በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ
የዛሬን አያድርገውና ታላቅ የክርስቲያኖች መናገሻ የነበረችው አግያ ሶፍያን የመሰለ ታላቅ ቤተክርስቲያን የነበረባት ቁስጥንጥንያ የዛሬዋ ኢስታንቡል የሮማ ግዛት ሁለተኛዋ መናገሻ ነበረች፡፡ በአንድ ወቅት በግርማው የተፈራ በዝናው የከበረ በኋይሉ የታፈረ ታላቅ ቄሣር ዘውድ ጫነ፡፡ በዚህ በዓለ ንግስ ላይ መኳንንቱና መሳፍንቱ እንደየማዕረጋቸው ንግግር እያደረጉ ታማኝነታቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ቤተክርስቲያንን በመወከል በጊዜው የነበረው ፓትሪያርክ ንግግር እንዲያደርግ ሲጋበዝ በዙፋኑ ላይ በታላቅ ግርማ ተቀምጦ ለነበረው ቄሣር እንዲህ አለ‹‹የዓለምን የሥልጣን ጫፍ ጨብጠሃል፤ መግደልም ሆነ ማዳን የሚችል ሰይፍ ታጥቀሃል፤ ካንተ በታች እንጂ ካንተ በላይ የሚታይ የለም፤ሁሉን ማድረግ እንደምትችል አንተ ታምናለህ እኛም ይመስለናል፤ግን ይህ ሁሉ እውነት ያይደለ ቅዠት ነው፡፡ምክንያቱም ያመንካቸው የሚክዱበት ወዳጆችህ የሚሸምቁበት ሰይፍ የጨበጠ ክንድህ የሚዝልበት ከሁሉ በላይ በሆንክባት ምድር ከሥሯ ተኝተህ ሁሉ ከበላይህ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ!››
ማመናችን ወይም አለማመናችን የማይለውጠው የዘላለም እውነት ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ ከዚያ እውነት ጋር የምንገናኝበት ቅጽበት ለእያንዳንዳቸን ከጥላችን ይልቅ ቅርብ ነው፡፡በየትኛውም ቀንና ሰዓት ደቂቃና ሰኮንድ ያን እውነት በድንገት እንጋፈጠዋለን፤እጃችንን እንዘረጋለን ወደ ሚወደውም ይወስደናል፡፡ይኸውም‹‹ሞት››ነው፡፡ ልክ በዚያች ቅፅበት እንኳን በሌላው ላይ በራሳችን ላይ ያለን ሥልጣን ያበቃል፡፡በምድር ሳለን የተሠጠን ዕድል ለሞት መዘጋጀት እንጂ ሞትን ማስቀረት የሚችል አይደለም፡፡ከሞት ማዶ ከመቃብርም ወዲያ በዳይና ተበዳይን ገፊና ተገፊን ለመዳኘት ሥልጣን ያለው እውነትና ፍትህ የዙፋኑ ጌጥ የሆኑ‹‹የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ›› ያለው እርሱ ሁሉን ይጠብቃል፡፡ በዘላለማዊው ዳኛ ፊት በኃፍረት ወይም በሀሴት ለመቆም ውሳኔው ያለው በእጃችንየተሠጠንም ጊዜ አሁን ነው፡፡መለወጥ ከፈለግን መለወጥ ትችላለንና ይህተጽፎልናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከሰማና የሆነበትን ካየ በኋላ ለመወሰን ያለው ጊዜ አሁንመሆኑን አውቋል ፡፡ኅሊናውን ማንበብ ቢከብድም ደግሞ ከጠየቀው ጥያቄ ቀድሞ የኖረበት እውነት መናዱንና አዲስ ለተገለጠበት እውነት ራሱን ምርኮ ለማድረግ መዘጋጀቱን ያሳያል፡፡ ማንም ሰው ቢሆን የለመደውን፤ረጅም ዕድሜ የኖረበትን፤ እውነት ነው ብሎ የተቀበለውን በቀላሉ መላቀቅ ይከብደዋል፡፡መክበድ ብቻ ሳይሆን ያስፈራዋል፡፡እንደ ታላቅ ሽንፈት ስለሚያየው እልህ ይጋባል፡፡ወደ ሕይወት መንገድ ለመምጣት የብዙዎች ችግር ይኸው ነው፡፡
ይልቁንም አንድ ቀን ከጌታ እግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት (የተለየመገለጥ) በራዕይ፣ በሕልም፣ በተዐምራት፣ በመከራ፣ በፈተና፣ በሞት… ወዘተ ሊሆን ይችላል ይዘነው የነበርነውን እውነት ይበልጥ ያጎላልናል ወይም የተከበርክበት እውቀት የደሰኮርከው ፍልሰፍና የሰበከው ስብከት የሞትክለት ሕይወት ባዶ መሆኑን ያሳይሃል፡፡
እውነት በባሕርይዋ እንደ እሳተ ገሞራ ያንቀላፋች ፍም ናት፡፡ጭምትነት፣ ገርነት፣ ራስን መሰወር፣በሒደት በመድመቅና ኃይሏን በመግለጥ፣ በዘመናት ውስጥ ሳትፋለስ ፀንታ በመቆየትም ትታወቃለች፡፡ ጊዜን መስላ አትገለጥም፡፡ጊዜያት ሁሉ የእርሷን መገለጥ አብሳሪ ታሪኳንም ዘካሪ ይሆናሉ እንጂ፡፡ አዝማናትን በመለወጥ እንጂ በመመሳሰል አትታወቅም፡፡ሁሉን ትማርካለች ሁሉን ትስባለች ለሁሉ ራሷን ትሰጣለች፡፡
ያወቋት በድካም ውስጥ ኃይልን፣በድንቁርና ውስጥ ጥበብን፣ በንድየት ውስጥ ብልጥግናን፣ በሞት ውስጥ ሕይወትን ያመልካሉ፡፡ ጠቢባንና አስተዋይ ነን ከሚሉ ተሰውራ ለሕጻናትና ለዚህ ዓለም ሞኞች የመገለጧ ምሥጢርም ይኸው ነው፡፡ ምርጫ እንጂ ሽርክና የእርሷ ፈሊጥ አይደለም፡፡ እርሷን የሚሹ ሁሉን ያጣሉ ከእርሷ የሚሸሹም የሚበልጠውን ያጣሉ፡፡ ያቺ ቀን ከባድ ናት የኖርክበት ሲናድ ሕይወትህን የሰጠህለት መና ሲሆን የምታይባት ቀን፡፡ያቺ ዓለም የዚህን ዓለም ሸቀጥ ሊያሳርፍ የሚችል ወደብ የላትም፤ቀድሞ ከዚያው የተሠጠህንና አክብረህ የያዝከውን ይዞ ከመሔድ በቀር፡፡
ጳውሎስ ተማረከ! ኃይሉ፣እውቀቱ፣ስሜቱ፣ ፍላጎቱ፣ የመኖር ዓላማው ወዘተ… ተማረከ፡፡‹‹ጌታ ሆይ ምን አደረግ ዘንድ ትወዳለህ?›› በሚል የእውነት መንፈስ ራሱን እስከወዲያኛው ሰጠ፡፡ የእርሱን ምኞት ቀብሮ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ኖረ፡፡ የዳግም ልደቱየሕይወት ፍልስፍና ‹‹ብንኖር ለክርስቶስ እንኖራን ብንሞትም ለክርስቶስ እንሞታለን›› የሚል ነበር፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ሰውን በሁለት መንገድ ይማርካል፡፡ የመጀመሪያው በፍቅሩ ይማርካል፤በቃሉ ይጠራል በቸርነቱ በርኅራኄው ይጎበኛል፡፡ ሰምተው የመለሱለት ሕይወትን ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛው በኃይሉ በሥልጣኑ ይማርካል፡፡ ይህ ለሕይወት የሚሆንላቸው እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ፍርድ የሚያገኛቸው ናቸው፡፡
ካለፈው የሕይወት ውጣ ውረድ ልምዳችን በመነሣት የጌታ እግዚአብሔርን ከኅሊና በላይ የሆነ ገናንነት በመረዳት ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ምርኮ አድርገን ብንሰጥ ሰማይና ምድር የሚዘክሩትን ሥራ በእኛ ይሠራል፡፡ስማችንም በሰማያዊው መቅደስ በሕይወት መጽሐፍ ይፃፋል፡፡በሕያዋን ምድር በበጉ ከተማ እንግዶችና መጻተኞች አንሆንም፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ነንና፡፡