በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3. ጽናት፡- ኅብረተሰቡ በተለያየ ችግር ምክንያት ቅስሙ ተሰብሯል፡፡የኢኮኖሚ ቀውስ፣ሥራ አጥነት፣ጦርነት፣ ያልተገለጠ የየማጀቱ ረሃብ ወዘተ… አድቅቆታል፡፡ከዚህ ሁሉ መጽናኛው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡እግዚአብሔርን እንዳገኘ የሚሰማው ደግሞ የሃይማኖት አባቶቹን ሲያገኝ ነው፡፡
በመሆኑም አገልጋዮች ከችግር ይልቅ መፍትሔ ላይ የሚያተኩሩ ለየትኛውም አስጨናቂ ሁኔታ የማይበገሩ መንፈስ ጽኑ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምድር የሥነ-ልቦና አማካሪዎች አይታወቁም፡፡ አሁን እንኳ በተለያዩ ቦታዎች የተከፈቱ የምክር አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ቢኖሩም፤በሚዲያም በነጻ ምክር የሚሠጡ ፕሮግራሞች ቢተላለፉም የሕዝቡ ቀዳሚ ምርጫ ግን አሁንም የሃይማኖት አባቶቹ ካህናት ናቸው፡፡ምክንያቱም፡-
ሀ. የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብና በችግር ወቅት ጠባዩን እንዳይቀይር እያበረታቱ፤በጦርነት በመከራ ጊዜ ወኔው እንዳይከዳው እያጠነከሩ ይዘውት ከኖሩ ካህናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ በሥጋ ከወለዱት ወላጆቹ ይልቅ ያከብራቸዋል፡፡ ስለዚህ እነርሱ አጠገብ በመገኘቱ ብቻ የሚሰማው ደኅንነት ሌሎች ባለሞያዎች ጋር አይሰማውም፡፡
ለ. በኢትዮጵያ ምድር አሁንም ቢሆን ሳይንስ በሃይማኖት ላይ የበላይ ለመሆን ስላልቻለና ሕዝቡ እምነቱን ስላልጣለበት ፡፡
ሐ. ለምሥጢር ትልቅ ግምት የሚሠጠው ሕዝባችን ካህናቱ ዘንድ ምሥጢሩ እንደሚጠበቅለት እርግጠኛ በመሆኑና፤ ይህንንም ከእግዚአብሔር እንደተሠጠው ዋስትና ስለሚቆጥር፤ ከባለሞያዎቹ ጋር ግን ይህ ልምድ ስለሌለውና በመካከላቸውም የምሥጢሩን ድኅንነት የሚያስጠብቅ ዋስትና አለ ብሎ ስለማያምን
መ.ትልቁና ዋነኛው ሕዝቡችግሩን ለካህናቱ ሲነግር ለእግዚአብሔር እንደነገረ ፍፁም ስለሚያምን፤ለሥነ-ልቦና ባለሞያዎች መንገርን ግን ለአንድ ተራ ሰው ችግራችንን ነግረን ከምንጠብቀው ምላሽ የተለየ ስለማይጠብቅ(ካህናቱ ዘንድ ጸሎት፣ ሱባዔ፣ሥልጣን፣ተዐምራት፣መለኮታዊ ኃይል ወዘተ… አለ ብሎ ማመኑ፤ ሌሎቹ ጋር ግን የተለየ ነገር ስለማይጠብቅ)
ሠ.በሕይወት ልምዱ ብዙዎች ለካህናት ነግረው ችግራቸው እንደተፈታ ምስክርነት ስለሚሰማና በአንፃሩ በሥነ-ልቦና አማካሪዎች ዘንድ ስላለው መረጃ ስለሌለው፡፡
ረ.ሕዝቡ(ምዕመኑ) ካህናት ጋር ለምድራዊ ሕይወት መረጋጋትን ለነፍሱ ደግም ሥርየትን ሽቶ እንደመምጣቱ፤ የሥነ-ልቦና ባሞያዎች ጋር የዚህ ዓይነት አገልግሎት እንደማይገኝ ማወቁ ወዘተ…
ስለዚህ ካህናት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሀዘኑ አፅናኝ፣ የደስታው ባራኪ፣የችግሩ አጋር፣የጭንቀቱ መተንፈሻ፣የነፍሱ ምሥጢረኛ እንደመሆናችን ችግርን የሚረግጥ ጽናት ተስፋ መቁረጥን የሚሰብር ጥርካሬ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ድቡሽት ላይ ቆሞ ረግረግ ውስጥ ያለን ማውጣት እንደማይቻል፤ ለችግር በቀላሉ እጅ የምንሠጥ ሆነን ሌሎችን መርዳት አይቻለንም፡፡
4. መንፈሳዊነት፡- መንፈሳዊነት ስል የተገለጠ የሚሠራ የማስመሰል ያልሆነ ማለት ነው፡፡ ይልቁንም ዛሬ ብዙዎቻችን ለመንፈሳዊነት የምንሠጠው ግምት አናሳ ሆኗል፡፡ከመንፈሳዊነት ይልቅ ዘመናዊነት(በተንሸዋረረ ትርጉም) ማርኮናል፡፡ሕዝቡም የኸው ደዌ ተጋብቶበት የእኔ አባት እኮ ዘመናዊ ናቸው ሲል ይደመጣል፡፡የሚጠቅመን ግን ዘመናዊ ሳይሆን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
ላያችን ቢመስለውም ውስጣችን የሚፈልገው ግን ሌላ ነው፡፡ የድሮው የአበው የአነጋገር ለዛ፣ በጨዋታቸው ያለ ቅኔ፣ በነገራቸው ውስጥ ያለ ምሥጢር፣ ከእርጋታቸው የሚፈስ ግርማ ሞገስ ይናፍቀናል፡፡አብሯቸው የኖረ መስቀላቸው፣ ወዝ የጠገበ ዳዊታቸው፣ ዕጣን ያወደው ቀሚስና ካባቸው፣ ንባብና እንቅልፍ ማጣት ያፈዘዘው ዓይናቸው ብዙ ይነግረን ነበር፡፡
ቀደምት አበው ከሕዝቡ ሳይለዩ ሕዝቡንም ሳይመስሉ ይዘውት ኖሩ፤ዛሬ ሕዝቡን መስለን ከሕዝቡ ተለይተን ይዘነው ጠፋን፡፡ትዝታ ምንኛ ደግ ነው፡፡ቢያንስ ዛሬን በትናንት እንታዘበዋለን፡፡ዛሬ እንመገበው ስናጣ የኋሊት ተመልሰን በትናንት እንጠግባለን፡፡
ይብላኝ ትናንትን ለማያውቅ ትዝታ ለሌለው፤
ድሮ እኮ እንዲህ ነበር ብሎ ማውራት ለማይችለው፡፡
ሐዋርያነት ትናንትን ከዛሬ ዛሬን ከዘላለም ጋር ማገናኘት ማዋሐድነው፤ እንደ ሁለቱ የዓለም ብርሃናት፡፡ ለተረዳው ላወቀበት ለኖረበት ለሞተለት!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ ጸጋና በረከታቸው ድል የማይነሣ ጽኑ እምነታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን!አሜን!
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ሐምሌ 2005 ዓ.ም
መታሰቢያነቱ ፡- በፈቱት ምላስ ለሚሰደቡ ባስተማሯቸው ለሚናቁ ለነ የኔታ፤ ለነበሩ ላሉ ለሚኖሩ ትሁን፡፡