በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ
የአንድ ሰነድ ማረጋገጫው ማኅተም እንደሆነ ሁሉ እኛም ከክርስቶስ ጋር ላለን ሕብረት አብረነውም የምንሠራ ለመሆናችን ማኅተሙ ‹‹ትወደኛለህን?›› ብሎ ለሚጠይቀን ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ነው፡፡ ይህን ማሰብ ልብን ያሳምማል፡፡ሁሉን በሚያውቀው በእርሱ ፊት መተወን ሲያስተውሉት ያሳቅቃል፡፡ ተውኔታችንን ሕይወት አልባ ትወናችንንም ለዛ ቢስ ያደርገዋል፡፡ እንዴት ያለ አለመታደል ነው የሕይወት ዘመን ክስረት?!
ዛሬ ያለን የክርስቶስ ተከታዮች ሕይወታችን ለሌላው ትምህርት መሆንም አልቻለም፡፡ምክንያቱም ሁል ጊዜ የሚገለጠው ጥንካሬያችን ንፅሕናችን ቅድስናችን እንጂ ድክመታችን ጥፋታችን ነውራችን አይደለምና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ እምነቱ እንደተገለጠ ‹‹የምትሉትን አላውቀውም››ብሎ የተናገረው ክህደቱም ተገልጾ በመታየቱ ከሕይወቱ ተማርን፡፡ ሁሌ ጥንካሬን ሁሌ ቅድስናን የምንሰማበትን ሕይወት ግን ከምንማርበት ይልቅ ተጠራጠርነው፡፡
በቤተ/ክ ታሪክ ለታላቅ ቅድስና ሕይወት የበቁ ቅዱሳን በቀደመ ሕይወታቸው ታላላቅ ስህተት የሠሩ ናቸው፡፡በእነርሱ ላይ የተገለጠች ታላቅ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በማድነቅ ለንስሐና ለቅድስና ሕይወት እንድንበረታታ ነው ታሪካቸው የሚተረከው፡፡
ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር እርግጠኞች ከሆንን በስሕተት ወይም በፍርሃት ለሚገጥመን ውድቀት ይቅርታው ቅርብ ናት፡፡ ከወደቅንም በኋላ ማረጋገጥ የሚፈልገው ለእርሱ ያለንን ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሌለው ሰው ለንስሐ አይቀርብም፡፡ ፍቅር የሌለው ንስሐም ሥርየትን አያስገኝም፡፡ከፍፁም ፍቅር የተነሳ ንስሐ ስንገባ ግን የጌታ እግዚአብሔር ይቅርታው በእኛ ላይ ትደንቃለች፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ንስሐ የጌታ እግዚአብሔር ይቅርታ ወደ ቀደመ ክብራችን መመለስ ብቻ አይደለም ከዚያ ወደሚበልጥ ከፍታ በማውጣት ትገለጣለች፡፡
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ጌታ እግዚአብሔርን በስንቱ ነገር ይቅርታ እንደምንጠይቅ ግራ እስኪገባን ድረስ በደላችን ይከድነናል አለማስተዋላችንም ይሸፍነናል፡፡የሚታገሉንን ለመጣል፣የሚቃወሙንን ለማጥፋት፣የሚያጠቁንን ለማጥቃት ስንት ጊዜ ተጠበብን፡፡ስንቱን ሸፍጥ በስሙ ስንቱን በደል በኃይሉ የተገኘ ፍትሕ አስመሰልነው፡፡በፍቅር ሳንታገል ተሸንፈን ሳናሸንፍ የትግላችን መሪ የውጊያችን ፊታውራሪ ልዑሉ መሆኑን ለፈፍን፡፡ የጥላቻችንን ድል የቅዱስ ስሙ መመስገኛ አደረግን፡፡ ታዲያ ለዚህ ላልተገለጠው በደላችን የሸፍጥ ጽድቃችን እንደ ነቀርሳ ውስጥ ውስጡን ርኩሰት ለበላው ቅድስናችን ቀርቶ ለተገለጠው ኃጢአታችን ምን ንስሐ ይበቃዋል? አሁን የኖርነውን ዕድሜ ደግሞ ቢጨመርልን ለመፀፀት አይደለም ለማስታወስ እንኳ ይበቃን ይሆን?
በሁሉ የምመስልህ ወንድሜ ሆይ! በሕይወት ለመቆየታችን በፊቱም ለመታየታችን የኃጢአትን ይቅርታ ለማግኘታችን ምክንያቱ የልዑሉ የይቅርታ ስፋት እንጂ የእኛ የንስሐ ጥልቀት አይደለም፡፡ ይህን ባመንበት ቅፅበት ወደ ምህረት ደጃፍ መቅረብ እንጀምራለን፡፡
ግን ደግሞ እንደ እውነቱ የሁላችን ኃጢአት ተገልጦ አለመታወቁ የይቅርታ ልብ በጠፋበት በዚህ ዘመን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰውን ፀፀቱን ንስሐውን አይቶ ይቅር (ከልቡ) ብሎ የተሻለ ክብር ከሚሠጠው ይልቅ የሚረግም የሚፈርድና መጠቀሚያ ለማድረግ የሚያደባ በበዛበት ጊዜ ተጋላጭ ሆኖ መገኘት አለመፈለጉ በዘመኑ ክርስቲያኖች ላይ ያለንን የእምነት ጥርጣሬ የሚያሳይ ነው፡፡ ማስተዋል አቃተን እንጂ የክርስትና መሠረቷ ይቅርታ ነበር፡፡ ጌታችን በመስቀሉ ደሙን አፍስሶ እኛ በበደልን እርሱ ክሶ ይቅር ባይለን ኖሮ ወዴት እንታይ ዘንድ አለን ነበር? እርሱም ያስተማረን የሰማዩ አባታችሁ ይቅር እንዲላችሁ እናንተም የበደሏችሁን እንዲሁ ይቅር በሉ በማለት ነበር፡፡ሰው ራሱን የሚገልጠው ውጤቱን ገምቶ ነው፡፡ የይቅርታ ጉልበት በመካከላችን ተገልጦ ቢሆን ኖሮ የማስመሰል ሕይወት ምንኛ በሞተ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ይቅርታ ስትደክም ኃጢአት በሥውርነገሠች፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት በጨረፍታ ቢሆንም እንኳ ከቀመስን የአሕዛብ ሐዋርያ ወደ ተባለ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ እናልፋለን፡፡
አስቀድሜ ይህን ለመጻፍ በመድፈሬ በራሱ ታላቅ ይቅርታን ሕይወታቸውን ኖረውለት ሞቱን በሚመስል ሞት ከመሰሉት ከሐዋርያት ጌታ እለምናለሁ፡፡የዚህ የተወደደ ሐዋርያ ሕይወትስ ይጽፍ ዘንድ ማን ይደፍራል? ይህ ከመታሰብ በላይ ነውና፡፡ እንዲያው ለቅምሻ ያህል እንሞክራለን፡፡በዚህ ጽሑፍ ተነሣስታችሁ ይበልጥ ቅዱስ ጳውሎስን ማወቅ ለምትፈልጉ ግንየሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሰባት ቁጥር ስድሳን መነሻ አድርጋችሁ የሐዋርያት ሥራን ሙሉውንና መልእክታቱን አንብቡ፡፡ስታነቡ ግን በጸሎትና በታላቅ ተመስጦ ይሁን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ቃልና ዓረፍተ ነገር የውቅያኖስ ያህል ጥልቀት ያለው ነውና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስን በመጽሐፍ ቅዱስ የምንተዋወቀው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲገደል የገዳዮቹን ልብስ ሲጠብቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ የታላቁን ሰማዕት ደም ለማፍሰስ እጆቹ ድንጋይ እንዳያነሱ መንፈስ ቅዱስ ቢጠብቀውም በመገደሉ ግን ተስማምቶ ነበር፡፡የወደፊቱን የአሕዛብ ቤ/ክ ካህንና ሐዋርያ መንፈስ ቅዱስ ከደም ጠብቆታል፡፡ የሰማዕታት ደም ሥራ ሳይሠራ በከንቱ አይቀርምና የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ጳውሎስን ለቤ/ክ አስገኝቷል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለኦሪት በነበረው ቅንዓት ክርስቲያኖችን ለማሰር ከሊቀ ካህናቱ ደብዳቤ ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሲሔድ ነው ከክርስቶስ ጋር የተገናኘው፡፡ ከኦሪት ሊቀ ካህናት ሰዎችን ለማሠርና ለማሠቃየት ነፃነታቸውን ለመግፈፍና እምነታቸውን ለማስካድ ሥልጣን ተቀበለ፤ ከአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከጣዖት፣ከኃጢአት፣ ከድንቁርና ጨለማና ከዲያብሎስ እስራት ነፃ እንዲያወጣ፤በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለሚገኝ አዲስ ሕይወት በእምነት እንዲፀኑ ለማስተማር ሥልጣን ተቀበለ፡፡የኦሪቱ ሊቀ ካህናት በቁጣና በጭካኔ ላከው የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት ግን በፍቅርና በርኅራኄ አሠማራው፡፡
ጌታ እግዚኣብሔር ያለ ዓላማሰውንም ሆነ ሌላውን ፍጥረት አልፈጠረምና ዓላማ ያለው ሰው ይወዳል፡፡በእርግጥ ሰዎች አጥፊ መሆኑን አምነው የሚይዙት ዓላማ ያለውን ያህል እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ካለ ማስተዋል የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚዋጉ እየመሰላቸው እራሱን እግዚአብሔርን የሚያሳድዱ አይጠፉም፡፡ጌታም በቃሉ‹‹…የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል›› ያለ ይህን ሲያመለክት ነው፡፡ ዮሐ16÷2
ነገር ግን ሁልጊዜ ክፉ ነገሮችን ለበጎ የሚለውጥ ጌታ እግዚአብሔር የቅዱስ ጳውሎስንም ቅንዓት ለወንጌል አገልግሎት ለቤ/ክ መስፋት እንዲልውል ፈቃዱ ሆነ፡፡ የዮሴፍ ወንድሞች ቅንዓት በኋላ ለእስራኤል ከረሃብ መዳን ምክንያት እንደሆነ የቅዱስ ጳውሎስም ቅንዓት አሕዛብን ከቃለ እግዚአብሔር ረሃብ ለመዳን ምክንያት ሆኗል፡፡