በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ
ከሁለቱ የቤተክርስቲያን አዕናቁ ሕይወት በላዕላይ ዳሰሳ ይህን ከተማርን ከዘመኑ አንጻር አገልጋዩች ምን ሆነው (ታጥቀው) መገኘት ይኖርባቸዋል የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት፡፡
1. በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊው እወቀት ሙሉ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡በመንፈሳዊው የቤተክርስቲያንን እውነተኛ አስተምህሮ በተጨማሪም የተቃዋሚዎችን አካሔድና አስተምህሮ ጠንቅቀው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በየዘመናቱ የተነሱ የሰው ልጅን አስተሳሰብ ያጣመሙ ወይም ያቃኑ ፍልስፍናዎችን መረዳትና በቂ መልስ(ሙግት) ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡በሳይንሱም በይበልጥ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለቸው በሕክምና፣በሥነ-ልቦና፣በማኅበራዊ ሳይንስ፣ ኪነጥበብ፣ ቴክኖሎጂ ወዘተ… ጋር ትውውቅ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ የሰውን ጥያቄ ጹም ጸልይ በሚል ብቻ የምንመልስበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ በክርስቲያኑ በእምነት የሚገለጡና በአመክንዮ የሚመለሱትን ለይተን ማሳወቅ ከእኛ ይጠበቃል፡፡
ምዕመናንም መንቃት ከልማድ መውጣት ይጠበቅብናል፡፡ ብዙዎቻችን ለቤተክርስቲያን ከጧፍ፣ከዕጣን ፣ከመጋረጃና ከምንጣፍ የዘለለ መባመስጠት አለመደብንም፡፡ ስንቶቻችን ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች በይበልጥ መንጋውን ለመጠበቅ ለሚደክሙ መጻሕፍትን፣ የትምህርት ዕድሎችን፣ የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣በጽሙና ሊያነቡ የሚችሉበትን ሥፍራ፣ እነርሱ ያለ ሀሳብ የቤተክርስቲያንን ሥራ እንዲሠሩ ለኑሮ የሚስፈልጋቸውን ወጪ፣ የመጻሐፍት የመጽሔትና የጋዜጣ ማዘጋጃ ወጪን የመሳሰሉት ስናመቻችና ስንደግፍ እንታያለን፡፡እኛ ብል ለሚበላው ምንጣፍ ስንጨነቅ ስንቶችን የኃጢአትና የክህደት ብል እንዳይበላቸውየሚጠብቅ እውቀት በከንቱ እየቀረ ነው፡፡በተጠናና በተቀናጀ ስልት በሚዘረጋ የትምህርተ ወንጌል አደረጃጀት እንጂ በሠርክ ጉባዔ ስብከትና በበዓላት ድምቀት ብቻ ትውልዱን ይዘን እንቀጥላልን ማለት ከሞኝነት ያለፈ ዕብደት ነው፡፡ በተናጠልም ሆነ በኅበረት በመሆን አሥራት በማውጣት ወይም የተለየ በጀት በመመደብ አገልጋዮችን መደገፍ ከሚበልጠውየወንጌል ትሩፋት መሳተፍ ነው፡፡ የጥንቷ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን መለያ የአብነት ተማሪዎችንና መምህራንን መደገፍ መጻሕፍትን አጽፈው አስደጉሰው ለየአድባራቱና ገዳማቱ መስጠት ነበር፡፡
2. የለውጥ አላማጆች(Activist) መሆን፡- በዓለም ታሪክ በተደረጉ የለውጥ ጉዞዎች፣የነጻነት ትግሎችና፣የሰው ልጆች ድኅንነት መጠበቅ የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎች ድርሻ ጉልህ ነበር፡፡ማሀተማ ጋንዲ፣ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ አቡነ ዴዝሞን ቱቱ፣ በሀገራችን ታሪክ ስንመጣ መንግሥታትን በማደራርና ደም መፋሰስን በማስቀረት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለሃይማኖት፣የሃገርን ነጻነት በማስጠበቅ ጻድቁ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና የጎሬው አቡነ ሚካኤል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ዛሬም ካለን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሰው ልጆች ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቶች መከበር፣በተፈጥሮ ደኅንነት ጥበቃ፤በሀገራዊና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ቀዳሚ ወኪሎችና ተሟጋቾች መሆን ይጠበቅብናል፡፡በዘመናዊው አስተሳሰብ የፈላስፎች የፖለቲከኞችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ትልቁ ግብ ሕብረተሰቡን ከሃይማኖትና ከሃይማኖት አባቶች ምሪት ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖቱን የሚያጠብቅና የሃይማኖት አባቶቹን የሚያከብርና የሚከተልን ሕዝብ እንደፈለጉ መንዳት አይቻልምና፡፡ ሃይማኖትና የሃይማኖት አባቶች ለብዙ ሺህ ዓመታት ይዘውት የነበረውን ቦታ ፈላስፎች ፖለቲከኞችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች መቆናጠጥ ይፈልጋሉ፡፡በምዕራቡ ዓለም የሆነውና በስኬት የተፈፀመው ይኸው ነው ፡፡ ሕብረተሰቡ በስልጣኔ ስም ላመነበት ሳይሆን ለተቀረፁለት ሥርዓት(system)ባርያ ሆኖ እየኖረ ያለው ለዚህ ነው፡፡በንግግር የሚጠቅሳቸው በኑሮ ዘይቤውም አብነት የሚያደርጋቸው እነዚህኑ ስለሆነ ከፍተኛ ለሆነ የሥነ-ምግባር ዝቅጠትና የሞራል ውድቀት ተደርጓል፡፡ሌላው ቀርቶ ከሰብአዊ ባህርይ እስከማፈንገጥ ደርሷል፡፡ምክንያቱ አርአያ(Icon) ከሚላቸው የሚያየውና የሚሠማው ቅንጦትን፣ ስግብግብነትን፣ዝሙትን፣ሰዶማዊነትን ወዘተ…ነው፡፡ይህ በእኛ እንዳይደገም ተጨባጭና ቀጥተኛ(Rational)በሆነ መንገድ የሚመክሩ የሚሞግቱና ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በሕዝቡ የታመኑ የሃይማኖት አባቶች መሆን ይጠበቅብናል፡፡
ወደድንም ጠላንም በሕዝቡ ውስጥ ያለንን ቦታለመንጠቅ ያሰፈሰፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ እየተሳካላቸውም ነው፡፡ ለመመለስ ግን አሁንም አቅሙ አለን፡፡ሕዝቡ የሚፈልገው በእኛ እርግጠኛ መሆንን ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ልንሠጠው ያልቻልነው ያን ነው፡፡በየትኛውም ዘርፍ ሕዝቡ ከኋላ ሆኖ የሚገፋው ሳይሆን ከፊት ሆኖ የሚመራው፣ለዓላማው እንዲሞት የሚሰብከው ሳይሆን ሞትን ተጋፍጦ የሚያሳየው መሪ ይፈልጋል፡፡ለዚህ ደግሞ ከመንፈሳዊ መሪዎች የቀረበ የለም፡፡
በበጎ አድራጎት ሥራ ቤተክርስቲያንና የሃይማኖት አባቶች ፊትአውራሪ መሆን ሲጠበቅብን ከእኛ ይልቅ እየተሠራ ያለው በጎ ኅሊና በቀሰቀሰላቸው ሰው መሆን ግድ ባላቸው ምዕመናን ነው፡፡መቅደም ሲገባን ተቀድመናል፣ እንኳ ለመምራት ለመመራትም በምናስቸግርበት ሁኔታ ላይ መገኘታችን ምንኛ አሳዛኝ ነው፡፡
ሕዝቡ ግን አሁንም ከሃይማኖት አባቶች ጉያ ላለመውጣት ያለው ምኞት ትንሽ በሚንቀሳቀሱ አባቶች(እውነተኞች ወይም አስመሳዮች)ሥር ከሚያሳየው ተስፋን ያዘለ መሰባሰብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ልንሠራ ነገሮችን ልንለውጥ የምንችልበት ቀን ሳይጨልም መንቃት የእኛ ፋንታ ነው፡፡