Login
Main menu

የ “at least” ክርስትና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን! የ “at least” ክርስትና

 

 

በቅርብ በቅዱስ ጋብቻ አንድ የሆኑ ጥንዶች ስለ ክርስትና ሕይወት ለመወያየት ፈልገው በቢሮዬ ተገናኘን፡፡ ውይይታችን ከተነሱት በርካታ ጉዳዮች የዘመኑን የክርስትና ሕይወት አጉልቶ የሚያሳዩ ሁለት ነጥቦችን እነሆ፡፡

የመጀመሪያው ከእንግዶቹ የተነሳው ሀሳብ በምንኖርበት አገር የሚያስተምሩን ካህን በክርስትና ሕይወት ስንኖር at leastእነዚህ እነዚህ ነገሮችን ልንፈጽም እንደሚገባ ነግረውናል፤ እርስዎስ ምን ይመክሩናል? በሚል ውይይታችንን ጀመርን፡፡ በተቀመጥኩበት የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ የተገለጠበትን መጽሐፍ ቅዱስን በኅሊናዬ ለመዳሰስ ሞከርኩ፡፡ እናም ላገኘው ያልቻልኩት ነገር ቢኖር at leastበሚል ቀዳሚ ቅጽል የተቀመጠን ትዕዛዝ ነው፡፡ መንግስተ እግዚአብሔርን ለመውረስ የተቀመጠ “minimum requirement” ምን እንደሆነ ማወቅ ብችል ብዬ አሁንም ለማሰብ ሞከርኩ ግን አሁንም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ያ መስፈርት መንግሰቱን ለመውረስ ካበቃ “minimum requirement” ሊሆን አይችልም፡

፡ ነገር ግን በተለምዶ መምህራነ ወንጌል ክርስቲያኖች ከሆንን at leastይህን ልንፈጽም ይገባናል እያልን ስለምናስተምር፤ አበ ነፍሳትም ልጆቻችንን ስንመክር ልጆቼ “ቢያንስ” ይህንና ይህን ለማድረግ ሞክሩ ስለምንል ምዕመኑን የ “at least” ክርስትና ውስጥ አመቻቸነው፡፡ ምዕመኑም ለሚበልጠው ጸጋ ከሚተጋ ይልቅ “at least” ይህን ይህን እየፈጸምኩ ነው በማለት ለራሱ የጽድቅ መስፈርት አስቀምጦ ተዘናጋ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ግን “አድርግ አታድርግ፤ ሁን አትሁን” እንጂ፤ at least” ይህን አድርግ ይህን አታድርግ፤ “at least” ይህን ሁን ይህን አትሁን የሚል የለም፡፡ ወጥመድ የማይመስሉ የክፉውን ማዘናጊያና የምኞታችንን ማባበያ ትተን “ንቁ፣ በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ” የሚሉትን የአባቶቻችን የሐዋርያትን ምክር መስማት ካልቻልን ሊውጠን ፈልጎ ዙሪያችንን ለሚያገሳው አንበሳ ጥሩ ታዳኝ እንሆናለን፡፡ ከእንግዶቹ ጋር የነበረን ውይይት በሌላ ልሳን ስለ ነበር በመጨረሻ የሰጠኋቸው ማሳሰቢያ “anyways do not tell the priest about the at least!” የሚል ነው፡፡

*** do you mind to list yours “at least”?

ሁለተኛው ነጥብ በየጊዜው የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰማት በቆምኩባቸው ጉባኤዎች ሁሉ እየታዘብኩ የመጣሁት ምዕመናኑ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ “ማስረጃ” እንዲቀርብ ያለው ፍላጎትና መምህራንም ምዕመኑን በማስረጃ እያረካን በእምነት ግን እያደኸየን መምጣታችንን ነው፡፡ ይህ በሊቃውንት (በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ ብቻ ማለቴ አይደለም) ዘንድ ቶማሳዊነት ይባላል፡፡ “ጌታ ተነስቷል” ሲባል ጣቴን በችንካሩ ካላገባሁ፤ በእጆቼም የተወጋ ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም ማለት ነው፡፡ ለሁሉ ማስረጃ ፍለጋ፡፡ ጌታችን ለዚህ መልስ ሲሰጥ “ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው” ነው ያለው፡፡ እምነትና ማስረጃ ፍጹም የተለያዩ መንገዶች ናቸው፡፡ እምነት የማስረጃ ጥገኛ አይደለም፡፡ በራሱ ጸንቶ የቆመና፤ ጸንቶ ለማቆምም መሠረት መሆን የሚችል ነው፡

፡ በክርስትና ለሁሉ ነገር ማስረጃ ከፈለግን ከማመን ይልቅ ለመካድ ቅርብ እንሆናለን፡፡ መምህራንም ያሳመንን እየመሰለን በማስረጃ ጋጋታ ከእምነት ምዕመኑን እያራቆትነው ነው፡፡ ማስረጃ አንድን ነገር እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን ያሳውቀናል፡፡ ማስረጃ ከእውቀት ጋር እንጂ ከእምነት ጋር ባህርያዊ መስመር አያገናኛቸውም፡፡ በክርስትና በእምነት እንጂ በማስረጃ ምንም ያህል ርቀት እንደማንሄድ ብዙ ማስረጃ ማምጣት ይቻላል፡፡ ግን ከዘረዘርኩ አሁንም ማስረጃ ላቀርብ ነውና በሀሳቤ ተቃርኖ ላይ ልቆም ነው፡፡ ስለዚህ እመን!!!

ይህ በሽታ ሲጀምር አንድ ቃለ እግዚአብሔር በተጠቀሰ ቁጥር ምን ላይ ተጽፏል በማለት ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት በሚያስተምረን መምህር ላይ እምነት የለንም ማለት ነው፡፡ ግን እኮ መምህሩ ለጠቀሰው ጥቅስ እንጂ ለሰጠው ማብራሪያና ትንታኔ፤ ላመጣው ትርጓሜና ላመሠጠረው ምሥጢር ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ወይስ ጥቅሱን ማሳየቱ ብቻውን ያቀረበውን ትንታኔና የተረጎመውን ትርጓሜ ትክክል ያደርገዋል? ያለው አማራጭ አንድ ነው፡፡ መምህሩን ካመንከው አዳምጠው ካላመንከው አታዳምጠው፡፡

በሽታው እያደገ ሲሄድ ምሥጢራትንና በምሥጢራት የምናገኘውን ጸጋ መጠራጠር እንጀምራለን፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደሚል የደረቁ ወንዞች ማለት “እምነት አልቦ ክርስቲያኖች” የምንሆንበት ደረጃ ነው፡፡ የሚታይብንም በልማድ የምንፈጽመው ሥርዓት እንጂ በመንፈስ በእውነትና በመንፈስ የሆነ አምልኮ አይደለም፡፡ የሥርዓት ክርስቲያኖች(canonical Christians) እንጂ መንፈሳዊ ክርስቲያኖች (spiritual Christians) ለመሆን እንቸገራለን፡፡ ፍጻሜውም የጸጋው ባለቤት የሆነውን መድኃኒታችን


ኢየሱስ ክርሰቶስን መጠራጠርን ያመጣል፡፡ ይህም ክህደት ነው፡፡ ዛሬ በቤተክርስቲያን ለምናየው የክርስትና ሕይወት ድርቅ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ አገልጋዩና ምዕመኑ አይተማመኑም፡፡ ስለዚህ የምንማረውም ሆነ የምናስተምረው ወደ ክህደት ለመድረስ ነው፡፡ ሳናውቀው!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ ሐምሌ 17 2011

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.

back to top

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ