በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ
በደማስቆ መንገድ ቅዱስ ጳውሎስ የጠየቀው ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ነው፡፡ የመጀመሪያው ጌታ‹‹ስለምን ታሳድደኛለህ?››ሲለው፤‹‹ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?›› በማለት የጠየቀውና ማንነቱን ካወቀ በኋላ ደግሞ ‹‹ጌታ ሆይ ምድ አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?›› የሚለው ፍፁም ራስን የመስጠት(የመገዛት)ጥያቄ ናቸው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የሚያናግረው የሚወቅሰው ማን መሆኑን ካወቀና ምን ማድረግ እንዳለበት ከተናገረው በኋላ ወደ ኋላ አልተመለሰም፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባው እንድትነግረው የተላከውም ወደ ቤተክርስቲያን ነው፡፡
ፊት ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ምዕመናንንም ለመሳደድ ተሰልፎ እንዳልነበር ኋላ ግን ጣዖትንና ክህደትና የሚያፈርስ የመንፈስ ቅዱስ መዶሻ፤የጠንቋና የአስማተኞች ሥራይ ማርከሻ፣የሕሙማንና ተስፋ የቆረጡ ሁሉ መፈወሻ ሆነ፡፡ ይህ ነው ለውጥ፤ ይህ ነው ክርስትና፤ ይህ ነው ሐዋርያነት፡፡
ዛሬስ ክርስቶስ ከመሳደድ አርፏልን? የሚሳደደውስኢ-ክርስቱን በሆኑት ብቻ ነውን? በሚሉት መጠይቆች እስኪ ራሳችንን እንመርምር፡፡
ኢ-ክርስቱን በሆኑት ክርስቶስ እንደሚሳደድና እንደሚታረድ በሶርያ በኢራቅና በሊብያ ያየናቸው የዘመናችን ዘግናኝ ጭካኔዎችና ቁርጥ የሰማዕትነት መንፈስ በቂ ማስረጃ ስለሆነ ብዙ ማለት አያስፈልግም፡፡(በረከታቸው ይደርብን)
በእኛ በክርስቲያኖችስ ክርስቶስ አይሳደድም? ባል ሚስቱን፤ሚስት ባሏን፤ወላጆች ልጆቻቸውን፤ልጆች ወላጆቻቸውን፤ ወንድም ወንድሙን፤እህት እህቷን ፤ ጓደኛ ጓደኛውን፤ ጎረቤትም አብሮት የሚኖረውን፣የትምህርት የሥራ አጋሩን ወዘተ… ቀን ስጠኝ ጊዜ ፈቀደልኝ ብሎ የሚበድል የሚያሰቃይ ላቡን ድካሙን የሚቀማ ከሥራ የሚያፈናቅል ይህ ሁሉ ክርስቶስን አሳዳጅ አይደለምን?
በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ (በቤተመንግስትም ሆነ በቤተክህነት) የሥልጣን ዙፋን ላይየተቀመጥን ጊዜ ሰጠን የብዕርናየአፈሙዝ ኃይል አጋደለልን ብለን ድሀውን የምንረግጥ፤ ያለመማለጃ ጆሯችን የማይሰማ ዓይናችን የማይገለጥ፤ ስህተታችንን የሚያርም ግፋችንን የሚቃወም ሲገኝ የምናስር የምናግዝ የምናሠቃይ የምንገድል ክርስቶስን ማሳደድ አይደለምን?
ዛሬ በእኛ ክፋት ክርስቶስ በረሃብ ጠውልጓል፤ የጎዳና አዳሪ ሆኗል፡፡ በመድኃኒት ከሰው ተራ ወጥቶ ይባዝናል፤ በጠበል በሆስፒታል ጓሮ ወድቋል፡፡ እኛ ግንከረሃቡ ነጥቀን ታላላቅ ቤተ መቅደሶች እናንጻለን፤ ጥም ካደረቀው ሰውነቱ ለተቀዳ ደሙ የወርቅ ጽዋ እንገዛለን፤እርሱ ጎዳና ወድቆ እኛ በምንጣፍ እናስቀድሳለን፤ የእርሱ እርቃን ተጋልጦ እኛ መጋረጃ እንመርጣለን ፡፡
የጥፋት ሀብት የሰበሰብን ረሃብ ክብሯን ያስጣላት ማጣት በሴትነቷ የፈተናት እህታችንን ርኩሰታችን ልንተፋባት ብልግናችንን ልናስታግስባት በገንዘብ ስናማልላት ከሰውነት ክብር አዋርደን ለመናገር የሚቀፉ ነውር ስንፈፅምባት ክርስቶስን ማሳደድ መሆኑን ረሳነውን?ለመዘርዘር የማይበቃን በታናናሾች ላይ የሚደረግ ሁሉ በእርሱ ላይ እንደሚደረግ ለነገረን ለእርሱ ይህ ሁሉ ስደቱ ሕመሙ አይደለምን?
የሰውን አእምሮ አፍዝዞ ሕዋሳቱን አደንዝዞ ለሀገር ለወገን በሚጠቅምበት የወጣትነት ዕድሜው የእፅ ምርኮኛ የሱስ እስረኛ በማድረግ ከዚያ በሚገኝ ገቢ ኑሮአቸውን ያጸደቁ ‹‹ቢዝነስ›› ነው እያሉ የሚመጻደቁ እኒህ ሁሉ ክርሰቶስን አሳዳጆች አይደሉምን?
ዛሬ የዓለምሕዝብ ምን ያህሉ ይሆን በዚህ ሥራ የተጠመደ? ብዙዎቻችን አገር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ፣የኬሚካልና ባዮሎጂካል መሣሪያዎችን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች እያልን ስንቃወም እንኖራለን፡፡ ነገር ግን ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲዎችን፣ ልቅ የተለቀቁ ጎጂ መጤ ባህሎችን፣ ሰው ፈሪሃ እግዘአብሔር እንዳይኖረውና በራሱ ላይ ብቻ ተጣብቆ እንዲኖር የሚያስተምሩ ሙት የፍልስፍና መጻሕፍትን፤በፊልም፣በሬድዮ፣በኢንተርኔት የሚለቀቁ ልቅ የወሲብና የወንጀል ፊልሞችና ፕሮግራሞችን ወዘተ… እኒህ ሁሉትውልድ ጨራሽ መሣሪያዎች የሚያሳስቡት ግን እጅግ ጥቂቶችን ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?›› ብሎ በጠየቀው ጥያቄ ታላቅ መልስ አግኝቷል፡፡
የጌታችን መልስ‹‹አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ መልስ ጌታችን ለቅዱስ ጳውሎስ የምዕመናን ስደት የእርሱ ስደት፤የክርስቲያኖች መከራና ስቃይ የእርሱ መከራና ስቃይ መሆኑን አስረድቶታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለተበደሉ የሚፈርድላቸው ለተገፉ የሚበቀልላቸው፤ ትዕቢተኞችን የሚያዋርድ የተዋረዱትን ደግሞ ክብር የሚሠጥ፤ የአቤልም ሆነ የቃየል አምላክ ሥራቸውንም የሚመዝንና ዋጋቸውን የሚከፍል በባህርዩ የማይሞት ሥልጣኑ የማይሻር ለግዛቱም ወሰን የሌለው የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ከመልሱ ተረድቷል፡፡‹‹የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሃል›› የሚለው ማስጠንቀቂያ አጥንቱ ደርሶ ዘልቆ ሳውልን አርዶታል፡፡ዛሬም በመውጊያው ብረት ላይ የሚዘብት ብዙ አለ እስኪያዝ ድረስ፡፡
ወዳጄ! በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ብትቀመጥ፣ የሀብት ጫፍ ብትቆናጠጥ የዕውቀትን ማማ ብትረግጥ የሁሉ መጨረሻ አንድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለሥጋ እርካታ ይሆን እንደሁ እንጂ ነፍስህን ከተጠያቂነት አያስጥላትም፡፡