Size
Duration
download
AbelAndCain

61.1 MB
1:06:43 min

Read more...

ታሪከ አበው: አዳም እና ሄይዋን ክፍል 2

Download
Name
Play
Size
Duration
download
AdamAndEve2

22.5 MB
24:33 min

Read more...

ታሪከ አበው: አዳም እና ሄይዋን ክፍል 1

Download
Name
Play
Size
Duration
download
AdamAndEve

107 MB
1:56:55 min

Read more...
Subscribe to this RSS feed

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ